Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖሊሲ እንድታወጣ ተጠየቀ

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በችግሮች የተተበተበ ስለሆነ፣ ችግሮቹን ለመፍታት መንግሥት የአጠቃቀም ፖሊሲ እንዲያወጣ ተጠየቀ፡፡

ይህ ጥያቄ የቀረበው ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ከተውጣጡ ወጣቶች ሐሙስ መጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል የፓናል ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህርና የዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ያለውን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የሚቆጣጠርና የሚመራ አካል የለም፡፡ በዚህም ሳቢያ ችግሮች እየተፈጠሩ ስለሆኑ መንግሥት የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖሊሲ ማውጣት አለበት ብለዋል፡፡

አቶ አስማኸኝ ‹‹ማኅበራዊ ሚዲያና የአገር ግንባታ›› በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖሊሲ ከማውጣቷ በተጨማሪ መንግሥት ሊቆጣጠረው የሚችል የአገር ውስጥ የማኅበራዊ ሚዲያ ሊኖር ይገባል፡፡

ከስብሰባው ተሳታፊ ወጣቶች መካከል ማኅበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ጠቁመው በኢትዮጵያ የተሳሳቱና ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ፣ የዜጎችን የአብሮ መኖር እሴት የሚሸረሽሩ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው ያሉ አሉ፡፡ ችግሩ ሊፈጠር የቻለበት ዋነኛው ምክንያትም መንግሥት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝቡ ባለማድረሱና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ተገቢውን ሥራ ባለማከናወናቸው እንደሆነ የተናገሩም አሉ፡፡ በጥር ወር 2010 ዓ.ም. በወልዲያ የተፈጠረውን ግጭት በተመለከተ የመንግሥት ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ሲያደርሱ እንዳልነበረና በዚህ ሳቢያም የከፋ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን የገለጹ ነበሩ፡፡

ከአገሪቱ የቀደመ ታሪክ ጋር የማይመጥን ችግር እየተፈጠረ መሆኑን፣ የአገሪቱ ሚዲያዎችም ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቀውና የተሟላ የሰው ኃይል ይዘው ከአንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ግለሰብ አንሰው የሚታዩበት አጋጣሚ እንዳለ የጠቆሙም ነበሩ፡፡

በተዘጋጀው የወጣቶች የፓናል ውይይት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የተሳሳቱና የአገርን ህልውና የሚንዱ መረጃዎች እንደሚተላለፉ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም በጎ ዓላማ በሌላቸው የመረጃ ምንጮች ግለሰብንና ሕዝብን ብሎም አገርን ለጉዳት ሊዳርጉ የሚችሉ መልዕክቶች ሲተላለፉ እንደነበር አስታውሰው፣ ወጣቱ ከእንዲህ ዓይነት አባዜ መውጣት እንዳለበትና በአገሪቱ ሁንተናዊ የዕድገት እንቅስቃሴ መሳተፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹ዘመን ባመጣው የወቅቱ ማኅበራዊ ሚዲያ በምርቃና እየተጻፈ አንዱ አንዱን እንዲቃወም ችግር እንዲፈጠር ሲሠራ ይታያል፤›› ብለዋል፡፡ ወጣቱ ግን ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማና ለአገር ግንባታ እንዲጠቀምበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy