Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዋስትናችን…

0 344

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዋስትናችን…

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

የህግ የበላይነትን ማስከበር የሰላም ዋስትና ነው። ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። የትኛውንም ሀገራዊ ህግ ተላልፎ የሚገኝ ግለሰብም ይሁን ቡድን ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ቅድሚያ የሚሰጠው የህግ የበላይነት ነው። በመሆኑም ከሰሞኑ በባንዴራ ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች መታየት ያለበት ከዚሁ ከህግ የበላይነት አኳያ ነው።

የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ተገቢ ነው።

ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ደንግጓል። ይህም የህገ መንግስቱን አንቀፅ 56 ላይ ተገልጿል። በዚህ አንቀፅ መሰረት በምክር ቤተ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅት የፌዴራሉን መንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ተገልጿል።

ይህም የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ከህገ መንግስቱ አኳያ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉ ማናቸውም የፖለቲካ አሊያም የሽብር ድርጅቶች ህገ ወጥ ናቸው።

ከእነርሱም ጋር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ወይም የእነርሱን አጀንዳ በማራመድ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች የህግ የበላይነትን መፃረር እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ሃይሎች ከህግ የበላይነት ጋር ሆድና ጀርባ በመሆናቸው ነው። ለምሳሌ ያህል በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ የተደነገገውን የባንዴራ ፅንሰ ሃሳብን መተላለፍ እንዲሁም ባንዴራውን በተመለከተ የወጡ ህጎችን ተላልፎ መገኘት ያስጠይቃል። የኢፌዴሪ ባንዴራ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይና መሐሉ ላይ ሰማያዊ ቀለም ያለው ቢጫ ኮከቦች ያሉት ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ ባንዴራ ይዞ መገኘት አሊያም መጠቀም ያስጠይቃል። ከሰሞኑ የተያዙት ሌላ ባንዴራ በመጠቀም የተያዙት ግለሰቦች ሁኔታም ከዚሁ አኳያ የሚታይ ነው።  

ርግጥ የህግ የበላይነት ልዕልና ሊጠበቅ ይገባል። የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል።

ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። በመሆኑም ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር በሀግ አስፈፃሚው አካል በሚፈፀምበት ወቅት የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም።

በእኔ እምነት የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው። ምክንያቱም ህገ መንግሰቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ አስፈፃሚውም አካል ሆነ ማንኛውም ዜጋ መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም። የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ ነውና። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል።

የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።

ርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው። ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል።

የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላምን እንጎናፀፋለን። ሰላምን ስንጎናፀፍ ደግሞ የምናውዳቸውን የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎችን ዕውን እናደርጋለን። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ለሆኑ አይችሉም።

በህግ የበላይነት ሁላችንም በህግ ፊት እኩል እንስተናገዳለን። የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም ተካፋዩች እንሆናለን። የህግ የበላይነት በህገ መንግስቱ ላይ የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን፤ ለአገራችን ጠቃሚነቱ ታምኖበት እንዲተገበር ምክንያት የሚሆን ይመስለኛል።

የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደረስ ይደረሳል።

መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየደረጋቸው ከመጣው መንገድ መውጣት የለበትም።

መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።

ይህ የመንግስት የህግን ልዕልና የማረጋገጥ እርምጃ በህዝቦች ደም ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚሹ አሸባሪዎች፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ፅንፈኞች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት ምህዳርና ህዝብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ ይሰጣሉ። ይህም የህግ የበላይነትን በማፅናት ህገ መንግፅታዊ ሥርዓቱን ከሴረኞችና ከተላላኪዎች የመታደግ ዋስትና ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy