Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከተልዕኮ ባሻገር

0 258

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከተልዕኮ ባሻገር

                                                         ሶሪ ገመዳ

ፅንፈኞች የፀጥታ ሃይሎችን ያልተገባ ምስል በመስጠት እያካሄዱ ያሉት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የህይወትን መስዕዋትነት በመክፈል ጭምር ሰላምን በማረጋገጥ የሚገኙ ሃይሎችን የሚወክል አይደለም። የፀጥታ ሃይሎቻችን ሕዝባዊ ናቸው። በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር እያደረገ ካለው ርብርብ ባሻገር፤ ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራት፣ ከህዝብ ጋር በመወያዬት፣ በልማት ስራዎች በመሳተፍ እና ለየአካባቢው ህብረተሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠትና በሌሎች ጉዳዩች ህዝባዊ ወገንተኛ ተግባራትን እያከናወኑ ናቸው። ከዚህ አኳያ ህዝባዊውን መከላከያ ሰራዊታችንን በምሳሌነት ማንሳት እንችላለን።

እንደሚታወቀው ሁሉ የመከላከያ ሰራዊታችን የልማት ገጽታ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ካለው አነስተኛ ገቢ በፍጹም ህዝባዊና ሀገራዊ ፍቅር የሚገልጽ ቀጥተኛ የልማት ተሳትፎ ማድረግ ነው፡፡ ሰራዊቱ በዚህ በኩል የነበረውን ድርሻ በቀላሉ መግለጽ ይከብዳል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ የትልቋ ኢትዮጵያ እውነተኛ ተምሳሌት ብቻ አይደለም። መሃንዲስ፣ መምህር፣ አርሶና አርብቶ አደርም ጭምር ነው፡፡ መንገድ ገንብቶ ህዝቦችን አገናኝቷል፡፡

ግድብ ሰርቶ አርብቶ አደሩ ወደ አርሶና ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲቀየር አስችሏል፡፡ ትምህርት ቤት ሰርቶም የመማር ዕድሉ ያልነበራቸውን ከዕውቀት ጋር አገናኝቷል፡፡ የጤና ተቋማት ላይ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን አፍስሶ ለዕልፎች የመኖር ዋስትና ሰጥቷል፡፡ የእናቶችንና ህፃናትን ሞትን በመቀነስ ረገድም በተግባር ተሳትፏል፡፡

በምህንድስናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቃት ያላቸው ሙያተኞቹን በማሳተፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር አብዮት ለኩሷል፡፡ ካለው እያካፈለ፣ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ጋር እየዋለ ድርብ ድርብርብ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ ሌላ ሌላም ተግብሮችን ፈፅሟል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሀገራችን የቀየሰችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ዕውን በማድረግ ረገድ ጠላትን ተዋግቶ ከማሸነፍ ያልተናነሰ ድል አስመዝግቧል፡፡ የተራቆተውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ ነበረበት ለመመለስና የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት ባደረገው ጥረት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የቻለ ኃይል ነው፡፡

የሰራዊቱ አባላት ለሀገራዊ ግዳጅ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክለዋል፡፡ ከሠራዊታችን ድርሻ ላይ ተቀንሶ በሚጠጡት ውኃ፣ በሚደረግላቸው ከሀገር ፍቅር የመነጨ እንክብካቤ ፀድቀዋል፡፡

ምንም እንኳን ሰራዊቱ ለህዝብ ስለ ህዝብ ያከናወናቸውን የልማት ሥራዎች በሙሉ ለማንሳት መሞከርም የማይቻል ቢሆንም፤ ከብዙ በጥቂቱ ማንሳቱ ግን ተገቢ መስሎ ታይቶኛል። እናም ያገኘኋቸውን መረጃዎች ተንተርሼ አለፍ አለፍ እያልኩ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡

በቅድሚያ ከምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ልነሳ። እዚህ የሀገራችን ክፍል ውስጥ የበረሃዎቹን አናብስት እናገኛቸዋለን፡፡ ይህ የሀገራችን ክፍል ፀረ ሠላም ኃይሎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱበት፣ ህገ-ወጥ ንግድን ጨምሮ ህገ-ወጥነት የተስፋፋበት አካባቢ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህ ጉዳይ ታሪክ ሆኗል።

በሠራዊቱ ጠንካራ ክንድ ሽብርተኞች ከስመዋል፡፡ የህግ የበላይነትንም ማስከበር ተችሏል። ሻዕቢያ የሚያሰማራቸውም አሸባሪዎችም ቢሆኑ ድንበር ሳይሻገሩ በህዝቡ ድጋፍ በቁጥጥር ስር ይውላሉ። ይህም በአካባቢው አስተማማኝ ሰላምን በማስገኘት ለኢንቨስትመንት ስራዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በዚህ ሁኔታ የሰላሙን ፍሬ ያጣጣመው የዚያ አካባቢ ህዝብ አንቅሮ እንደተፋቸው የተገነዘቡት ፀረ-ሠላም ኃይሎችና አሸባሪዎች ከፍተኛ አመራሮች ጭምር ከጥፋት ይልቅ ለህዝቡ በጎ ተግባር መሥራትን መርጠው በልማቱ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆንም ችለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ እነዚህ ወገኖቻችን የህገ-መንግሥቱንና ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ፋይዳና ለዚች ሀገር ያለውን ፍፁም ጠቃሚነት መመስከር ጀምረዋል፡፡

በምዕራቡ የሀገራችን ክፍል የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረውን ፀረ-ሠላም ኃይል ታሪክ ከማድረግ ባሻገር፤ ለህዝቡ በሚያደርጉት ድጋፍ ህዝባዊ ፍቅርን መጎናፀፍ የቻሉ ናቸው። ከሚያከናውኗቸው ልማታዊ ሥራዎች ባሻገር፤ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ጭምር ማህበራዊ ተሳትፎም ያደርጋሉ። በአካባቢው ሰላምን በማስፈን ህገ-መንግስቱን ተመርኩዘው ህዝባዊ ተልዕኳቸውን ከህዝቡ ጋር በመሆን በብቃት እየተወጡ ነው።

በሰሜኑ ክፍል የሚገኘው የሰራዊቱ ክፍልም ልክ እንደ ሌሎቹ የሰራዊት ክፍሎች ተመሳሰይ ተግባራትን በመፈፀም ይታወቃሉ። እንደሚታወቀው ሻዕቢያ ወረራ በፈጸመብን ወቅት የዛላንበሳን ከተማ ወደ ፍርስራሽነት ለውጧት ነበር፡፡

ሆኖም እብሪቱን አስተንፍሶ በኃይል የያዘውን መሬታችንን ሳይወድ በግድ ለቆ ሉዓላዊነታችንን እንዲከበር ካደረጉት የሠራዊታችን ክፍሎች ውስጥ አንዱ በዚህ አካባቢ የሚገኘው ሰራዊት ነው። ከዚያም በኋላ ይህ የሰራዊት ክፍል በከተማዋ መልሶ ግንባታ ያደረገውን ከፍተኛ ድጋፍ ታሪክ መቼም የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ ዛሬ ከተማዋ ለምትገኝበት ደማቅ ገፅታ በአካባቢው የሚገኘው ሰራዊት ህዝባዊ ወገነተኝነቱ አሻራውን አሳርፏል፡፡ ሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆንም ጭምር።

በትግራይ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው የሰራዊቱ ክፍልም ቀደም ሲል እንደ ጠቀስኳቸው የሰራዊቱ ክፍሎች ተነግሮ የማያልቅ የህዝባዊ ወገንተኝነት ማሳያዎች አሉት፡፡ በዚያ አካባቢ የሚገኘው ሰራዊት ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን በማቀናጀት ጊዜ የማያቆረፍደው የልማት ተግባራትን ከውኗል፤ እየከወነም ነው።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ‘ተልዕኮዬን አሳክቻለሁ፣ የተሰጠኝን ግዳጅ በብቃት ተወጥቻለሁ’ ብሎ የሚቀመጥ ሃይል አይደለም። ባለበት አካባቢ ሁሉ ካለው ቀንሶ ያካፍላል፣ የታረዙትን ያለብሳል፣ የተራቡትን ያበላል፣ የታመሙትን ያክማል፣ ቤት ንብረት የወደመባቸውን በመልሶ ግንባታ ያግዛል…ወዘተርፈ።

ታዲያ ሠራዊቱ እነዚህን ሁሉ ተግባራት የሚከውነው ከምንም ተነስቶ አለመሆኑን ግንዛቤ መያዝ የሚገባ ይመስለኛል። መከላከያ ሰራዊቱ እነዚህን ህዝባዊ ክንዋኔዎች ዕውን የሚያደርገው ከተልዕኮው ባሻገር ባለው ከፍተኛ ህዝባዊ ወገንተኝነት ስሜት ነው። የሰራዊታችን ህዝባዊ ወገንተኝነት መቼም የሚቀየር አይደለም።

ከራሱ በፊት ለህዝቡና ለሀገሩ ሲል ህይወቱን ለመስጠት የተሰለፈ ኃይል በምንም መልኩ ቢሆን የተነሳበትን ዓላማ ሊስት አይችልም። ሰራዊቱ እንደ ወታደር ህዝብና ሀገር የምትጠብቅበትን ማናቸውንም ተግባር መወጣት እንደሚችል በተለያዩ ወቅቶች ማስመስከሩ የዚህ አባባሌ መገለጫ ነው። በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባሮች ከዚሁ ህዝባዊነቱ የሚቀዱ ናቸው። ሌሎች የፀጥታ ሃይሎችም ተመሳሳይ ተግባራትን የሚፈፅሙት ከዚሁ ሰራዊት ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ስላላቸው ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy