Artcles

ነገረ-ኤች አር 128

By Admin

April 19, 2018

ነገረ-ኤች አር 128

                                                          ሶሪ ገመዳ

የአሜሪካ የህግ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ኢትዮጵያን አስመልክቶ ሰሞኑን ያወጣው ኤች አር 128 በይዘቱ፣ የኢትዮጵያ መንግስት አስቀድሞ የለያቸውን ችግሮችና ችግሮቹን ለመፍታት ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች እና በተግባርም እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎች እየመጡ ካሉት ለውጦች አንጻር ወቅታዊነት እና ተገቢነት የሌለው ነው።

ውሳኔው የአሜሪካ መንግስት አቋም ሳይሆን የተወሰኑ የኮንግረስ አባላት ጥቂት የዲያስፖራ ተቃዋሚ አካላትን ለማስደሰት ብለው ያስተላለፉት ይመስላል። በአንጻሩ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ ውሳኔው እንዳይተላለፍ ሲታገሉ የነበሩ የኮንግረስ፣ የሴኔትና የዋይት ሃውስ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት መኖራቸውም ቅሳኔው ሁሉንም የኮንግረሱን አባላት ይሁንታ እንዳላገኘ የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ረጅም እድሜ ያስቆጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው። ግንኙነታቸውም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው። በመሆኑም ውሳኔው በአገራችን ላይ የሚያሳድረው አንዳችም ተፅዕኖ አይኖርም።

የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም “አለቃችን ህዝቡ ነው፣ ተጠያቂነታችንም ለህዝባችን ነው” የሚል በመሆኑ መቼም ቢሆን ለውጭ ተፅዕኖ የመንበርከክ ታሪክ የለውም። ሆኖም እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲ አራማጅነታችን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሊደግፈን የሚፈልግ አካል ካለ አንቀበልም የምንልበት ምንም ምክንያት የለም።

ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስከበር ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዘናል። የአገራችን ህዝቦች ባለፉት ስርዓቶች ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባይተዋር ነበሩ። ያኔ ሰብዓዊ መብቶች በአገራችን ይከበር የነበረው ለገዥዎች እንጂ ለህዝቡ አይደለም። ህዝቡ በገዛ ሀገሩ ሰብዓዊ መብቶቹ ተጥሶበት፣ ሰው መሆኑም ሳታወቅ እጅግ ዘግናኝ ሁኔታዎችን አሳልፏል። ይህ ሁኔታም ህዝቦች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲጓዘ ያስችላቸው ዘንድ ለትግል ያነሳሳቸው ጉዳይ ሆኗል። በዚህም ህዝቡ ይህንንና ሌሎች መብቶቹን ለማስከበር ከፍተኛ ትግል አድርጓል። ባካሄዱት መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል ይህን መብቶቻቸውን ማስመለስ ችለዋል።

በዚህም ባለፉት 27 ዓመታት ራሳቸው ተስማምተው ባፀደቁት ህገ መንግስት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን መጎናፀፍ ችለዋል። የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አለመኖር በመሆኑና ይህ የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቂ ምላሽ በማግኘቱ ነው። እነዚህ መብቶች የራሳቸው ተግዳሮቶች ቢኖሩባቸውም፣ ችግሮች በሂደት የተፈቱ ሰብዓዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲተገበሩ ማድረግ ተችሏል።

እርግጥ የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ለዜጎች ካጎናፀፋቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል የቡድንና የግለሰብ መብቶችን መጥቀስ ይገባል። መብቶቹ በዋነኛነት የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን ማቅረብን የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች ሀገራችን ውስጥ ጥበቃ እየተካሄደላቸው ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ በተጨባጭ ገቢራዊ እየሆኑ የመጡም ጭምር ናቸው።

በተለያዩ ወቅቶች በተደጋጋሚ ይካሄዱ የነበሩት ሰላማዊ ሰልፈኞችና ባለቤቶቹ ህግን እስካልጣሱ ድረስ ከፖሊስ ምንም ዓይነት ትንኮሳ ሲደርስባቸው አልተመለከትኩም። እናም ለእኔ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ በሀገራችን ውስጥ የሚታየው ተደራጅቶ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያመላክትና ለፖለቲካ ሂደቱ አዲስ መንገድ በሂደት እየታየ መሆኑን የሚያንፀባርቅ ይመስለኛል።

የሃይማኖት ነጻነትን በተመለከተም የሚነሳው ክርክር ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የሚጣጣም አይመስለኝም። ምክንያቱም የኢፌዴሪ ህገ- መንግስት የመንግስትና የሃይማኖት መለያየትን በግልፅ መደንገግ ብቻ ሳይሆን ድንጋጌውም ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ በመሆኑ ነው።

እስካሁን ድረስ መንግስት ከድንጋጌው በማንኛውም ሃይማኖት ጣልቃ ገብቶ ‘ይህን አድርግ ያንኛውን ደግሞ ተው’ ያለበትን ሁኔታ ለማስታወስ ይከብደኛል። የሃይማኖት መሪዎችን ሲሾምና ሲሽርም የታዘብኩበት አግባብ የለም፡፡ እርግጥ በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄዱ የሽብር ተግባራትን የማውገዝ፣ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ የመንግስት ግዴታ መሆኑ ማንም የሚክደው ሃቅ አይደለም። ሆኖም እነዚህ ተግባራት ከሃይማኖት አክራሪነት እንጂ፤ ከሃይማኖት ነጻነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።

መንግስትና ሃይማኖት በተለያዩበት ሀገር ውስጥ ሃይማኖታዊ መንግስትን መመስረት አይቻልም። እናም ይህን ችግር ለመፍታት መንግስት በሃይማኖት ስም በሚነግዱ ፖለቲከኞች ላይ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል።

በመሆኑም የሃይማኖት አክራሪነት ሀገራችን ከምትከተለው ከዴሞክራሲ መርሆዎች አንፃር የሚጋጭ ከመሆኑም በላይ፤ መንግስት የሁሉንም ዜጎች የእምነት ነፃነትና የሃይማኖት እኩልነት ህገ-መንግስታዊ መርሆዎችን ለማስጠበቅ የሚያደርጋቸው ጥረቶች ከሃይማኖት ነፃነት ጋር የሚቆራኙበት ምክንያት ለማንም ግልፅ የሚሆን አይመስለኝም።  

በአጠቃላይ ቀደም ሲል ያነሷኋቸው ክርክሮችና እኔም ከራሴ እይታ በመነሳት መልስ ለመስጠት የሞከርኳቸው ጉዳዩች ሙሉ ለሙሉ ምንም ዓይነት ችግሮች የላቸውም የሚል እምነት የለኝም። በሂደት የሚፈቱ ተግዳሮቶች መኖራቸው እሙን ነው። ይሁንና በደፈናው ‘ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እዚህ ሀገር ውስጥ የሉም’ የሚያስብሉ አይደሉም። የኮንግረሱ አባላት ይህን እውነታ አልተገነዘቡትም።

ከ27 ዓመታት በፊት ከነበረው ኮሚኒስታዊ ስርዓት ተነስቶ፣ ዛሬ ሊፈቱ ተግዳሮቶች ቢኖም የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት ማክበርና ማስከበር ትልቅ እመርታ ይመስለኛል። እርግጥ ዛሬ እዚህ ሀገር ውስጥ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበረው የሌሎችን ፍላጎትን ለማሟላት ወይም የውጭ መንግስታትን ለማስደሰት አይመስለኝም።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሀገራችን ውስጥ በውጭ ሃይሎች አማካኝነት የሚዘወሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊኖሩ አይችሉም፤ አይገባምም። ምክንያቱም መብቶቹ የሚከበሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ትግል ውጤት እንዲሁም የሀገሪቱ የህልውና ጉዳይ ስለሆኑ ብቻ ነው።

በመሆኑም ባለፉት 27 ዓመታት የተናወኑትንና ዕመርታ ያሳዩትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማጣጣል የሚቻል አይመስለኝም። የተገኙት ውጤቶች ማንም ሳይጠይቃቸው ራሳቸው የሚናገሩ በመሆናቸው ነው። እነዚህ ውጤቶች የተገኙት መንግስት ባደረጋቸው ቁርጠኛ ውሳኔዎች ነው።

እርግጥም ባለፉት ስርዓቶች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይፈፀምበት የነበረው የሀገራችን ህዝብ፤ በራሱ ትግል ባገኘው በምት ሰብዓዊ መብቶቹን ሊያረጋግጥ ችሏል። በስም ብቻ ወይም ሲነገሩ የመጡ ሰብዓዊ መብቶችን ይሰማ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ ላይ የመብቶቹ ተጠቃሚ ሆኑ ለልማቱ እየተጋ ነው። ሰብዓዊ መብቶቹ ያልተከበሩለት ህዝብ ልማትን ሊያረጋግጥ አይችልም። በዚህም ሳቢያ የሀገራችን ህዝቦች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ስለተከበሩ ባለፉት 16 ዓመታት ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጡ ነው። ይህም ሰብዓዊ መብቶች ከዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ተለይቶ የሚታይ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ነገረ-ኤች አር 128 ከዚህ አኳያ መታየት ይኖርበታል።