Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እነዚህ አመራሮች የኢህአዴግ ውጤት አይደሉምን?

0 1,119

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እነዚህ አመራሮች የኢህአዴግ ውጤት አይደሉምን?

 

አባ መላኩ

ኢህአዴግ በግለሰቦች ጥንካሬና ድክመት ላይ የተንጠለጠለ ፓርቲ እንዳይሆን ተደርጎ የተዋቀረ ጠንካራ  ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ ነው። ለዚህም ይመስለኛል ድርጅቱ የገጠሙትን በርካታ ውጣ ውረዶች ሁሉ በስኬት ማለፍ የቻለው። ኢህአዴግ በርካታ ጠንካራ አመራሮችና አባላት ያሉት ድርጅት በመሆኑ  ግለሰቦች ሲሄዱና ሲመጡ በድርጅቱ ህልውና ላይ የሚኖራቸው ተጽዕኖ እጅግም የሆነው። በርካታ አመራሮች በተለያየ ምክንያት ከድርጅቱ ሲሰናበቱ ፓርቲው የስኬት ጉዞውን ማስቀጠል የቻለው አንዱና ዋንኛው ምክንያት በፓርቲው የቡድን አሰራር የበላይነት የነገሰበት በመሆኑ ነው። አቶ መለስ  በአንድ ወቅት ስለኢህአዴግ እንዲህ ብለው ነበር። ለኢህአዴግ ጥንካሬ ትልቁ ነገር በድርጅቱ ውስጥ ያለው የቡድን አንድነትና የቡድን ስራ እንጂ ድርጅቱ በግለሰቦች ጥንካሬ ላይ የተንጠለጠለ አለመሆኑ ነው። ኢህአዴግ ሺህ ጠንካራ ስብዕና ያላቸውን አመራሮች ያፈራ፣ ነገም የሚያፈራ፣ የበርካታ በለራዕዮች   ፓርቲ ነው። የአንድ ፓርቲ ጥንካሬ ከሚለካባቸው ነገሮች መካከል ቀዳሚው የፓርቲው ህልውና በጥቂት ግለሰቦች ስብዕና ወይም ይሁንታ ላይ ያለመመስረቱ ነው። ኢህአዴግን በዚህ መለኪያ ስንመለከተው ድርጅቱ በቡድን አሰራር ላይ መሰረት ያደረገ ፓርቲ በመሆኑ በግለሰቦች መሄድና መምጣት ሳቢያ በድርጅቱ ላይ የሚከሰተው ተጽዕኖ እጅግም  ነው።

 

ኢህአዴግ በየጊዜው ለህዝብ የሚያስቡ አመራሮችን ያፈራ ፓርቲ ነው። እንደአቶ መለስ ዜናዊ  ያሉ ሁለመናቸውን ለህዝብ አሳልፈው የሰጡ በቅርቡ ደግሞ እንደክቡር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ  ያለ በአፍሪካ ያልተለመደ ውሳኔ የሚያሳልፉ አመራሮች ማፍራት ችሏል። ከቅርብ አመታት ወዲህ በአገራችን ለተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመፍትሄ አካል ለመሆን፤ የአገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ በአዲስ አመራር ሊጠበቅ ይችላል ብለው በማሰብ፣ ለአህጉራችን ምሳሌ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ያሸጋገሩት ክቡር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ  የዚህ ድርጅት ውጤት ናቸው። አቶ ኃይለማሪያም በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣን በቃኝ ከእኔ የተሻለ ግለሰብ ቦታውን ይታካ ያሉ ቅንና ለህዝብ አሳቢ የሆኑ ግለሰብ ናቸው። ኢህአዴግ እንዲህ ያሉ ህዝባዊ አመራሮችን ማፍራት የቻለ ፓርቲ ነው።

አቶ ሃይለማሪያም  ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩበት ወቅት እጅግ ፈታኝ እንደነበር  ይሰማኛል። በእርሳቸው የአመራር ጊዜ በአገራችንም ይሁን በኢህአዴግ ውስጥ  በርካታ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የታዩበት የውጭና የውስጥ ጫናዎች የበረቱበት ወቅት በመሆኑ  ኢትዮጵያን ለመምራት ፈታኝ ወቅት እንደነበር በርካቶች ሲገልጹ ይደመጣሉ። ለዚህ ሃሳቤ ድጋፍ የሚሆነኝ የኢህአዴግ እና የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከኢህአዴግ መርህ ባፈነገጠ መልኩ በነበሩ የተለያዩ ፍላጎቶች ቀደም ሲል የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ተገቢው እገዛ አልተደረገላቸውም፡፡  ተገቢው እገዛ ያልተደረገላቸው አቶ ሃይለማሪያም በአገሪቱ የነበሩትን የተለያዩ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። እኚህ ታላቅ ሰው ስልጣን ሳያጓጓቸው ስልጣናቸውን በፍቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል። ይህ ውሳኔ ለህዝብ አሳቢነትን በተግባር ያረጋገጠ ነው።

አዲሱ የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ውጤት ናቸው። በዚህች አጭር ጊዜ  ስለዶክተር አብይ አስተያየት መስጠት ተገቢ ባይሆንም ስለአንደበተ ርዕቱነታቸውና ከሁሉ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት  በተመለከተ መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ዶ/ር አብይ ወቅቱ የሚጠይቀውን ስብዕና የተላበሱ፣ አንደበተ ርትዑ አመራር ናቸው። እኚህ ግለሰብ ኢህአዴግ  የሰራቸው የድርጅቱ ውጤት ናቸው። በዚህም ኢህአዴግ ሊወደስ ይገባል።

ኢህአዴግ  የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚስተናገድበት የብዙሃን ድምጽ አሸናፊ የሚሆንበትን አሰራር የሚተገብር ፓርቲ ነው።  ድርጅቱ የቡድን አሰራር የነገሰበት ፓርቲ በመሆኑ ድርጅቱ በግለሰቦች መሄድና መምጣት የሚያጣው ወይም የሚያገኘው ነገር እጅግም  ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያው አቶ መለስ ናቸው። አቶ መለስ በኢህአዴግ እንዲሁም በኢትዮጵያ ከዚያም አልፎ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትልቅ ስብዕና ያላቸው ሰው ናቸው። ይሁንና ኢህአዴግ እሳቸውን አጥቶ እንኳን በስኬት መጓዙን ቀጥሏል። ኢህአዴግ በየዘርፉና በየወቅቱ ጠነካራ አመራሮችን  ማፍራት የቻለ ፓርቲ ነው። መለስም ይሁን ሃይለማሪያምም ወይም አብይ የኢህአዴግ ውጤቶች፤ የድርጅቱ ግርፎች ናቸው። ኢህአዴግ ወቅቱን የሚመጥኑ አመራሮችን ማፍራት የሚችል ፓርቲ መሆን በመቻሉ ሊኮራ ይገባዋል ባይ ነኝ።

 

ኢህአዴግ ግለሰቦች ስብዕና ላይ የተንጠለጠለ ፓርቲ አይደለም ስል  ግለሰቦች በድርጅቱ ስኬት ወይም ድክመት ላይ ምንም አስተዋጽዖ የላቸውም ማለቴ እንዳልሆነ  ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ድርጅቱ በጋራ አሰራር ያምናል፣ የብዙሃን ድምጽ የበላይነት የሚያገኝበት አሰራር ይተገብራል ማለቴ እንጂ ግለሰቦች ለድርጅቱ ስኬት ምንም ፋይዳ የላቸውም ማለት አይደለም። አንዳንዶች የአቶ መለስ ህልፈትን ተከትሎ ካለመለስ ኢህአዴግ እስትንፋስ የለውም፣ ኢህአዴግ  አበቃለት፣ ኢትዮጵያም አደጋ ላይ መውደቋ አይቀርም ወዘተ ቢሉም እውነታው ፍጹም ከዚህ የተለየ ሆኗል። ከላይ እንዳልኩት ኢህአዴግ በግለሰብ ላይ የተንጠለጠለ ድርጅት ቢሆን ኖሮ በርካታ የድርጅቱ መስራች የሆኑ አባላት በተለያየ ምክንያት ድርጅቱን ሲሰናበቱ ፓርቲው በተዳከመና በፈረሰ ነበር። ይሁንና ኢህአዴግ ማንም ሄደ ማንም መጣ እርሱ ግን በድል ላይ ሌላ ድሎችን ማስመዝገቡን ቀጥሎበታል።

 

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን የተፈጠረው ሁኔታ ዓለም በአንድ በኩል በአድናቆት በሌላ በኩል ደግሞ በስጋት እየተመለከተው ያለ አገራዊ ለውጥ ላይ ትገኛለች። አዲሱ አመራር ስኬቶቻችንን የሚያስቀጥልበትንና ተግዳሮቶችን የሚያስወግድበትን  አሰራር ሊተልም ይገባል። ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በስኬት ጎዳና እንድትጓዝ ኢህአዴግ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል። አገራችን በቀጠናው ጠንካራ መንግስት መስርቷል፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትታቸውን እንዲጎናጸፉ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ በፖለቲካው መድረክ ታግሏል፣ ህዝቦች መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ እንዲሁም  ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ኢህአዴግ የበኩሉን ጥረት አድርጓል። በተከታታይ ለ15 ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በአገራችን ድህነትን ከግማሽ በላይ መቀነስ ተችሏል፤ በስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች የአገራችን ተሰሚነት በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  እጅጉን አድጓል፤ አገራችን በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም በአፍሪካ ትኩረት የምትስብ አገር በመሆን ላይ ነች። ኢህአዴግ ለአገራችን ስኬቶች ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል፤ በማበርከትም ላይ ይገኛል። ኢህአዴግ በየጊዜው ችግሮቹን በመለየት ለማስተካከል የሚጥር ተማሪ ፓርቲ ነው።

 

በአገራችን ታሪክ ኢህአዴግ በመልካም ስነ-ምግሩ በጥሩ ዓረዓያነቱ በቀዳሚነት የሚፈረጅ ብቸኛ ፓርት ነው ብል አብዛኛዎቻችንን የሚያስማማ እውነታ ነው፡፡ የድርጅቱ የውስጥ አሰራር የግለሰቦች ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንሸራሸርበት ሃሳብ በነፃነት የሚፋጭበት፤ ሁሌም የብዙሃኑ ድምጽ የበላይነት የነገሰበት ፓርቲ  ነው፡፡ ይህ አሰራሩም ብዙሃኑን ያማከለ፣ ከአንባገነናዊነት የፀዳና በግልፅነት ላይ የተመሰረተ አሰራርን የሚተገብር በመሆኑ በርካታዎችን ወደፓርቲው አባልነት እንዲሳቡ ያደረገ ነገር ይመስለኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድርጅቱ ውስጥ የሚስተዋሉት ነገሮች ድርጅቱን ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ከፉኛ ፈትኗታል። ኢህአዴግ ሁኔታዎችን በአግባብ ፈትሾ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል። አዲስ የድርጅትና  የአገር አመራር መርጧል። እኚህ ግለሰብ በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አገኝኘተዋል።

በአጭር ጊዜ  የበርካቶችን ቀልብ መግዛት የቻሉት ዶ/ር አብይ  ኢህአዴግ ያበቃው ኢህአዴግ ኮትኩቶ ያሳደገው ወጣት አመራር ነው።  ዶ/ር አብይ ወቅቱ የሚጠይቀውን ስብዕና የተላበሱ፣ አንደበተ ርትዑ አመራር ናቸው። በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ላይ  “ማንነታችንን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳትነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደ እና የተዋሀደ ነው፤ አማራው በካራ-ማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራ-ማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉል፣ ወላይታ፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሀዲያው እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል። …!” ሲሉ  የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት የገለጹበት አንቀጽ የበርካታ ዜጎችን ቀልብ የገዛ ንግግር ነው። አዲሱ ጠቅላያችን ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉት የድርጅቱንም ሆነ የህዝቡን ድጋፍ ሲያገኙ ነውና ማንኛውም ኢትዮጵያዊም ይሁን ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአገር ውስጥ የሚኖር ይሁን በውጭ ድጋፉን ሊያደርግላቸው ይገባል።

 

 

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy