Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአያያዝ ይቀደዳል

0 288

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአያያዝ ይቀደዳል

ለሚ ዋቄ

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰላሟ ስጋት ላይ መውደቁ ይታወቃል። የሰላም ስጋት የፈጠረው በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለይ ኦሮሚያ የየተቀሰቀሰው ተቃውሞ ነው። ይህ ተቃውሞ በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎችም አጋጥሟል። የሰላም ስጋት ምንጭ የሆነው ተቃውሞ የተለያየ ቀስቃሽ ምክንያት ቢኖረውም መሰረታዊው ምክንያት ግን ህዝብ በመንግስት አፈጻጸም ላይ ያለው ቅሬታ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ይህ የሰላም ችግር እያደረ ከመቃለል ይልቅ እየባሰና መልኩን እየቀያየረ ቀጥሎ ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት መክንያት ሆኗል። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል የዜጎችን ኑሩና የመኖር ዋስት ስጋት ውስጥ ከቷል። በመቶ ሚሊየን ለሚገመት የህዝብና የግለሰቦች ሃብት ውድመት ምክንያት ሆኗል። ይህን የሰላም መደፍረስ በተለመደው ህግን የማስከበር ስርአት መቆጣጠር ስላልተቻለ ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ታውጇል። አሁን ሃገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች።

በሃገሪቱ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በአጠቃላይ የሃገሪቱን ዘላቂ ህለውና ወደአደጋ እየገፋ ነው። ይህን ሁሉንም ዜጎች፣ ከዜጎችም አልፎ የሃገሪቱን ወዳጆችና አጋሮች በሙሉ ያሳሰበ የሰላም ስጋት የማቃለል ጉዳይ የሃገር ህልውናን የማስቀጠል ጉዳይ ሆኗል። ይህን መነሻ በማደረግ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከፌደራልና  የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ የሰላም ኮንፈረንስ አካሂደዋል። በዚህ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የገዢው ፓርቲና የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ኡጋዞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች . . . ተሳትፈዋል። በሰላም ኮንፈረንሱ ላይ የሃገሪቱን የሰላም ችግር መንስኤዎችና መፍትሄዎችን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂደዋል። የሃገሪቱን ሰላም ወደነበረበት ሊመልሱ የሚችሉ የተለያዩ ሃሳቦች ቀርበዋል።

በዚህ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የቀረቡትን ሃሳቦች በሙሉ በአንድ የጋዜጣ ጽሁፍ ማቅረብ አይቻልም። ይሁን እንጂ የሰላም መደፍረስ ምንጭና መፍትሄዎችን በተመለከተ የቀረቡትን ሃሳቦች የሚወክሉ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ወድጃለሁ።

የሰላም መደፍረስ ችግር ምንጭ በሚል በርካቶች የተስማሙበት የመንግስት የአፈጻጸም ችግርን ነው። ይህ ችግር ቀደም ሲልም በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጭምር የታመነበት መሆኑ ይታወቃል። በመንግስት በኩል የነበረው አሁንም ተቀርፏል ለማለት የማያስደፍረው መሰረታዊው ችግር፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ወይም ባለስልጣናት የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ማጣት ነው። ከፌደራል እስከክልል፣ ከክልል እስከቀበሌ የተሾሙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ስልጣናቸውን ህዝብን ለማገልገል ሳይሆን የግል ኑሯቸው ማደላደያ አድርገው የመውሰድ ዝንባሌና ተግባር በስፋት ታይቷል።

የተወሰኑ የመንግስት ባለስልጣኖች ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የተሟሉላቸው ጥቅማጥቅሞች ውስጥ ተሟሙቀው መኖርን የመረጡበት ሁኔታ በተጨባጭ ታይቷል። ይህ ሁኔታ ባለስልጣናቱ ለህዝብ ፋይዳ ያለቸውን ውሳኔዎች በድፍረት በማሳለፍና አፈጻጸማቸውን በመከታተል መተጋገል ውስጥ ከመግባት፣  ከአጥፊዎችም ጋር ጭምር ተስማምተው መኖርን የመረጡበትን ሁኔታ አስከትሏል። እነዚህ ባለስልጣናት ምናልባት በሙስና የሚያስጠይቅ ተግባር ውስጥ አልተሳተፉም ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አጥፊዎችን ከመጋፈጥ ይልቅ፣ ስልጣን ውስጥ ያለውን የሞቀ ኑሮ ላጣ እችላለሁ በሚል ስጋት ዝምታን የመረጡበት ሁኔታ ተስተውሏል። ለህዝብ የሚጠቅም ውሳኔ ከማሳለፍም እጃቸውን የሰበሰቡበት ሁኔታ ነበር። ውሳኔ ማሳለፍ ያልተጠበቀ ውጤትም ሊያስከትል ስለሚችል ይህን ተከትሎ ሊያጋጥም የሚችል ተጠያቂነትን ለማስቀረት ነው እጃቸውን የሚሰበስቡት። እነዚህ ባለስልጣናት ስልጣናቸውን የህዝብን መብትና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ውሳኔ ከማሳለፍ በመሸሻቸውና አጥፊዎችን ባለመጋፈጣቸው ህዝብ የሰጣቸውን ስልጣን ህዝብን ለማገልገል አላዋሉም። ይህ አንዱ የመንግስት የህዝብ አገልጋይነት መጥፋት መገለጫ ነበር።

ሌላኛው የመንግስት የህዝብ አገልጋይነት መጓደል መገለጫ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ህዝብን ለማገልገል በተሰጣቸው ስልጣን ከባለሃብት ነን ተብዬዎችና ደላሎች ጋር የጥቅም መተሳሳር ፈጥረው ተገቢ ያልሆነ የግል ጥቅም ለማጋበስ ተግተዋል። ይህ የኪራይ ሰብሳቢነት ትስስር የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መሆን በሚገባው ልክ እንዳይራመድ እንቅፋት ሆኗል። ህዝብ ተስፋ የጣለባቸው በርካታ የመሰረተ ልማትና የማሀበራዊ ልማት ግንባታዎች እሳት ላይ የወደቀ ቂቤ ሆነዋል። ይህ የኪራይ ሰብሳቢነት ትስስር ጥቂት ተለጣፊ ባለሃብቶችና ደላሎች በድንገት እንዲበለጽጉ ሲያደርግ፣ በርካቶች ደግሞ የሚገባቸውን እንዳያገኙና እንዲደኸዩ ምክንያት ሆኗል። የልማታዊ ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ተነሳሽነት አዳክሟል። የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተሳታፊነት በመገደብ ስራ አጥነት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ወጣቶች ከሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ገድቧል። በአጠቃላይ ሁኔታው በሃገሪቱ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሚዛን እንዲዛባ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የታየው የህዝብ አገልጋይነት ማጣት የፈጠረው ኪራይ ሰብሳቢነት ተጽእኖ በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሚዛን መዛባት ብቻ የተገለጸ አልነበረም። ለመልካም አስተዳደር መጓደልም ምክንያት ሆኗል። የፍትህ ስርአቱንም አዛብቷል። የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ስልጣናቸው ላይ ተሟሙቆው ለመቆየትና የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የገቡበት ሁኔታ የሃገሪቱን ዴሞክራሲም አቀጭጮታል። በአጠቃላይ የመንግስት የህዝብ አገልጋይ አለመሆን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መጓደል፣ የዴሞክራሲ መቀጨጭ ምክንያት ሆኗል።

በዚህ ሁኔታ ከመንግስት ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት ያጣው ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ በማጣቱ አኩርፏል። በማኩረፍ አልተገደበም፤ ተቃውሞውን አደባባይ ወጥቶ አሰምቷል። በየደረጃው በመንግስት የስራ ሃላፊነት ባሉ ባለስልጣናት የተፈጸመው በደል ህዝብ ላይ ያሰደረው ቅሬታ የቀሰቀሰው ቁጣ፣ ተቃውሞዎች ከሰላማዊነት ይልቅ የሃይል ተቃውሞ ባህሪ እንዲኖራቸው ያደረገበትም ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ ሁከት በማጋጋል ሃገሪቱን ለማተራመስ ለሚፈልጉ ቡድኖች መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል። ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ማስወገድ የሚፈልጉ ቡድኖችና ያሀገሪቱ ጠላቶች በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመው እጃቸውን ሰደደው ሁኔታው አደገኛ መልክ እንዲይዝ አድርገዋል። ይህ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የሃገሪቱን ዘላቂ ህልውና አደጋ ላይ የጣለው የሰላም ስጋትም ከዚህ የተፈጠረ ነው።

የሀገሪቱ የሰላም ስጋት መንስኤ ላይ ከላይ በተብራራው እውነታ ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው የሰላም ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የመፍትሄ ሃሳቦችንም አቅርበዋል። በዚህም ጉዳይ ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን አነሳለሁ። በኮንፈረንሱ ላይ እንደመፍትሄ ከተቀመጡት ሃሳቦች መሃከል ዋነኞቹ ዴሞክራሲን ማስፈንና ድህነትን ማቃለል የሚሉት አንኳር አንኳሮቹ ናቸው።

የዴሞክራሲ መስፈን መንግስት የስልጣን ምንጭ ለሆነው ህዝብ ተጠያቂነት እንዲኖረው ያደርጋል። የመንግስት አሰራር ግልጽነት እንዲኖረውም ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ ህዝብ እና/ወይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅሬታቸውንና ፍላጎታቸውን መግለጽ የሚችሉበት እድል ይፈጥራል።

በዚህ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ውስጥ  መንግስት የህዝብ አገልጋይነትን እንደዋዛ ችላ ሊል አይችልም። ችላ ብሎ ሲገኝም ሁኔታው ከህዝብ ተሰውሮ አይኖርም። በመንግስት ላይ ያለውን ችግር የተገነዘበ ህዝብ በዚህ ላይ ያለውን ቅሬታ በይፋ አሳውቆ ተጠያቂ እንዲሆን ያደርጋል። ብሶቱንና ፍላጎቱን ያሰማል። ይህ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ህዝብ መንግስትን እንዲቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ ቅሬታዎች የሚስተናገዱበት መድረክ ስለሚፈጥር ችግሮች ታፍነው ሳይታሰብ በአውዳሚ የሃይል ተቃውሞነት የሚወጡበትን እድል ያስቀራል። ይህ ደግሞ ሰላምን ያረጋግጣል። እናም የሃገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ዴሞክራሲን ማስፋት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው።

ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንደመፍትሄ የቀረበው ሌላው ጉዳይ ድህነትን ማቃላል ወይም ከድህነት መውጣት ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በፊት በእርስ በርስ ጦርነት የደቀቀች፣ በዓለማችን የመጨረሻዋን ደሃና ከእድገት ጎዳና ውጭ የሆነች ሃገር ነበር የተረከበው። ይህን ለዘመናት በሃገሪቱ የኖረና ከጊዜ ወደጊዜ አየከፋ የመጣ ድህነት ለማቃለል የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ግብርና ላይ የተመሰረተ የኢንደስትሪ ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ በማደረግ በተለይ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። በማህበራዊ ልማትም በተለይ በትምህርትና በጤና አገልግሎት ከፍተኛ እድገት ታይቷል። ይህ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ማህበራዊ ልማት በሚሊየን የሚቆጠሩ ዘጎችን ተጠቃሚ አድርጓል። ከምንም ተነስተው ሚሊየነር ባለሃብት ለመሆን የበቁ አርሶ አደሮችንና የአነስተኛና ጥቃቅን የልማት ተቋማት አንቀሳቃሾች ተፈጥረዋል። ለሚሊየኖች የስራ እድል ተፈጥሯል። በአጠቃላይ በሃገሪቱ የነበረውን ድህነት በግማሽ መቀነሰ አስችሏል።

ይሁን እንጂ በሃገሪቱ የነበረው ድህነት ስር የሰደደ በመሆኑና ቀደም ሲል እንደተገለጸው በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት እድገቱ በሚፈለገው እርምጃ እንዳይጓዝ መሰናክሎች የገጠሙት መሆኑ፣ እንዲሁም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛባት ድህነትን የማቃለሉ ተግባር መሆን የሚገባውንና የሚፈለገውን ያህል እንዳይሆን አድርጓል። በርካታ ዜጎች ከድህነት የመውጣታቸውን ያህል፣ የዛኑ ያህል ተስፋ አስቆራጭ ድህነት ውስጥ ታጥረው ለመኖር የተገደዱም አሉ። በከተሞች የስራ አጥነትን ችግር ለማቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደው ውጤት ማምጣት ቢቻልም፣ የስራ አጦች ቁጥር በተለይ የወጣት ስራ አጦች ቁጥር ከመቃለል ይልቅ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የሄደበት ሁኔታ ታይቷል። ጥቂቶች ከአርሶ አደሩ ለልማት በሚል በተወሰደ መሬት በህጋዊነትም በህገወጥ የጥቅም ትስስርም ሲበለጽጉ፣ በርካታ አርሶ አደሮች ከነልጆቻቸው ከነበሩበትም የባሰ አስከፊ ድህነት ላይ የወደቁበት ሁኔታ ታይቷል።

ታዲያ ድህነት ውስጥ ያለ ሰው ይህ የኑሮ ሁኔታው እንዲለወጥ ይፈልጋል። አሁን ከሚኖርበት ሁኔታ ይልቅ የማያውቀው ማንኛውም መጪ ሁኔታ ውስጥ ተስፋ ይኖራል ብሎ ይገምታል። ለውጥ አያሰጋውም፤ ምንም ስለሌለው ለውጡ ምንም ይሁን የሚያሳጣው ነገር የለም። በመሆኑም ለውጡ ወዴትም ያድርስ የት ለለውጥ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ይደፍራል። በመሆኑም ድህነት ባለበት ቦታ ሁሉ የሃይል ተቃውሞ፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ አክራሪነት፣ ሽብርተኝነት ወዘተ ይኖራል። እናም ዘላቂነቱ የተረጋገጠ ሰላም እንዲኖር ድህነትን መዋጋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ የችግሩ መነሻ ከአያያዝ ይቀደዳል እንዲሉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ስልጣናቸውን የተጠቀሙበት አኳኋን ነው።  ሃገራችን አሁን የገባችበት የሰላም እጦት ስጋት ምንጭ የመንግስት የህዝብ አገልጋይነት መጓደል ነው። ታዲያ በዚህ አኳኋን ህዝብን የማገልገል ዝንባሌ በሌላቸው በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት እጅ የገባችው ሃገር ፈተና ላይ ወድቃለች። ስለዚህ የመንግስት ስልጣን የተያዘበትን አኳኋን በማስተካከል ሃገሪቱ ከገባችበት ፈተና ወጥታ ዘላቂ ሰላሟ ይረጋገጥ ዘንድ፣ ዴሞክራሲን ማስፈንና በእድገትና ልማት ድህነትን በጉልህ ማቃለል የግድ ነው።        

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy