Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም ጥሪውና የኤርትራ መንግስት

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም ጥሪውና የኤርትራ መንግስት

                                                  ዘሩባቤል ማትያስ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ላይ “…ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለት ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለለጽኩ፤ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።…” በማለት የሰላም ጥሪን ከቁርጠኛ አቋም ጋር ማቅረባቸው ይታወቃል።

ይሁንና የኤርትራ መንግስት ጥሪውን ተከትሎ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ በአቶ የማነ ገብረመስቀል አማካኝነት “ሀገራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ልትደራደር የምትችለው ባድመ ከተመለሰላት ብቻ ነው” ብለዋል። አቶ የማነ አያይዘውም፤ ሰላም ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው በመግለፅ፤ ኢትዮጵያ አሁንም ዓለም አቀፍ ህጉን ባልተከተለ መንገድ ባድመን በኃይል ይዛለች ብለዋል። የድርድር ኳሱ በኢትዮጵያ እጅ እንደሆነ እንደሆነና ኢትዮጵያ የኤርትራን ሉዓላዊነት በማክበር በኃይል የያዘችውን የኤርትራ ግዛት ባድመን ጨምሮ መልቀቅ እንዳለባት ተናረዋል። ይህ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ አባባል ሁሌም ሀገራችን ለሰላም የዘረጋቻቸውን እጆች የማጠፍ ልማድ ያለው ነው። አዲስ ነገር የለውም።

ምንም እንኳን ሀገራችን ለሰላም ቀናዒ በመሆን ከራሷ አልፋ የጎረቤቶቿን ሰላም የምታስከብር የአፍሪካዊያን የችግር ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ብትሆንም፤ የሻዕቢያ መንግስት ግን ሰላምን ሊያመጡ የሚችሉና ሁለቱንም ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዩችን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ተነገግሮ ከመስራት ይልቅ፤ ከ18 ዓመት በፊት ይዞት የነበረውን ዲስኩር ዛሬም ያነበንባል። ይህ ሁኔታም የሁለቱን ሀገራት በተለይም ወንድም የሆነውን የኤርትራን ህዝብ በእጅጉ እየጎዳው ነው። የኤርትራ ህዝብና መንግስት ከኢትዮጵያ መጠቀም የሚገባቸውን ምጣኔ ሃብታዊ ትሩፋቶችን እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። የአስመራው መንግስት ህዝቡን መመገብ እንኳን ተስኖት በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲማቅቅ እያደረገው ነው። ሁኔታው አጣብቂኝ ውስጥ ከቶትም ጦርነትን እንደ ንግድ በመቁጠር “የጦር ነጋዴ” (War Merchant) ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ነው። “በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የኤርትራ መንግስት ያልወረረው ራሱን ብቻ ነው” እስከሚባል ድረስ ያለውን ጥሪት አሟጦ በሚሸምተው የጦር መሳሪያ አጎራባቹን ወሯል። የአጎራባቾቹን አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ሃይሎች እያደራጀ፣ እያሰለጠነና እያስታጠቀ በማሰማራት የድንበር አካባቢዎቻቸውን ያውካል። በተለይም የራሳቸው ፍላጎት ያላቸውንና የኢትዮጵያ ጠላቶች የሆኑ አንዳንድ ሀገሮችን ፍላጎት በማስፈፀም የቀጣናው ስጋት እየሆነ ነው።

እነዚህን ሁሉ ችግሮች በቀጣናው ሀገሮች ላይ በመፈፀም ኑሮውን በድጎማና በወደብ ሽያጭ ያደረገው የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ በኩል የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ለመቀበዕ ፈቃደኛ አለመሆኑን በቅድመ ሁኔታነት “ባድመ ይሰጠኝና ከዚያ እድራደራለሁ” ማለቱ ብዙ የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም አሁን ያለበት የተላላኪነት ሚናው አዋጭ መስሎ ስለሚታየው ነው።

ሃቁ ግን ለይስሙላም ቢሆን አቶ የማነ ገብረመስቀል እንዳሉት ሰላም ሁለቱንም ሀገሮች የሚጠቅም መሆኑ ነው። የተላላኪነት ሚና የመላላኩ ምክንያት በሚያቆምበት ጊዜ ብን ብሎ መጥፋቱ አይቀርምና። እናም ሻዕቢያ ለሰላም የተዘረጋውን የኢትዮጰያን እጅ መግፋት አይኖርበትም። ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ ይኖርበታል። “የእንቁጣጣሽ ቀን ያበደ ሁሌም ዘፈኑ አበባ ይሆሽ ነው” እንደሚባለው ‘በመጀመሪያ ባድመ ይመለስልኝና ከዚያ እደራደራለሁ’ ማለት የሚያዋጣው አይመስለኝም።

ባድመ መቼም ቢሆን የኤርትራ ሆና አታውቅም። እንዲያው የሻዕቢያን መሪዎች ደስ እንዲላቸው ብለን “ነበረች” እንኳን ብናስብ፤ የዚህች አነስተኛ መሬት ጉዳይ ይህን ያህል ሊያንገበግበው አይችልም። ሊያንገበግበውና ሊያሳስበው የሚገባው ጉዳይ የህዝቦች ዘላቂ ሰላም ነበር። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ሳይለያዩ እንዴት አብረው መኖር እንዳለባቸው እንደ ሀገር ማሰብ በተገባው ነበር። ቤተሰቦች ተለያይተውና ጎጆአቸውም ሁለት ቦታ ተገምሶ ይኑሩ የሚል ፍርደ ግምድልነትን ባላቀነቀነ ነበር።

የባድመንና አካባቢውን ጉዳይ በሰለጠነ መንገድ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መጨረስ እየተቻለ የህዝቦችን ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ሁኔታን አንግቦ እንደ ቅድመ ሁኔታ መጠቀም ማቅረብ ትክክል አይደለም። በየትኛውም ወገን ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ይሁንና የኤርትራ መንግስት በባህሪው ለህዝብ የማያስብ እንዲያውም የህዝቦችን ተጠቃሚነት በመሸርሸር ፀረ ዴሞክራሲያዊነት የተጠናወተው ስለሆነ ‘ለምን እንዲህ ያስባል’ ማለት የሚቻል አይመስለኝም።

በእኔ እምነት ምናልባትም የምግብ ዋስትናን በሀገረ ኤርትራ ከማረጋገጥ በፊት የባድመ ጉዳይ መቅደም ይኖርበታል ሳይል የሚቀር አይመስለኝም። እናም የራሱ ያልነበረችውንና ሆና የማታውቀውን ባድመን እንደ ምክንያት በማቅረብ የሰላም ጥያቄን ውድቅ ማድረግ የተለመደ ተግባሩ ሆኗል። ያም ሆኖ ግን አሁንም የኢትዮጵያ የሁልጊዜ ሰላም ወዳድ አቋም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነትም ቀርቧል። እናም የኤርትራ መንግስት አንድ ቦታ ላይ ተቸክሎ የሚያቀርበውን የተሳሳተ አቋሙን ወደ ጎን በማለት ስለ ሰላም የተዘረጉ እጆችን መጨበጥ ይኖርበታል—ከሁሉም በላይ የህዝብ  ሰላምና ተጠቃሚነት ይቀድማልና።

ሌላው ቀርቶ ‘የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ በኤርትራ መንግስት ወራሪነት የተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ባድመና አካባቢዋ ነበሩ ወይ?’ የሚል ጥያቄ ብናነሳ፤ የጦርነቱ መነሻም ይሁን መድረሻ ባድመና አካባቢዋ አለመሆኑን ራሱም የኤርትራ መንግስት በሚገባ ያውቀዋል። እንደሚታወቀው የአስመራው አስተዳደር የራሱን የተፈጥሮ ፀጋዎች ከመጠቀም ይልቅ በሌሎች አንጡራ ሃብት ላይ ተንጠላጥሎ ለማደግ የሚሻ ነው።

በዚህም ሳቢያ ከነፃነት በኋላ የኤርትራ መንግስት ፍፁም ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለመጠቀም ቆርጦ ተነሳ። የሀገራችንን የተለያዩ ምርቶች በራሱ ስም እየተለጠፈ ከመሸጡም በላይ፤ ሀገራችን ውስጥ በነበረው ባንኮች ውስ ፎርጂድ እስከመስራት የደረሰ ወንጀሎችን ሲፈፅም ነበር።

በድንበር አካባቢም የገንዘብ ልውውጡ እርሱን በሚጠቅም መንገድ ብቻ እንዲከናወን እስከመጠየቅ ደረሰ። ሁሉንም ጉዳዩች በትዕግስት ሲይዝ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ግን ሀገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማሻሻዎችን በመከተሉ ሻዕቢያ አኮረፈ። ኩርፊያውንም ባድመንና አካባቢዋን በመውረር ገለፀ። ሃቁ ይህ ነው። ይህም ሲጀመር የወረራው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እንጂ ከድንበር ጋር የተገናኘ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ያም ሆኖ ሻዕቢያ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ወሰደው። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግን ቀደም ሲል እንዳልኩት ህዝቦችን የሚጠቅም አልነበረም። የአንድን ቤተሰብ ጎጆ ሁለት ቦታ የሚከፍልና ቤተሰብን ጭምር የሚለያይ ነው።

ይሁንና እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የተወሰነው የአልጀርሱ ስምምነት ለህዝቦች ዘላቂ ሰላም የማይጠቅም መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱ ሀገራትን ህዝቦች የሚያቀራርብና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ ነበር። ይህን ለሁለቱም ሀገራት የሚበጅና በጠረጴዛ ዙሪያ እንደራደር የሚል ወሳኝ መግለጫን ወደ ጎን በማድረግ በኢፌዴሪ መንግስት የተዘረጉትን የሰላም እጆች አልቀበልም በማለት ጦረኝነትንና ትንኮሳን የሙጥኝ ያለው የኤርትራ መንግስት ነው።  

በመሆኑም በእኔ እምነት የድንበር ማካለሉ ጉዳይና የመደራደሩ ሁኔታ በኤርትራ መንግስት ሜዳ ላይ የሚገኝ ኳስ እንጂ በኢትዮጵያ መጫወቻ ሜዳ ላይ አይደለም። ይሁንና የኤርትራ መንግስት በራሱ ሜዳ ላይ ያለችውን ኳስ የውስጥ ችግሮቹ ማስተንፈሻ ከማድረግ አልቦዘነም። እነሆ በሀገሩ ህዝብ ላይ የጫነውን የባርነት ቀንበር ዕድሜ ለማራዘምም የድንበር መካለሉን ጉዳይ በመጫወቻ ካርድነት እየመዘዘው ይገኛል።

የኤርትራ መንግስት የባድመን ጉዳይ በንግግር ከፈፀመ በህዝቡ ላይ የጫነበት የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ሊያቆም ነው። ‘ኢትዮጵያ ልትወረን ነው’ በማለት የህዝቡን ስነ ልቦና በመስለብ የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም የሚጠቀምበት እንዲሁም ‘ኤርትራ በጠላት የተከበበች ናት’ እያለ ለህዝቡ የሚገልፀው አስገራሚ ትረካም መቆሙ ነው። አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ጠላት ስለሆነ እንዲሁም ተቃዋሚ ኃይሎችን ለጥቃት የሚያሰለጥን በመሆኑ ሳቢያ የሚሰፍሩለትን ዳረጎትም ማጣቱ ነው። እናም በእነዚህና ለሌሎች ጉዳዩች ሻዕቢያ የሰላም ጥያቄውን ጉዳይ ምክንያት ያልሆነችውን ባዕመን እንደ ምክንያት በማቅረብ ሁሌል ለሰላም የተዘረጉ እጆችን አይቀበልም።

በእኔ እምነት ግን የኤርትራ መንግስት ቅድሚያ ለህዝቦች ዘላቂ ሰላምና ተጠቃሚነት ማሰብ ይኖርበታል። የሁለቱ ሀገር ህዝቦች ሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል ዴሞክራሲያዊ መርህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት ይኖርበታል። እናም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበላትን የሰላም ጥያቄ የሚቀበልበትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ወደ ተግባር የሚገባበት ወቅት አሁን መሆኑን መረዳት ይኖርበታል እላለሁ።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy