Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ክራሞቱ…!

0 411

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ክራሞቱ…!

ዳዊት ምትኩ

በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት መሰረት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባሮችን የሚመረምረው መርማሪ ቦርድ ስራውን ጀምሮ እንቅስቃሴው እያደረገ ነው። ቦርዱ በህገ መንግሥቱ ተለይተው የተሰጡትን ተግባሮች ከመወጣት አኳያ ስራውን በተገቢው ሁኔታ እየተወጣ ነው። በህገ መንግስቱ ላይ ፈፅሞ መጣስ የሌለባቸው ህገ መንግስታዊ መብቶችን ሁኔታ እየተከታተለ ለሚመለከተው አካላት ያቀርባል። የታሰሩ ግለሰቦችን ከማሳወቅና ሌሎች ተግባሮቹን በሚገባ ሁኔታ እየተወጣ ነው።

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ አምስት ላይ “በሀገሪቱ የአስቸኳይ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከአባላቱና ከህግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል። ቦርዱ አዋጁ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በሚፀድቅበት ጊዜ ይቋቋማል።” የሚል ግልፅ የሆነ ድንጋጌ ተቀምጧል።

ይህን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ተከትሎም ፓርላማው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ15 ቀናት ውስጥ መርምሮ በማፅደቅ፤ የአዋጁን አፈፃፀም የሚመረምሩ የቦርድ አባላትን በህጉ መሰረት ሰይሟል። ተግባራቸውን በገለልተኝነት ይወጡ ዘንድም ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን አድርጓል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ ስድስት መሰረት በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ስራውን ጀምሯል።

የቦርዱ ህገ መንግስታዊ አሰራር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁንም ግን ቦርዱ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩትን ኃላፊነቶችን በሂደት መወጣት ያለበት ይመስለኛል። በመሆኑም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ ስድስት ስር ከ “ሀ” እስከ “ሠ” ድረስ የተዘረዘሩትን ድንጋጌዎች ገቢራዊ በማድረግ፤ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በብቃት መፈፀም ይጠበቅበታል።

እናም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚወሰዱት ርምጃዎች በማናቸውም ጊዜ ኢ-ሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል ይኖርበታል። እንደሚታወቀው በተለያዩ ፅንፈኛ የመገናኛ ብዙሃንና እንደ ቪኦኤ (የአማርኛው ክፍል) ዓይነት የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ሚዲያዎች እንዲሁም ሀገራችን ሁሌም በትርምስ ውስጥ እንድትኖር የሚሹ አካላትን አሉባልታንም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ዕውነታ ተንተርሶ ሃቁን በመግለፅ ርቃኑን ማሳየት አሊያም ትክክለኛ ከሆነም ስህተትነቱን ማመላከት ያለበት ይመስለኛል።

በእነዚህ ፅንፈኛና የፖለቲካ ዝማሜ ባላቸው ሚዲያዎች አማካኝነት የሚተላለፉና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተዓማኒነት ለማጉደፍ የሚሰነዘሩ ጉዳዩች ካሉም ክትትል በማድረግና ያገኘውንም ግኝት ለህዝብ በማሳወቅ የሚነዙትን ውዥንብሮች የማጋለጥ ተግባሩን መፈፀም አለበት እላለሁ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈፃሚዎች አሊያም አንዳንድ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን አጀንዳ ለማሳካት ሲሉ በሚንቀሳቀሱ አካላት አማካኝነት ከአዋጁ መሰረታዊ እምነትና አሰራር ውጭ የሚፈፀም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ካለም ይህን ፈልፍሎ በማውጣት ሊያሳውቅና ተገቢው የማስተካከያ ርምጃም እንዲወሰድ ማድረግ ይኖርበታል። በ

አዋጁ አስፈፃሚዎች በኩል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚስተዋሉ ህፀፆች ካሉና ህፀፆቹም ኢ-ሰብዓዊ መሆናቸውን ሲያምን በህጉ መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አሊያም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በማሳወቅ ርምጃው እንዲስተካከል ሃሳብ ማቅረብ የቦርዱ ተግባርና ኃላፊነት ነው።

እንዲሁም አንዳንድ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭና የውስጥ ኃይሎች የተለያዩ አጥፊ ተግባራትን በተቀናጀ ሁኔታ በመፈፀም ‘መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲህ እያደረገ ነው’ በሚል ገፅታን የማጠልሸት ተግባር ሊፈፅሙ ይችላሉ።

መርማሪ ቦርዱ የእነዚህን ኃይሎችና የተላላኪዎቻቸውን ማንነት በሚገባ በመፈተሽ ተገቢው ህጋዊ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ መትጋት ይኖርበታል። በአጠቃላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈፅሙ ግለሰቦችንና ህጋዊ ሰውነት ያላቸውን አካላት ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ የተጣለበትን ህዝባዊና ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል እላለሁ።

እርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ኃላፊነቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ምናልባትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል የሚጠይቅ ጥያቄ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርብበበት ወቅት፤ የቦርዱ ተጠሪነት ለምክር ቤቱ እንደመሆኑ መጠን አስተያየቱን የማቅረብ ኃላፊነትም ተጥሎበታል። እርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለቤት ህዝቡ ነው።

ህዝቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሰላም ባለቤትነቱን እያረጋገጠ ነው። ከታሪክም ይሀን ካለፉት የሀገራችን ልምድ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ህዝብን ማዕከል በማድረግ የሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት ፍሬያቸው ያማረ ይሆናል።

እናም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ህዝቡ በሁከቱና በብጥብጡ የተሳተፉ አካላትን ለፀጥታ ኃይሎች አሳልፎ ከመስጠት ባሻገር፤ ራሱ የሰላሙ ዘብ በመሆን የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታን እየፈጠረ ነው።

ቦርዱ ለስድስት ወራት የሚዘልቀውን አዋጅ አፈፃፀም ከስር ከስር የመመርመር ተግባርና ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ፤ በእነዚህ ወራቶች ውስጥ ያሉትን አዎንታዊና አሉታዊ ለውጦችን መቃኘት ይኖርበታል። በዚህ ረገድም የሀገራችን ሰላም ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመለስ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

እርግጥ ቦርዱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢ-ሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሀሳብ ይሰጣል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈፅሙትንም ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ መርማሪ ቦርዱ ለሚመለከተው ያሳውቃል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀረብም ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ያቀርባል። ይህም ከላይ እንዳልኩት በአዋጁ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለማጣራት ያስቸለዋል።

መርማሪ ቦርዱ የሚያከናውናቸው ተግባራት ለሰብዓዊ መብቶች ዋስትና የሚሰጡ በመሆናቸው መጠናከር ይኖርባቸዋል። ከላይ መከናወን አለባቸው በማለት የጠቀስኳቸው የመርማሪ ቦርዱ ህገ መንግስታዊ ተግባራት ተጠናክረው ይገባል። ዜጎችም ለቦርዱ ሁለንተናዊ ስራዎች ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። የቦርዱ ተግባራት ሥርዓቱ ራሱን በራሱ የማረም ስራ በመሆኑ ሊደነቅና ለክንዋኔዎቹ ሁሉም የዜግነት ድርሻውን መወጣት አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy