Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እነ አቶ መላኩ ፈንታ በሁለት የክስ መዝገቦች ጥፋተኛና ነፃ ተባሉ

0 654

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰው ከአራት ዓመታት በላይ ሲከራከሩ የከረሙት እነ አቶ መላኩ ፈንታ፣ ዓቃቤ ሕግ ክስ ካቀረበባቸው ሦስት መዝገቦች ውስጥ በሁለቱ መዝገቦች በተወሰኑ ክሶች ጥፋተኛ ሲባሉ በተወሰኑ ክሶች ደግሞ በነፃ ተሰናበቱ፡፡

ክስ ከተመሠረተባቸው ከ2006 ዓ.ም. መጀመርያ ወራት ጀምሮ ክሳቸውን ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነትና በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ የሰጠው፣ ዓርብ መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በፊትና በኃላ ነው፡፡

በመዝገብ ቁጥር 141354 ውስጥ የተካተቱት አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ማሞ አብዱ፣ አቶ አሞኘ ታገለና አቶ ጥሩነህ በርታ ናቸው፡፡

አቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት፣ ከታክስና ከገቢ ጋር በሚመለከት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ማስተናገድ የሚያስችሉ አዋጆች እያሉ፣ ከግብር ከፋዮች ጋር መደራደር የሚያስችል ሕገወጥ ኮሚቴ አቋቁመዋል የሚል ክስ እንደቀረበባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ኮሚቴው የግብር ከፋዮች ጉዳይ ቀርቦ በመጣራት ላይ እያለ የይግባኝ አቀራረብ ሥነ ሥርዓትን ሳይከተል የተለያዩ ድርጅቶች ጉዳያቸው በአቋራጭ እንዲታይላቸው በማድረግ፣ መንግሥት ከግብር ከፋዩ ማግኘት የሚገባውን እንዳያገኝ ማድረጋቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ ባቀረቡት የመከላከያ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ሊያስተባብሉ ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ናቸው ሲል ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ሁለቱም ተከሳሾች በሌላ ክስ ያማቶ ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት መክፈል የሚገባውን ግብር ባለመክፈሉ ከተወሰነበት ግብር 50 በመቶ አስይዞ መከራከር ቢኖርበትም፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና ዝቅ አድርገው በመገመት የመንግሥት ሥራን በማያመች ሁኔታ መምራታቸውን ማስተባበል ባለመቻል ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ አቶ ገብረ ዋህድ ጥፋተኛ የተባሉት በተመሳሳይ የክስ መዝገብ በአምስተኛ ክስ ሲሆን፣ ኬጂኤች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ መክፈል የነበረበትን ግብር፣ በኦዲት ተረጋግጦበትና ይግባኝ ቢልም ፀንቶበት እያለ፣ ‹‹እንዲሻሻል›› የሚል ሕገወጥ ትዕዛዝ በመስጠት፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኃን መርተዋል ተብሎ፣ የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ነው፡፡

አቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድ በነፃ የተሰናበቱበት ክስ ደግሞ፣ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ከቀረበባቸው ሰባተኛ ክስ ነው፡፡ የተከሰሱበት ክስ ኦቨርኒጋስ ቴክኖሎጂ ሊሚትድ መክፈል የነበረበትን 34.3 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ከተወሰነ በኋላ ጠቋሚ ላልሆኑ ሰዎች ጠቋሚ እንደሆኑ በማስመሰል ሰነድ አዘጋጅተው እንዲመዘገቡ አድርገዋል የሚል ነበር፡፡ ክሱን በበቂ ሁኔታ በመከላከላቸው በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

አቶ ገብረ ዋህድ ለብቻቸው ከተከሰሱበት ግብር ያልከፈሉ ድርጅቶችን ሕገወጥ የኦዲት ሪፖርት በመሥራት እንዲከፍሉ አስደርገዋል ተብሎ ከቀረበባቸው ክስ ነው፡፡ በብቃት በመከላከላቸውም በነፃ እንዲሰናበቱ ሲል ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

አቶ መላኩ 3.2 ሚሊዮን ብር ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርተዋል የሚል በዘጠነኛ ክስ፣ 1.4 ሚሊዮን ብር ቤት ለመገንቢያ ብለው ተበድረው 1,050,286 ብር ለባንኩ መክፈላቸው በአሥረኛ ክስ የተጠቀሰባቸው ሲሆን፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው አቅርበዋል የሚል ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን እሳቸው በሥራ ላይ የቆዩበትን ዘመን፣ ይከፈላቸው የነበረን ደመወዝ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አበል፣ እንዲሁም የቦርድ አባል በመሆናቸው ይከፈላቸው የነበረን ክፍያ በማሥላት፣ እንደ ወንጀል የተቆጠረውና ለክስ ያበቃቸው ገንዘብ ተገቢ ባለመሆኑ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡

ሌላው ከተከሰሱበት የሙስና ክስ በነፃ የተሰናበቱትና ዓርብ መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ የተሰጠላቸው አቶ ጥሩነህ በርታ ሲሆኑ፣ የባለሥልጣኑ የመረጃ ቡድን መሪ ነበሩ፡፡

አቶ አሞኘ ታገለ የባለሥልጣኑ የአዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ፣ በአዳማ ከተማ የሚገኘው ይልማ ኦዳ ሥጋ ቤት ከነሐሴ 1996 ዓ.ም. እስከ ጥር 1998 ዓ.ም. ድረስ ያልከፈለውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር እንዲከፍል ሲወሰንበት፣ 50 በመቶ ከፍሎ ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ አቤቱታ ማቅረብ ሲገባው ክፍያውን ከ922,368 ብር ወደ 262,587 ብር ዝቅ አድርገዋል የሚለውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ ነገር ግን ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) የሚገኘው ቶሚ ኢንተርናሽናል ባርና ሬስቶራንት መክፈል የነበረበትን 805,122 ብር የኦዲት ሪፖርት ግኝት አስነስተዋል መባላቸውን በብቃት በማስተባበላቸው በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

አቶ በላቸው በየነና አቶ ማሞ አብዲ አዳማ የሚገኘውን አሊፍ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ያልከፈለውን ከ1.7 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ወደ 83,387 ብር ዝቅ አድርገዋል ተብሎ የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው፣ ጥፋተኛ እንዳላቸው ፍርዱ ቤቱ አስታውቋል፡፡ አቶ ማሞ አብዲ ሞኤንኮ ኩባንያ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ባስገባቸው ዕቃዎች ላይ የከፈለውን ቀረጥና ታክስ ሕጋዊነት ለማረጋገጥ የድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ከተሠራ በኋላ፣ ኩባንያው ታማኝ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ነው በማለት ኦዲቱ እንዲቋረጥ አድርገዋል የሚለውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከቀትር በኋላ በሰጠው ፍርድ የተመለከተው በመዝገብ ቁጥር 141356 ክስ የቀረበባቸውን አቶ መላኩ፣ አቶ ገብረ ዋህድ፣ አቶ አምኘ፣ አቶ ተመስገን ጉላላ፣ አቶ ያለው ቡላ፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር (ነፃ ትሬዲንግና ባሰፋ ትሬዲንግ)፣ አቶ ከተማ ከበደ (ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር)፣ አቶ ጌቱ ገለቴ (ጌት አስ ኢንተርናሽናል) እና አቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬ (ኮሜት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር) ናቸው፡፡

ክሱ በዋናነት በተለይ ከላይ የተጠቀሱት የአቶ ነጋ፣ የአቶ ከተማ፣ የአቶ ገብረ ሥላሴና የአቶ ጌቱ ድርጅቶች በተሽከርካሪዎቻቸው ከውጭ የሚያስገቡት ጥሬ ዕቃ በጂቡቲ በኩል ጋላፊ ላይ በማሽን ተፈትሾ ማለፍ ሲገባው፣ ከአቶ መላኩና ከአቶ ገብረ ዋህድ ጋር ባላቸው የጥቅም ትስስር የተመረጡና የማይፈተሹ እንደሆኑና ‹‹ይለፍ›› የሚል ምልክት በመስጠት፣ እስከ መዳረሻ ድረስ ሳይፈተሹ እንዲያልፉ አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ የሰነድና የሰዎች ምስክሮች አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ተከሳሾቹ በተሰጠው ብይን እንዲከላከሉ ሲባሉ በብቃት የተከላከሉ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ባይጠይቅም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ባለሥልጣኑ በእነዚህ ድርጅቶች በሕዝብና በመንግሥት ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ እንዲላክለት ትዕዛዝ ሰጥቶ ምላሽ አግኝቷል፡፡ ባለሥልጣኑ በላከው ምላሽ ድርጅቶቹ በአግባቡ ተፈትሸው ያለፉ መሆኑን፣ በመዳረሻ ፍተሻ ጣቢያዎችም ተገቢ የሆነውን የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት የፈጸሙና በሕዝብም ሆነ በመንግሥት ላይ ያደረሱት ጉዳት እንደሌለ ገልጾ፣ ምላሽ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም አቶ ነጋ፣ አቶ ከተማና አቶ ገብረ ሥላሴ በብቃት በመከላከላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ አቶ ጌቱ ገለቴ ግን ክሱ የተካሄደው በሌሉበት መሆኑን ጠቁሞ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡

አቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድም ሥራን በማያመች አኳኃን መምራት በማለት ጥፋተኛ ብለዋቸዋል፡፡ አቶ ተመስገን ጉላላና አቶ ያለው ቡላ በተወሰኑ ክሶች ነፃ ቢሆኑም በተወሰኑ ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ አቶ አሞኘ ታገለም ነፃ ተብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ በሁለቱም የክስ መዝገብ ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾች በ15 ቀናት ውስጥ የቅጣት ማቅለያቸውን፣ እንዲሁም ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በአሥር ቀናት ውስጥ የቅጣት ማክበጃ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ለሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ቅጣት ለመንገር ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

FacebookTwitterLinkedInShare

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy