Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህይወት አድን መንገድ

0 322

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህይወት አድን መንገድ

ገናናው በቀለ

የኢፌዴሪ መንግስት የአገሪቱ ዜጎች ማንነታቸው ታውቆና መብቶቻቸው ሁሉ ተከብሮ በውጭ አገራት በህጋዊ መንገድ ሄደው መስራት የሚችሉበት እንዲሁም ለደህንነታቸው አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ አሰራር ከመፍጠር አኳያ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በምሳሌነትም በአሁኑ ሰዓት ከኩዌትና ከሳውዲ አረቢያ መንግስታት ጋር አስፈላጊውን ስምምነት መፈራረሙን መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ዜጎች በውጭ አገራት ሄደው ለመስራት እስከወሰኑ ድረስ ከህገ ወጥ ህይወት ጠላፊ ስደት ራሳቸውን በማራቅ መንግስት ለዜጎቹ ያመቻቸውን የህይወት አድን መንገድን መከተል ይኖርባቸዋል።  

ይህ የህይወት አድን መንገድ መንግሥት በአገር ውስጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅን በማውጣት ጭምር የታገዘ ነው። ሆኖም የህይወት አድን መንገዱን ከመመልከታችን በፊት በቅድሚያ የህገ ወጥ ስደት ሰላባ የሚሆኑት አብዛኛዎቹ ወጣቶች በመሆናቸው ‘ለምን ይሰደዳሉ?’ ብለን መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው ሁሉ ስደት የነባራዊ ሁኔታ መገለጫ ነው። ዜጎች በተለይም ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ሊሰደዱ ይችላሉ። ሆኖም አብዛኛው ወጣን የሚሰደደው የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው። የኢኮኖሚ ሁኔታ አንድን ሰው የተሻለ በተሻለ ሁኔታ ራሴን ልመራበት እችላለሁ ብሎ ወደ ሚያስበው ቦታ እንዲሰደድ ያደርገዋል።

ይህን ሁኔታ ወደ እኛ ሀገር ስንመልሰው፤ የሀገራችን ወጣቶች የሚሰደዱት ኢኮኖሚያቸውን በማሻሻል ራሳቸውን ጠቅመው ቤተሰባቸውን ብሎም አገራቸውን ለመጥቀም መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ወጣቶች የሚሰደዱት በፖለቲካ ምክንያት አይደለም። ወጣቱ በአገሩ የመኖር ህልውናው አጠራጣሪ የሆነበት፣ እየታፈሰ ወደ ጦርነት የሚማገድበት፣ በሚያራምደው የፖለቲካ አመለካከቱ ሳቢያ እስር ቤት የሚወረወርበት ዘመን ካከተመ 27 ዓመታት ተቆጥረዋል።

በአሁኑ ሰዓት ምንም እንኳን የተጠቃሚነት ደረጃው አሁንም ገና የሚቀረው ቢሆንም፤ ወጣቶች መንግሥት ባዘጋጀላቸው ምቹ ሁኔታ የስራ ፈጠራ እድላቸው ለምልሟል፣ የመኖር ዋስትናቸው ከፍ ብሏል፣ ዛሬ ጦርነት እያካሄዱ ያሉት ፊት ለፊቱ ከተጋረጠባቸውና አገራችንን ለዘመናት አንገት ሲያስደፋ ከነበረው ድህነት ጋር ብቻ ነው። ወጣቶች ዛሬ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በመሳተፍ በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን እንደ ልባቸው መግለፅ ይችላልሉ። ከልካይ የላቸውም። እዚህ ሀገር ውስጥ የፀረ ዴሞክራሲያዊነት መጋረጃ ዳግም ላይከፈት ተከርችሞ ተዘግቷል።

ይህ ሁኔታም የሀገራችን ወጣቶች ስደትን ከመረጡ፣ የሚሰዱበት ምክንያት ምናልባት እጅግ ባልዳበረውና በተለያዩ የአፈፃፀም ጉድለቶች ምክንያት ሁሉም ወጣቶች በሚገባ መንገድ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ብቻ ነው። ስደት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፖለዪካ ጋር አይገናኝም። ምክንያቱም የፖለቲካ ችግር ከዛሬ 27 ዓመት ገደማ በህዝቦች ሁለንተናዊ ትግል ምላሽ ያገኘ ከመሆኑም በላይ፤ በአሁኑ ሰዓት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቶች እየጎለበቱ በመምጣታቸው ነው።

ያም ሆኖ በእኔ አስተሳሰብ ወጣቶች በአገር ውስጥ ሰርተው ማደግና መለወጥ እንደሚችሉ ማስታወስ ተገቢ ነው። ስደትን በምንም ዓይነት ስሌት እንደ መጨረሻ አማራጭ መያዝ ተገቢ አይሆንም። በየትኛውም አገር ውስጥ ማርና ወተት እንደ መና ከሰማይ አይዘንብም። እጅግ ተደክሞ፣ ተለፍቶና ተጥሮ ተግሮ ነው ጥሪት የሚቋጠረው። ታዲያ ይህን ልፋትና ድካም አገር ውስጥ ማዋል ከተቻለ ማንኛውም ሰው መለወጡ የሚቀር አይመስለኝም።

የሆነ ሆኖ ዜጎች ወደ ውጭ ሄጄ እለወጣለሁ እስካሉ ድረስ ህገ መንግስታዊ መብታቸው ስለሆነ መንግሥት የፈጠረው የህይወት አድን መንገድን መገንዘብ ይገባል። እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ ወጥ ስደት የግለሰቦችንና የአገርን ክብር የሚጋፋ ነው።

ታዲያ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቀደም ባሉት ጊዜያት በመንግስት በኩል ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የህገ ወጥ ስደት ችግርን ለመፍታት የፖሊሲ፣ የፕሮግራምና የህግ ማዕቀፎች ተበጅተው ሰፊ ርብርብ ተደርጓል፤ በመደረግም ላይ ይገኛል። ጉዳዩን የሚከታተል ግብረ ኃይል ከማቋቋም አንስቶ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እስከመስጠት ድረስ ያሉት ጥረቶች መንግስት ዜጎቹን ከአላስፈላጊ እንግልትና ህይወት የማጣት አደጋ እንዲላቀቁ ያደረገው ጥረት አካል ነው።

በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል። በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ተችሏል።

እንዲሁም አገራችን የውጭ አገር የስራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 በአዲስ መልክ አውጥታ ዜጎቿ እንዳይንገላቱና በህይወት አድን ህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። አዋጁ ህጋዊነትን የሚደግፍና የሚያበረታታ እንዲሁም የህገ ወጥ ስደትን በር መዝጋት የሚችል ነው። ከአዋጁ ውጭ በህገ ወጥ መንገድ መንቀሳቀስ አደጋው ህይወትን እስከ ማጣት የሚያደርስ ነው።

በመሆኑም የትኛውም አካል ቢሆን ህገ-ወጥ ስደት ህይወትን የሚያሳጣ የተሳሳተ መንገድ መሆኑን ለመገንዘብ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ዕውቀት ሊኖረው የግድ ይለዋል። እርግጥ የአገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግም ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ማዘዋወርን በወንጀል ተግባር ይፈርጀዋል። ይኸውም ሰዎችን በኃይል ወይም በማታለል መመልመል፣ በአገር ውስጥ ወይም ወደ ሌላ ሀገር ህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር እና አዘዋዋሪዎች ተበዳዮችን የገንዘብ ጥቅም ማግኛ ማድረጋቸው ወይም ለብዝበዛ የተጠቀሙባቸው እንደሆነ በወንጀል ድርጊት እንደሚያስጠይቅ መደንገጉ ነው።

ሆኖም ጉዳዩን ህግ በመደንገግ አሊያም አዋጅ በማውጣት ብቻ መግታት ወይም ማስቆም አይቻልም። የህይወት አድን መንገዱን አውቆ ከህገ ወጡ ህይወት ቀጣፊ ዝውውር መቆጠብ ይገባል። በተለይ ቤተሰብ ልጆቹን ወደ ውጭ አገር መላክ ከፈለገ ይህንኑ ህጋዊ መንገድ መከተል ይኖርበታል።

ህጎችና አዋጆች በህዝቡ መታወቅና መደገፍ ይኖርባቸዋል። ህዝቡ ልጆቹ የት፣ ለምንና እንዴት እንዲሁም በየትኛው የህግ ማዕቀፍ ለውጭ አገር የስራ ስምሪት እንዲሚሄዱ ማወቅ ይኖርበታል። በመንግሥት ፈቃድ ያገኘው የትኛው ኤጀንሲ እንደሆነ አጣርቶ ማወቅ አለበት። ህጋዊውን ከህገ ወጡ በመለየት ለልጆቹ የህይወት አድን መንገድን ማሳየትም ይጠበቅበታል። ይህን ተግባር ማከናወን የልጁን እንግልትና ስቃይ ብሎም እስከ ህይወት ማጣት ድረስ የሚዘልቀውን አደጋ መከላከልም ጭምር ነው።   

 

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy