Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዋስትናው

0 291

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዋስትናው

                                                          ታዬ ከበደ

የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር የእስረኞች መለቀቅ አኳያ ያለው እውነታ ቀጥተኛ ነው። የእስረኞች መለቀቅ የህግ የበላይነትን አይሸረሽርም እንዲያውም እስረኞች የሚለቀቁት ህግና ስርዓትን በተከተለ መንገድ ነው። የህግ የበላይነትን እየተረጋገጠ ሲሄድ የሚታሰሩ ሰዎች ሊኖሩ መቻላቸው እርግጥ ነው።

ሆኖም ሰዎች እንዳይታሰሩ በማሰብ የህግ የበላይነትን ትግበራ ማቆም አይቻልም። የማእከላዊ ምርመራ ማዕከል መዘጋትን ተከትሎም ሌሎች የማረሚያ ተቋማትም እንዲዘጉ መጠየቅ ህግን አታስከብሩ የሚል ቀጥተኛ ትርጉም ያለው በመሆኑ እሳቤው ተገቢ አይመስለኝም።። የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለአንዲት አገር የሰላምና የልማት ዋስትና ነው። ክንዋኔው ለድርድር የሚቀርብ መሆን የለበትም። አይገባምም።

በእኔ እምነት በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው። ምክንያቱም ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ስለሆነ ነው። የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁ ለይስሙላ የተደነገጉ አይደሉም። ዜጎች ሰዎች በመሆናቸው ሳቢያ የተጎናፀፏቸው መብቶች ናቸው።

ስለሆነም ማንኛውም አካል የህግ የበላይነት እንዳይሸረሸር መፍቀድ ያለበት አይኖርበትም። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ በሌላኛው እሳቤ የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ በመሆኑ ነው። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። ይህም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህንም ይጥሳል።

የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።

አገራችን የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ስለሚሆንባት ነው። ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል። ዋስትናዋም ነው።

በሰላም ውስጥ ሆነው ነገ ተምረውና ተመራምረው ሀገርን ሊጠቅሙ የሚችሉት። ያለ ሰላም በብጥብጥ ውስጥ የሚዳክር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ምንም ዓይነት አገራዊ ትሩፋት ሊያስገኝ አይችልም።

ከሁሉም በላይ ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ይህ አሰራር በማንኛውም ዜጋ ወይም አካል ላይ ገቢራዊ የሚሆን ነው።

አንዱን ዜጋ ከሌላው በማበላለጥ የሚከናወን የህግ አሰራር በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፤ መቼም ቢሆን። እናም የህግ የበላይነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስከበር ማለት የህገ መንግስቱን መንፈስ በሁሉም መስኮች ማስፈፀም ማለት መሆኑን የትኛውም ዜጋ ግንዛቤ መያዝ ይኖርበታል።

በህግ ጥላ ስር የዋሉ ግለሰቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መከበር አለባቸው። ለዚህ ደግሞ የአገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መጠን ማረፊያ ቤት መኖሩ የግድ ነው። እናም ማረፊያ ቤቶች መኖር የለባቸውም የሚለው ክርክር መንም ዓይነት መሰረት ያለው አይለም።

አንድ ተጠርጣሪ አሊያም ፈርደኛ ማረፊያ ውስጥ ካልተቀመጠና ከሰው ተገልሎ ቅጣቱን እዚያው ካልወሰደ ሊፈጥር ካሰበው አሊያም ከፈጠረው የወንጀል ድርጊት እንደምን ሊታረም ይችላል? በመሆኑም የማረፊያ ቦታን አስፈላጊነት በሰከነ መንገድ ከዚህ አኳያ መመልከት ይገባል። ማዕከላዊ ባለፉት ስርዓቶች ከነበረው መጥፎ ገፅታ አንፃር እንዲዘጋ ስለተወሰነ ሌሎችም ማረፊያዎች ይዘጉ የሚል ክርክር ተገቢ አይደለም። ቅቡልም ሊሆን አይችልም።

በእኛ አገር ውስጥ የህግን ልዕልና የማረጋገጥ እርምጃ በህዝቦች ደም ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚሹ አሸባሪዎች፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ፅንፈኞች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት ምህዳርና ህዝብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ-ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ከተያያዙት ድህነትን ድል የመንሳት ትግል አንድም ስንዝር ቢሆን ፈቀቅ ሊሉ የሚያደርጋቸው አይደለም።

እርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው።

ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚኖርባት ይመስለኛል።

የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላምን እንጎናፀፋለን። ሰላምን ስንጎናፀፍ ደግሞ የምናውዳቸውን የልማትና የዴሞፐክራሲ ስራዎችን ዕውን እናደርጋለን። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ለሆኑ አይችሉም።

ሰላምን እውን ለማድረግ፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የህግ የበላይነት እውን እንዲሆን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። የህግ የበላይነትን ማስከበር የፌዴራላዊ ስርዓቱ ዋስትናው እንዲሆን ያደርገዋል። ህግና የበላይነቱ በማንኛውም ጊዜ ውስጥ ለድርድር እንዳይቀርብም ቀዳዳ አይከፍትም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy