Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አስተሳሳሪው ድር

0 308

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አስተሳሳሪው ድር

                                                    ዘአማን በላይ

በዓባይ ወንዝ ጉባ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቀጣናው አስተሳሳሪ ድር ነው። ይህ ድር የሚበጠስ አይደለም። አስተሳሳሪው ድር አሁን በሚገኝበት ቁመናው 65 በመቶ ደርሷል። ይህ ረጅም እመርታ ብቻ አይደለም። ለተፋሰሱና ለቀጣናው ሀገራትም የምስራች ጭምር ይመስለኛል። ውሃው ምግብ፣ መጠጥ፣ ፋብሪካ…በጥቅሉ የዕድገት ምሶሶ ሊሆን ነውና።

ይህን አብሮ የማደግ መንገድ የሚቃወም ሃይል አዲሱ የሉላዊነት የትስስር ድር ያልገባውና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ እንደሌለ የሚቆጠር ነው። ምክንያቱም የቀጣናው የዕድገት አስተሳሳሪ ድር የእኛና የሁሉም ወንድሞቻችን ጭምር በመሆኑ ነው። የጋራ ተጠቃሚነትን የሚጠላ ባለመኖሩ ድሩን ለመበጠስ የሚደረጉ ማናቸውም አሉታዊ ጥረቶች ልማትን ከመቃወም ተለይቶ የሚታይ አይመስለኝም።

ርግጥ ነው—እዚህ ላይ አንዳንድ የግብፅ ተቋማት “ከመንግስታቸው ዕውቅና ውጭ” በሚመስል መልኩ፤ እንደ 21ኛው ክፍለ ዘመን ተቋማት ሲንቀሳቀሱ እንደማይስተዋሉ እዚህ ላይ አለመግለፅ ራስን እንደ መዋሸት የሚቆጠር ይመስለኛል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ላለፉት 16 ተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ ላለፉት 27 ዓመታት ተጉዟል።

በሂደቱም የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት መብቃት ችሏል። በዚህም ህዝቡን ከጫፍ እሰከ ጨጠጫፍ በማንቀሳቀስ ሀገራችን የያዘቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የሀገራችን ህዝብ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረገና ግብፆች አሁን ለደረሱበት “የአቋም ለውጥ” መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች ስትገልፅ ቆይታለች፡፡

የሀገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው።

ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የ“ይቻላል” መንፈስን መፍጠር የቻለና ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍ የሚያደርገን ነው። እናም ቢያንስ በእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የሀገራችንን ፍትሐዊና “ኑ አብረን እንጠቀም” የሚል ቀና አስተሳሰብን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፤ ለየትኛውም ወገን ቢሆን።

ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ በጉልህ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች።

ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም። እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች። በሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቷም ግንዛቤም ማስያዝ ችላለች።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲከናወን የተወሰነው ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ተጠግቶ ነው፡፡ ይህም ግድቡ ለመስኖ አገልግሎት ሊውል እንደማይችል ያሳያል። እናም ግድቡ የኤሌትሪክ ሃይልን የማመንጨትና የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ሀገራዊ ልማትን ከማፋጠን ውጪ፤ ጉዳትን ያዘለ አይደለም፡፡

ሌላ ምክንያት ላክል፡፡…የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድቦች ሃይልን ከማመንጨት ባሻገር፤ አንድ ጠብታ ውሃም ቢሆን እንደማያባክን ሁሉም ጠንቅቆ የሚያውቀው ዕውነታ ነው፡፡ ግድቡ የማንኛውም ሀገር ጥቅም ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ የማያበረክትና የማይነካና የጉዳት መጠኑም እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን አስረድቷል፡፡

አንዲያውም ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ በየዓመቱ ሲደርስ የቆየውን ከፍተኛ የውሃ ትነት መጠን የሚያስቀር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው። እናም ይህ ምስክርነት እንደ ግብፅ ተቋማት ያሉ ሃይሎችን “የይጎዳናል” አስተሳሰብ ቅቡል እንዳይሆን የሚያደርገው ነው።

እናም የኢፌዴሪ መንግስት እነዚህንና ሌሎች እውነታዎችን በዲፕሎማሲ ጥረት በመደጋገም ማስረዳት ያለበት ይመስለኛል። ርግጥ በዲፕሎማሲ ጥረቱ ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ መምጣት የቻሉ ይመስላል። ቢያንስ ግልፅ በሆነ መንገድ ከሚያከናውኑት ተግባር በመነሳት። ይህ በጎ መንገድ እንዲበረታታም የግብፅን መንግስት ኦፊሴላዊ መግለጫን ከዚያች ሀገር ተቋማትና ሚዲያዎች ለይቶ መመልከት ተገቢ ነው።

ርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ የሀገራችንን መቼም የማይቀየር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ዕውን የሚያደርግና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አካሄድ በዘመነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ማሳየት ይገባል።

በተጨማሪም ከህዳሴው ግድብ አኳያ ሶስቱም ሀገራት የሄዱበት በሰከነ መንገድ የመደማመጥ መንፈስ እንዲጠናከር ተገቢውን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ ጊዜያዊ ስሜቶች በሚፈጥሯቸው ሁኔታዎች መነዳት አይኖርብንም።

ዲፕሎማሲያችን አሁን እየተደረገ ባለው የሰከነ መንፈስ እየታገዘ ሁኔታዎችን ይበልጥ በማስረዳትና የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር እያደረገ መጓዝ ይኖርበታል። በዓባይ ወንዝ ላይ የሚደረጉ የልማት ስራዎች ሁሉንም ሀገራት የመጥቀምና እንደ ድር አቆራኝቶ የሚያስተሳሰር እንዲሁም የሚያስተባብር እንጂ የቅራኔና የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደማይችል አሁንም ማስረንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy