Artcles

አይቀሬው ለውጥ

By Admin

April 17, 2018

አይቀሬው ለውጥ

ዳዊት ምትኩ

መሪው ድርጅትና መንግሥት እያካሄዱት ባለው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ፤ ያለፉ ዓመታት አፈጻጸማቸውን በጥልቀት በመፈተሽ ጠንካራ ጎናችን ለማስቀጠል እና ደካማ ጎኖችን ለማረም የሚያስችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጠው ወደ ተግባር ገብተዋል። ከህዝቡም ጋር በመሆን ያሉትን ችግሮች ነቅሰው በማውጣት እየተረባረቡ ናቸው። ወደፊትም የተሃድሶውን እንቅስቃሴ ሕዝቡ ይበልጥ በባለቤትነት ሲረከበው አገራችን ያጋጠማት እያንዳንዳንዱ ችግር መፈታቱ አይቀሬ ነው።

በአሁኑ ሰዓት ኢህአዴግና መንግሥት የአገሪቱን ችግር ከመጠን በላይ ወደ ውስጥ መመልከታቸውንና ቀደም ሲልም የነበረውን ጥንካሬ መልሶ ለማምጣት አስፈላጊውን ሥራ እያከናወኑ ነው። ተፈላጊው ለውጥም በሂደት እየመጣ ነው። ያም ሆኖ ‘የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋል’ የሚል እምነት ያላቸው አንዳንድ ወገኖች ፍላጎታቸውን ገቢራዊ ለማድረግ ቢፈልጉ እንኳ ብዙ መሥራት እና በዋነኛነትም ህዝቡን ማሳመን ይጠበቅባቸዋል። ይህ ግን ሊሳካ የሚችል አይደለም። ምናልባት በህዝቡ ፍላጎት የተመሰረተውን ሥርዓት እንለውጥ ብለው ቢያስቡ እንኳ፤ አገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ የሚፈቅድላቸው አይሆንም። ምክንያቱም ሥርዓቱ የተመሰረተው በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቃድና ፍላጎት በመሆኑ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በህዝቡ የተመሰረተና ግቡም ህዝቡን ማገልገል ነው። ሥርዓቱ ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም። በየትኛውም የስልጣን እርከን ውስጥ ያለ አመራር ከህዝቡ ፍላጎት ውጭ መሆን የሚችልበት ሁኔታ በፌዴራላዊ ፅርዓቱ ውስጥ ተቀባይነት የለውም።

በመንግስት ስራ ላይ የሚገኝ አመራር የህዝቦችን መብት በሚሸርፍበት ወቅት የሚያስተካክለው ራሱ ህዝቡ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱትና በመካሄድ ላይ ያሉት ህዝባዊ መድረኮች የዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።

በየመድረኮቹ ህዝቡ ፍላጎቱን ይገልጻል፤ የተፈፀሙበትን የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በማቅረብ የሚመለከተው አካል ከቦታው እንዲነሳ ያደርጋል። ይህም ሥርዓቱ የህዝብና በህዝብ የሚመራ እንደሆነ ያሳያል። የሥርዓቱ መነሻም ይሁን መድረሻ ህዝቦች በመሆናቸው የህዝብ ንቅናቄ እሳት በሆነ ቁጥር የአመራሩ መቀጠል ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባም የሚገልፅ ነው። የሥርዓቱ ህዝባዊነት ማረጋገጫም ናቸው።

እርግጥ በህገ መንግስቱ የተለያዩ አንቀፆች ላይ የተቀመጡት ሁሉም መብቶች የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በትግላቸው የተጎናፀፏቸው ትሩፋቶች ናቸው። እነዚህን ህገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን መብቶች ተጠቅመውም የበርካታ ትሩፋቶች ባለቤቶች ሆነዋል።

ዛሬ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ ባለቤቶችና ለሌሎች አፍሪካውያን አርአያ የሚሆን ዕድገት በሁሉም መስኮች እያስመዘገቡ ነው። በዚህም የህዳሴያቸውን ጉዞ ቅርብ ለማድረግ ግስጋሴያቸውን ተያይዘውታል።

ሆኖም በዚህ ሂደት ውስጥ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት ይበልጥ መስፈን ይኖርበታል። የመንግስት አሰራሮች ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መንፈስ እውን መሆን አለበት። ይህ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሀገሪቱ ህዝቦች መንገስት እንደያከናውነው የሚፈልጉት ጉዳይ ነው።

እናም መንግስት ሁሌም በአሰራሮቹ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም በመሆኑ በየጊዜው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የየወራት ስራዎቹን ያቀርባል። ያስገመግማል። መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላል።

በዴሞክራሲ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው። ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው።

እናም የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 27 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ጅምር በመሆኑ ምንም ዓይነት ችግሮች የሉበትም ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም። አሁን የምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም።

በመሆኑም አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል። የአሰራሩን ተጠያቂነትና ግልፅነት በዚያኑ ልክ ለህዝቡ ማረጋገጥ አለበት። በእነዚህ ጉዳዩች ዙሪያ ረጅም ርቀት መሄድ ቢቻልም፤ ችግሮች መኖራቸው ግልፅ ነው።

ገዥው ፓርቲና መንግስት እያካሄዱ ባሉት የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከህዝቡ ጋር በመሆን እየተረባረቡ ነው። ወደፊትም ህዝቡ በባለቤትነት መንፈስ ሙሉ ለሙሉ መንቀሳቀስ ሲጀምር ችግሮቹ ፈር መያዛቸው አይቀሬ ነው። እናም ችግሮቹን ለመቅረፍ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ሃሳብ ማራመድ ምክንያታዊ አይደለም። ለምን? ከተባለ፤ አንድን በመጠኑ ዘመም ያለ ቤት በአነስተኛ ወጪ በቀላሉ ማቃናት ሲገባ ‘ቤቱን እናፍርሰው’ የሚል ዓይነት ሃሳብ መስጠት ስለሚሆን ነው።

መፍትሔዎች እየተበጁና ችግሮች እየተቀረፉ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት ‘የስርዓት ለውጥ’ን ማቀንቀን ተገቢ ሊሆን አይችልም። ሃሳቡ የጥቂቶች ከመሆኑም በላይ ይህን ማድረግ የሚችሉት የአገራችን ህዝቦች ብቻ ናቸው። ውህዳኖች ምንም ዓይነት ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም። ከሃሳብነት በስተቀር ኢ-ህገ መንግሥታዊም ነው።

በአገራችን ውስጥ ዜጎች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነታቸው ተረጋግጧል። ምክንያቱም ዛሬ አገራችን ውስጥ ጠያቂና ሞጋች ማህበረሰብ ከመፈጠሩም ሌላ በተገቢው መንገድ የመንግስትን አገልግሎት የማይሰጥ ሁሉ በህዝቡ ከፍተኛ የንቅናቄ መድረኮች ተጠያቂም እንዲሆን እየተደረገ ስለሆነ ነው። እርግጥ ኢትዮጵያን ከአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት አገዛዝ ያላቀቀው ኢህአዴግ መራሹ ሥልጣን በህዝብ እና በህዝብ ብቻ የሚረጋገጥ እንደሆነ በማመን ዜጎች የትግላቸው ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነታቸውን አስመልክቶ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 8 ላይ፤ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሚሆን ተደንግጓል። ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በራሳቸው በባለቤቶቹ ካልሆነ በስተቀር በማንም ሊሻር የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ድንጋጌው በግልፅ እንደሚያሳየው፤ ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ ህዝብ ያዛል እንጂ አይታዘዝም። የፍላጎቱን ይፈፅማል እንጂ በአንዳንድ ‘የሥርዓት ለውጥ’ ናፋቂዎች “ይህን ከውን፣ ያንን ደግሞ አታድርግ’ ሊባል አይችልም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ትብብሩና ፋና ወጊነቱ ይጠየቃል እንጂ ሊገደድ አይችልም። ሁሉም ነገር በስምምነትና በጋራ አመራር ተፈፃሚ እንዲሆን ይፈለጋል እንጂ፤ ህዝብ አሊያም ወኪሎቹ ሳያውቁትና ሳይመክሩበት የሚከናወን አንዳችም ነገር አይኖርም። እናም ይህ ህዝብ አሁን እየፈጠረ ካለው የጠያቂነት ሁኔታ አኳያ ጥረቱን አጠናክሮ ሲቀጥል ከገዥው ፓርቲና ከመንግሥት ጋር በመሆን ያሉትን ችግሮች መፍታቱና በለውጥ ጎዳና ላይ መራመዱ አይቀሬ መሆኑን ማንም ሊጠራጠር አይገባም።