Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እርጥባን ሰብሳቢዎቹ…

0 479

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እርጥባን ሰብሳቢዎቹ…

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ራሱን “አርበኞች ግንቦት ሰባት” እያለ የሚጠራውን ቡድን መጠሪያ አይቀበለውም። ምክንያቱም በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ራሱን “ግንቦት ሰባት” እያለ የሚጠራው የሽብር ቡድን ስለሆነ ነው። ቀሪው “አርበኞች” የተሰኘው ፀረ ሰላም ቡድን የኤርትራ መንግስት ጥርጣሬ ሲያስድርበት ከሽብርተኛው “ግንቦት ሰባት” ጋር አጣብቆ የሰፋው ነው። እናም እኔ በበኩሌ ለዚህ ፀረ ሰላም ሃይል እውቅና አልሰጥም። መንግስትም የሚሰጥ አይመስለኝም። አይታወቅምም። የኤርትራ መንግስት እራፊ ቡድኖችን ሰፍቶ ባጣበቀ ማግስት እኛም እርሱን ተከትለን መንጎድ የሚገባን አይመስለኝም።

የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ስለ ስያሜ ክርክር አይደለም— እግረ መንገዴን በአንዳንድ ሚዲያዎች ሳይቀር ለተጣማሪው የሽብር ቡድን እውቅና መሰጠት የለበትም ለማለት እንጂ።…እናም የዚህ አነስተኛ መጣጥፍ መነሻ ሰሞኑን የአሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ነዓምን ዘለቀ ከቢቢሲው “ሃርድ ቶክ” ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነው። ሰውዬው በቃለ ምልልሳቸው ውስጥ የውሸት ክምርን ሲወቁ ነበር። ከበርካታ ክምራቸው ውስጥ ሁለት ጉዳዩችን ብቻ ለማንሳት እሞክራለሁ።

አንደኛው፤ ትናንት የእነ ዶክተር ብርሃነኑ ነጋ ‘ቀስተ ደመና፣ ቅንጅት…ምንትሴ’ ቡድን ሀገር ቤት እያለ በሰላማዊ መንገድ ሲንቀሳቀስ “አሰብን ከኤርትራ እናስመልሳለን” ሲል እንዳልነበር፤ ዛሬ ለቢቢሲው ጋዜጠኛ “ባድመ ለኤርትራ ተወስኗል” በማለት ያነሱት ጉዳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ ጋዜጠኛው “በግብፅ ትረዳላችሁ ወይ?” በማለት ላቀረበው ጥያቄ “አንረዳም” የሚል ውሸትን ከማሰማታቸውም በላይ፤ ‘ቢሰጡን ከመቀበል ወደ ኋላ አንልም’ የሚል ቀልድ አዘል ዲስኩርንም አሰምተውናል።

እነ ነዓምን ዘለቀ ከኤርትራ መንግስት የወረሱት ትልቁ ነገር ‘በማንኛውም ጊዜ ውሸት ከመናገር ወደ ኋላ አትበል’ የሚለውን የአስመራውን ቤተ መንግስት መዝገበ ቃላት የሚገኘውን መርህ ይመስለኛል። ሻዕቢያም ይህን መዝገበ ቃላት አስመራና ምፅዋ ውስጥ አስቀምጦ ቃለ ምልልስ ሲደረግለት በሃሳቡ ገለጥ እያደረገው ውሸትን ቆርጦ በመቀጠል ይሟገትበታል። ‘ልጅ በአባቱ ይወጧል’ ይሏል እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ይመስለኛል።

“ግንቦት ሰባት” የተሰኘው የእነ ነዓምን ዘለቀ የሽብር ቡድን ልክ እንደ ወላጁ ወላዋይ ባህሪ ያለው ነው። ትናንት በሰላማዊ መንገድ እንቀሳቀሳለሁ ብሎ እዚህ ሀገር ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲነት ተደራጅቶ በሚንቀሳቀስበት ወቅት “አሰብን እናስመልሳለን” ይል እንዳልነበር፤ ዛሬ ግን በባንዳነት የሀገሩን መሬት (ባድመን) ለኤርትራ ይገባታል በማለት እየተከራከረ ነው። ይህም የሽብር ቡድኑ ከወላዋይነቱ ባሻገር፤ በምን ዓይነት የክህደት መንገድ እንደሚመራ የሚያሳይ ነው።

ርግጥ የአሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ክህደት ዛሬ የተጀመረ አይደለም። የነበረ ነው። የሽብር ቡድኑ ከውጭ ሃይሎች በሚሰጠው ዳረጎት ኑሮውን የሚገፋ ድርጅት ነው። በዚህም ኢትዮጵያን ለማተራመስ አጀንዳ ዶላር ለሚሰጠው ሁሉ አፋሽ አጎንባሽ ነው። ሀገራዊ ክብርና የህዝቦች ጥቅም የሚባል ነገር የማይታየው የእርጥባን ሰብሳቢዎች ስብስብ ነው። አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑን ጨምሮ ሁሉም አመራር ከሚሰበሰበው እርጥባን ቃርሚያ ለመለቃቀም የተሰለፉ ናቸው። በዚህም ምክንያት ሀገራቸውን በጠራራ ፀሐይ እያስማሙ የሚሸጡ የከሃዲዎች ስብስብ ሆነዋል። ለዚህም ይመስለኛል—ትናንት “አሰብን እናስመልሳለን” ባሉበት አንደበታቸው ዛሬ ደግሞ “ባድመ ተቆርሳ ለኤርትራ ይሰጣት” የሚል የክህደት ዲስኩርን የሚያወሩት።

አሸባሪው “ግንቦት ሰባት” በራሱ የማይንቀሳቀስ፣ እንዲያውም አንዳንዶች እንደሚሉት ሃላፊነቱ የተወሰነ የኤርትራ መንግስት የግል ኩባንያ መሆኑን እገነዘባለሁ። ድርጅቱ የሚመራውና የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ለማባላት “በእነ የኤርትራ መንግስት” የተቋቋመው “ኢሳት” ወይም እሳት ከኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አጀንዳ እየተቀበለ የሚሰራ ጣቢያ መሆኑም ግልፅ ነው። ከሚያወሩት ቋንቋ በስተቀር አሸባሪው ቡድንም ይሁን ዘርን ለይቶ የሚያጠቃው ኢሳት የተሰኘው የዳረጎት ጣቢያ

ይህን እውነታም ዝም ብዬ ያልኩት አይደለም። የአሸባሪው ቡድን መሪ የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ራሳቸው በአንድ ወቅት የኤርትራ መንግስት ለስድስት ወር ስራ ማስኬጃ 500 ሺህ ዶላር ሲሰጣቸው በድምፃቸው የተናገሩትን ስለማስታውስ ነው። እርሳቸው በድምፃቸው 200 ሺህ ዶላሩ ለኢሳት እንደተመደበ ሲናገሩ አዳምጫለው። ቀሪውንም ‘ለእገሌና ለእገሌ’ እያሉ ሰያከፋፍሉም ከተቀረፀው ድምፃቸው ላይ ሰምቻለሁ። ታዲያ ይህን መሰሉን ወረታ ለመመለስ ሲሉ እንኳንስ ባድመን ቀርቶ ራሳቸውንም ቆርጠው ቢሰጡ ቅር የሚላቸው አይመስለኝም። አቶ ነዓምን ለቢቢሲው ጋዜጠኛ የሰጡት ምላሽም ከዚህ እውነታ አንፃር የሚታይ ነው።  

አሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ሀገሩን የካደና ለባዕዳን የተሰለፈ በመሆኑ ለግብፅም ይሁን ለሌላ ቡድን በተላላኪነት የሚሰራ ነው። ቡድኑ በአንድ ወቅት በግብፅ አሌክሳንደሪያ ውስጥ ቢሮ ለመክፈት ሽር ጉድ ሲል እንደነበር ይታወቃል። እንደተሳካለትም ተነግሯል። ብርሃኑ ነጋም ይሁን ነዓምን ዘለቀ እንደ ውሃ ቀጂ ካይሮ ሲመላለሱ እንደነበር ማንም የሚያውቀው እውነታ ነው። ይህን ሀገር የሚያውቀውን እውነታ አቶ ነዓምን በአደባባይ ለምን እንደሚክዱ ለማንም ግልፅ አይደለም።

የግብፅ ጉዳይ ደግሞ ህዳሴውን ግድብ የተመለከተ ነው—አሁን የሚታየው መለሳለስ እንደተጠበቀ ሆኖ። ግብፆች ከዘመነ ሳዳት ጀምሮ ኢትዮጵያን በማዳከም ስራ ላይ መሰለፋቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ለዚህም ቀደም ሲል ኦነግን እስከመደገፍ አሁን ደግሞ ከሃዲዎችን በመመልመል ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖረን ሲያደርጉ ነበር።

በእኔ እምነት የግብፅ መንግስት ከአል-ሲሲ በዓለ-ሲመት ጀምሮ ወደ አዲስ ምዕራፍ የውይይት መድረክና አስተሳሰብ ያመራ የሚመስል መንገድን እየተከተለ ነው። ምንም እንኳን አንዳንዴ ያረጀውና ያፈጀው የቅኝ ግዛት ውል ብቅ ጥልም እያለ ቢያስቸግረውም። አብዛኛው የግብፅ  ህዝብ ግን ተባብሮ በማደግ የሚያምን ይመስለኛል። ያ ህዝብ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በየጊዜው ሲገልፅ አዳምጫለሁ።

ሆኖም አንድ ያገጠጠ ሃቅ ይታየኛል። ይኸውም ግብፆች ከተለያዩ የሙባረክ ዘመን ቅሪት ባለስልጣኖቻቸውና በመንግስታዊ ተቋማቶቻቸው አማካኝነት ተዘዋዋሪና ቀጥተኛ አስተያየት እንደምንሰማው ነገር፤ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን ለመጋፋት ብቻ ሳይሆን እንድንተራመስና ግድቡን እንድናቆም የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ የቀድሞዎቹ የግብፅ ገዥዎች አመለካከት ነው— ትናንትና ተሞክሮ ያልሰራና ዛሬም ቢሆን ሊሰራ የማይችል መወያየትንና መደማመጥን ወደጎን ያደረገ እሳቤ።

እናም የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ደፋ ቀና ማለታችን የሚያስኩርፋቸው ወገኖች መኖራቸው አይቀርም— ስጋታቸው ከባዶ የስጋት መንፈስ ብቻ የመነጨ ቢሆንም። አጋጣሚውን ተጠቅመው ከግብፅ መንግስት ተቋማት ጉያ ስር በመወሸቅ የግል ጥቅማቸውን ለማጋበስ ሽር ጉድ የሚሉ እንደ አሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ዓይነት ሀገርን ለመሸጥ የተሰለፉ ቡድኖች መኖራቸውን ማንም አይክድም።

እነ ነዓምን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚያራምዱት ‘ግድቡ መገንባት የለበትም’ የሚል አሳፋሪና የኢትዮጵያን ህዝቦች የማደግ መብት የሚቃወም ተግባር የዚህ እውነታ መገለጫ ነው። እናም የእነ ነዓምን ቡድን “ከሰጡን ከመቀበል ወደ ኋላ አንልም” ባይነት ውሸት ብቻ ሳይሆን፤ እርጥባን እየተሰጣቸው የህዝባቸውን የልማት ተስፋ ለማጨለም የተሰለፉ መሆናቸው ግልፅ ነው።

እነርሱ በከሃዲነት የተሰለፉለት ሀገርን የመካድ ተግባር ግን ፍሬ የሚያፈራ አይደለም። ምክንያቱም በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን የሚነፍግ አንዳች ህግም ይሁን ኃይል ከፀሃይ በታች ሊኖር ስለማይችል ነው።

እንደሚታወቀው የህዳሴው ግድብ ግንባታ መላው ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡን የደገፈው በሞራል ብቻ አይደለም። በጉልብቱም፣ በዕውቀቱም፣ በገንዘቡም በፀሎቱም ጭምር ነው። የህዳሴው ግድብ ግንባታ አንድነታችንን ይበልጥ ያጠበቀ ነው። መቻልን የቻልንበት፣ አንድ ከሆንንና ከተባበርን የማንወጣው ፈተና አለመኖሩን ያየንበትም ይሁን ያሳየንበት ጭምር ነው— ለወዳጆቻችንም፣ ለጠላቶቻችንም። ይህን እውነታ አቶ ነዓምንና ሀገርን በመሸጥ እርጥባን እየሰበሰቡ የሚተዳደሩት አመራሮቻቸው ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy