Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመከራውን ጊዜ ተሻግረነዋል!

0 252

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመከራውን ጊዜ ተሻግረነዋል!

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

የፌዴራላዊ ስርዓታችንን  አገራችን በስኬት ጎዳና እንድትጓዝ  ያደረገው አስትዋጽዖ እጅግ የጎላ እንደሆነ ማንም  በቅን ልቦና ለሚመለከተው ዜጋ መገንዘቡ የሚከብድ አይመስለኝም። ቅንነት የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ እንኳን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ለሚኖርባት አገር ይቅርና በጣት ለሚቆጠር የቤተሰብ አባላት ቅንነት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው።  ከህመማችን ወይም ከስቃያችን ለመፈወስ ስንል በሃኪም ትዕዛዝ የምንወስዳቸው ማንኛቸውም መድሃኒቶች እንኳን የየራሳቸው የሆነ የጎንዮሽ ጫና እንዳላቸው ይታወቃል።

 

የፌዴራል ስርዓታችንም  ለበርካታ ችግሮቻችን መፍትሄ እንዳስገኘልን ሁሉ  አንዳንድ ችግሮችም አስከትሎ ሊሆን ይችላል። ይሁንና እነዚህ ችግሮች ሊስተካከሉና ሊታረሙ የሚችሉ መሆናቸው  ደግሞ ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምንታት የነበረው ሁኔታ አረጋግጦልናል። “አይጥ አስቸገረ ተብሎ ቤት አይቃጠልም” እንደሚባለው፤  ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጥበት በሚያደርጉት መሳሳብ እንዲሁም ባለፉት 27 ዓመታት መንግስት የህዝቦችን አብሮነት ለማጎልበት፤  የአገሪቱን አንድነት ለማጠናከር ያከናወናቸው ተግባራት የሚጠበቀውን ያህል አለመሆናቸው አገራችንን ለቀውስና ሁከት ዳርጓታል። በርካታ ንጹሃን ዜጎች ያለሃጢያታቸው ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ወዘተ።  ይሁንና ያን የመከራ ጊዜ ተሻግረነዋል፤ ያ መጥፎ ጊዜ አሁን አልፏል፤ ዛሬ አገራችን በአዲስ አመራር በለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች።

 

ኢትዮጵያ  የቀንዱ አካባቢ  የሰላም ደሴት ለመባል ያበቃት ይህ  የፌዴራል ስርዓት ነው። አገራችን የተረጋጋች ሰላም የሰፈነባት ለመሆን የበቃችው የህዝቧቿ መሰረተዊ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የሚያስችል አስተዳደርን  መከተል በመቻሏ ብቻ ነው። በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች ለአብነት የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የማንነት፣ የአስተሳብ የሚስተዋሉባት እንዲሁም በዓለም በነውጥ ቀጠናነቱ በሚታወቀው ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምስራቅ አፍሪካ  ቀጠና የምትገኘው አገራችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የበቃችው በተከተለችው የፌዴራላዊ የአስተዳደር ስርዓቷ ነው። አህዳዊ ስርዓት ለኢትዮጵያ ህዝቦች አዲስ ነገር አይደለም፣ የባለፉት አህዳዊ ስርዓቶች አገሪቱን ለምን ዳርገዋት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በመሆኑም የጎደለን ነገር እያሟላን አገራችንን ወደከፍታው ማሸጋገር እንጂ  በትንሽ በትልቁ መናቆራችን ለውጭ ጥቃት እንደሚዳርገን መገንዘብ ይኖርብናል። እንደእኔ እንደኔ በ21ኛው ዘመን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከፌዴራል ስርዓት ውጪ ማሰብ ራስን በራስ እንደማጥፋት የሚቆጠር ተግባር ይመስለኛል። ምክንያቱም በርካታ ልዩነቶች ተይዞ ጠቅልዬ ልግዛ ማለት ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ አይመስለኝም።

 

የፌዴራል ስርዓታችን  ዘላቂ ሰላም አስፍኖልናል፤  ልንለማ፣ ልናድግና ልንለወጥ እንደምንችል ባለፉት 27 ዓመታት  በተጨባጭ አሳይተውናል። ብዝሃነትን በአግባብና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መያዝ ከተቻለ የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ እንደሚሆነም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ጥሩ ምሳሌ ናት።  የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን ተቀብሎ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት መገንባት በመቻሏ፣ ህብረ ብሄራዊነት የልዩነት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የሥርዓቱ ዋልታና ማገር ስለሚሆን በልዩነት ወስጥ ያለውን አንድነት የህዝቦች አብሮነት  ማሰሪያ ገመድ ነው። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ከተረጋገጠ አብሮነትን የሚጠላ አካል አይኖርም። እስካሁን ያለው አብሮነትም የስኬታችን መነሻም መድረሻም ነው። በዘመነ ግሎባላይዜሽን የህዝብ ብዛት ተጨማሪ አቅም እንጂ ክስረት አይደለም። ስለመለየት ጉዳት ኤርትራዊያኖች  ቢመሰክሩ መልካም ይመስለኛል። ኤርትራ አሁን ላይ ከአንድ ሶስተኛው የማይተናነሰው ዜጋዋ ለስደት የተዳረገባት አገር ለመሆን የበቃችው አምባገነን መሪ ያላት አገር ስለሆነች ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ያላት ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ደካማ በመሆኑ ነው።

 

መንግስት ልዩነታችንን ሊያሰፉ ህዝብን  ሊያራርቁ የሚሯሯጡ ሃይላትን ከእንግዲህ ሊታገሳቸው አይገባም። እንደእኔ እንደኔ  እነዚህ ሃይሎችን መንግስት ከህዝቡ ጋር በመተባበር ህግ ፊት ሊገትራቸው ይገባል ባይ ነኝ። የህግ የበላይነት መቼም  ከድርድር መቅረብ የለበትም። አዲሱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በልባችን የዘሩት ተስፋ ፍሬ እንዲያፈራ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ሁሉም የሚችለውን  ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጠባቦችና ትምክህተኞች የህልውናችን መሰረት የሆነውን የፌዴራል ስርዓታችንን ለመበትን የሚያደርጉትን መሯሯጥ ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ልንዋጋቸው ይገባል።  ሌባ ከየትኛውም ብሄር ይሁን ሁላችንም ተባብረን ሌባ ልንለው ድርጊቱን ልናወግዘው ይገባል። የብሄር ካባ ለብሶ ጥቅም ማሳደድ ሊወገዝ የሚገባው ድርጊት መሆን መቻል አለበት።

 

የፌዴራል ስርዓታችን ያስተማረን ትልቅ ነገር መቻቻል፣ መከባበርና አበሮ መኖርን ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ይህን እሴታችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በየአካባቢው እያስተዋልን ነበር። ህዝቦችን በማጋጨት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ለማንም አይበጅም። ባለፉት 27 ዓመታት ተቻችለንና ተከባብረን አብረን  በመኖራችን በርካታ ነገሮችን አትርፈናል፤ ሰፊና አማላይ ገበያ፣ ጠንካራና አዳጊ ኢኮኖሚ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ መንግስት፣ በስነ ምግባር የታነጸ ህዝባዊ የጸጥታ ሃይል ወዘተ ባለቤት ሆነናል። የአገራችን ስኬቶች የሁላችንም ድምር ውጤቶች ናቸው።  እንግዲህ ስኬቶችን እንደተጋራናቸው ሁሉ ድክመቶችም የሁላችንም እንደሆኑ ታሳቢ ማድረጉ ተገቢ ነው። ይህ ሲሆን ለችግሮቻችን መፍትሄ ማፈላለጉ ቅርብና ቀላል ይሆናል።

ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ መድረክ የነበራት ገጽታም ሆነ  ተሰሚነት ባለፉት 27 ዓመታት እጅጉን ተለውጧል፤ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም በመስፈኑ  በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው። ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃን ዋቢ ላድርግና  በ2009 ዓ.ም ብቻ አገራችን በከባድ ድርቅ ተመትታና በበርካታ አካባቢዎች ሁከት ተከስቶ ሳለ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የ30 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በዚህ መሠረት በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ካፒታል ላስመዘገቡ 290 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ይህ የሚያመላክተው የኢፌዴሪ መንግስት በውጩ ዓለም ያለው ታዓማኒነትን ነው። ኢንቨስትመንት ሁሌም ተዓማኒነትን ይፈልጋል።

በውጭ ግንኙነት ረገድም  ኢትዮጵያ የምትከተለው ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ አገሪቱን ስኬታማ አድርጓታል።   ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ  ባለስልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን በተባበሩት መንግስታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረከኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን መንግስት ባከናወነው  ተግባር ሳቢያ የመጣ ስኬት ነው።

 

ኢትዮጵያ  የምስራቅ አፍሪካ  አገሮችን ሰላም ዘላቂ እንዲረጋገጥ  ከምታደርገው የሰላም ማስከበር ስራ ባሻገር አገራት በኢኮኖሚ ጥቅም እንዲተሳሰሩ  በርካታ ተገባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ለአብነት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱ ነው።   በታዳጊ አገር አቅም ለመገንባት አይታሰብም የሚባለውን ይህን ፕሮጀክት አሁን ላይ ከ65 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህስ የፌዴራል ስርዓቱ እውን ከሆነ ብኋላ የመጣ ስኬት አይደለምን?  እንዲሁም አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር ሙገሳን ተችሯታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች።  

አገራችን ከላይ ያነሳኋቸውን ስኬቶች  ማስመዝገብ የቻለችው በመከባበርና በመቻቻል አብሮ በመኖራችን ነው። አብሮ መኖር ያስቻለን ደግሞ ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ  የስቻለን የፌዴራል ስርዓታችን ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የህዝቦች አብሮነት፣ የአገር አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም  የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲችሉ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለን አገር ወዳድ ዜጎች ከጎናቸው ልንቆም ይገባል። የበቀል መንገድ ይዘጋ፤ በበቀል አሸናፊም ተሸናፊም የለም። የሁለት ዓመት ተኩል ሁከትና ነውጥ አገራችንን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላት  ተመልክተናል። አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ በቀጣይ ማየትም ሆነ መስማት የሚፈልገው ስለ ሁከትነና ነውጥ፤ ስለስደትና ረሃብ ሳይሆን ስለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ስኬት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy