Artcles

አክቲቪስት ተብዬዎቹ

By Admin

April 04, 2018

አክቲቪስት ተብዬዎቹ

ዳዊት ምትኩ

ሰሞኑን በድጋሚ የታሰሩት አክቲቪስት ተብዬ ግለሰቦች የህግ የበላይነትን የጣሱ ናቸው። ሰሞኑን የወጡ አንዳንድ ዘገባዎች እንደገለፁት እነዚህ አክቲቪስት ተብዬዎች አሜሪካውያን ለቀለም አብዮት ቅስቀሳ አቅጣጫ ሰጥተዋቸው ነበር። ይህም ከአሜሪካ ኤምባሲ ዌብሳይትና በራዲሰን ብሉ ሆቴል ተካሂዷል ከተባለ ስብሰባ እንደሆነ ተገልጿል። የአሜሪካ አክቲቪስት ተብዬዎቹ ሕገ ወጥ ባንዴራ በመያዝና ያልተፈቀደ ስብሰባ በማድረግ መንግስትን ለመፈታተን ሆን ብለው ያደረጉት መሆኑ ግልፅ ነው። ያም ሆኖ ግን መንግስት በህግ የበላይነት ላይ ሊደራደር አይችልም። በመሆኑም አክቲቪስት ተብዬዎቹ የታሰሩበት ምክንያት የሀገራችንን የህግ የበላይነት ልዕልና በመጣስ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ዕውን ለማደረግ ውድ የህዝብ ልጆች ባካሄዱት እልህ አስጨራሽና መራር ትግል መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። በዚህም በ1988 ዓ.ም. በቁጥር 16/1988 ‘የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ’ እንዲወጣ መሰረት ጥለዋል—ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ሰንደቅ ዓላማውን ላስረከቡን ውድ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልጆች ክብርና ምስጋና ይግባቸውና።

ታዲያ ይህን ዕውነታ በሚገባ የተገነዘቡት የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የሰማዕታቱን አደራ ተቀብለው በተለይም ላለፉት 23 ዓመታት በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ተሰባስበው አያሌ ሀገራዊ ተግራትን ፈፅመዋል። ዙሪያ መለስ ዕድገትን እያስመዘገቡም ዛሬ ላይ መድረስ ችለዋል።

እርግጥ በህገ-መንግስቱ ሳቢያ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ መብቶች (የግልና የቡድን) በተቀናጀ መልኩ አንዱ የሌላውን በሚደግፍ አኳኋን ተመልሰዋል። በዚህም ብዝሃነትን ለማስተናገድ ችግር የነበሩ በርካታ ጉዳዩች ሊመለሱ ችለዋል። ይህም የሀገሪቱ ልማት ላለፉት 14 ዓመታት ያለ አንዳች ሳንካ ፈጣንና ተከታታይ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል አድርጓል።

እርግጥ ባለፉት ዓመታት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ትሩፋት ሊገኝ የቻለው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት እየተመሩ ብዝሃነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ አድርገው በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው ሌት ተቀን በመስራታቸው መሆኑን ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።

በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን የጥንካሬው መሰረት አድርጎ በመቁጠር በ‘ባንዴራው’ ስር ተጠልሎ ድህነትን ለማሸነፍ ላለፉት ዓመታት ታግሏል። የትግሉ ባለቤትም በመሆን ላይ ይገኛል። ለዚያውም ከዓለም በፈጣን ዕድገት ከቻይና እና ከህንድ ቀጥሎ የልማት ተምሳሌታዊ ማማውን ጫፍ ላይ ሰቅሎ። እናም ድሉን ይበልጥ ለማጠናከር የሚችልበትን በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከአንዴም ሁለቴ ተልሞ ወደ መከከለኛ ገቢ የመገስገስ ራዕዩን ተያይዞታል—ነገሩ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉት ነውና።

አበው “ለብልህ አይነግሩትም” እንዲሉ፣ በሁሉም የልማት ዘርፎች ከጫፍ እሰከ ጫፍ በመንቀሳቀስ በ‘ባንዴራው’ አጊጦና አሸብርቆ የትናንት የውርደት ምንጩ የሆነውን ድህነት ዛሬ ላይ ድል በመንሳት ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው—የሀገራችን ህዝብ። ብዝሃነቱ የድሉ ምንጭ እንጂ የልዩነቱና የመፋለሱ ምክንያት እንዳልሆነ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት በተግባራዊ ክንዋኔው ያረጋገጠው ይህ ህዝብ፤ ነገም ይህን ጥንካሬውን አጠናክሮ መቀጠሉ አጠያያቂ አይሆንም።

ይሁን እንጂ ከዚህ የህዝቡ ፍላጎት ውጪ በሆነ መንገድ ከላይ የጠቀስኳቸው አክቲቪስት ተብዬዎች እዚህ ሀገር በተጨባጭ በመምጣት ላይ ያለውን ለውጥ በማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች ህገ ወጥ ባንዴራ በማውለብለብ የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ለማኮስመን ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ የህዝቦች አንድነትና እኩልነት የሆነውን መሰረታዊ ጉዳይ አለመቀበል በመሆኑ ከህገ መንግሰቱ ጋር የሚጣረስ ነው። ተቀባይነትም ሊኖረው አይችልም።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የሀገራችን ህዝቦችና ሃይማኖቶች አንድነትና እኩልነት መገለጫ በመሆን ዜጎች በስሩ ተሰባስበው ዛሬ ላይ ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት ነው። ስለ ሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሲነሳ፤ ጉዳዩ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም ከግምት ውስጥ ገብቶ ይመስለኛል።

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው በየትኛውም ሀገር ውስጥ በቡድንም ይሁን በሀገር ደረጃ ከአንድነት ውጪ የሚከናወን ምንም ዓይነት ነገር የለም። አዎ! አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል። አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖሩ ይመስለኛል።

የሀገራችን ህዝቦች አንድነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው እንዲሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕኑ ፍላጎትንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው። የዚህ ዕውነታ ነፀብራቅ መሰባሰቢያ ጥላ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሆኑ አይካድም። እናም የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ህዝቦች ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ጠብቀው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን የትኛውም ወገን ሊያውቀው የሚገባ ይመስለኛል።

ሰንደቅ ዓላማው በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የተቀየሰው ህዳሴ መሰረትም ነው። ከዚህ አኳያም ሀገራችን በምጣኔ-ሃብት እንድታድግ፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ዕድገት ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ብሎም በርካታ ተግባራት ገቢራዊ ሆነው ውጤት ተገኝቶባቸዋል፤ በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ። ለዚህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ፍትህ መረጋገጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተ ይመስለኛል። ህዳሴያችንን ለማረጋገጥ የምንሰበሰብበት ጥላ ነው።

ህዳሴውን እውን ለማድረግና መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን የሚሻ ዜጋ ሁሉ ከሰንደቅ ዓላማው አንፃር የሚነሱ ማናቸውንም ተግባራት ሊቃወምና የድርጊቱን ፈፃሚዎች በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅበታል ባይ ነኝ። ህገ ወጥ ባንዴራ ማንገብም ተቀባይነት የለውም።

ህገ ወጥ ሰንደቅ ዓላማን ይዞ መገኘት በአንድነትና በእኩልነት ሊገኙ የሚችሉ ትሩፋቶችን ‘አልፈልግም” ከማለት ባሻገር፤ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መፃረር መሆኑ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል። በቅርቡም ዳግም የታሰሩት አክቲቪስት ተብዬዎች ሰንደቅ ዓላማውን ባለማክበር የሚፈፀሙ ተግባራት ከዚሁ አንፃር የሚታዩ ናቸው።

አገራችን ውስጥ በሚካሄዱ ማናቸውም ስብሰባዎች የሚታዩ የማይታወቁ ሰንደቅ ዓላማዎች የህዝቦችን አንድነት የማይቀበሉ እንዲሁም የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ እኩልነት መብቶችን የሚነፍጉ በመሆናቸው በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት ሊኖራቸው ስለማይችል የህግ የበላይነት ተፈፃሚ መሆኑ የግድ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ክልከላዎች በመተላለፍም ያልተፈቀደ ስብሰባ ማድረግ በግልፅ የህግ ልዕልናን መፃረር በመሆኑ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም። በአክቲቪስት ተብዬዎቹ ላይ የተወሰደው ርምጃም ይኸው ነው።