Artcles

የስልጣን ሽግግሩና አንድምታው

By Admin

April 12, 2018

የስልጣን ሽግግሩና አንድምታው

                                                       ዘአማን በላይ

ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ በኋላ፤ ለመላው የሀገራችን ህዝብ ካሰሙት ንግግር ውስጥ ስለ ስልጣን ሽግግሩ የገለፁት እውነታ የዚህ ፅሑፍ መነሻ ነው። እርሳቸው እንዳሉት የስልጣን ሽግግሩ ሁለት አበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው። ይኸውም አንደኛው፤ የሽግግሩ ክስተት በአንድ በኩል በሀገራችን ዘላቂ፣ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መሰረት ለመጣላችን ማሳያ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ከጊዜው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝ እንዲሁም በህዝብ ፍላጎት ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ስርዓት እየገነባን መሆኑን ያመላክታል ማለታቸው ነው። እነዚህን ሁለት አበይት ሁኔታዎችን ዘርዘር አድርጎ በመመለከት አንድምታቸውን መቃኘት ይገባል ብዬ አስባለሁ።

አዎ! ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት፤ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ ዘላቂና የተረጋጋ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መገንባት ችለናል። ባልተረጋጋና መሰረት በሌለው ስርዓት ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሊካሄድ አይችልም። ባልተረጋጋና መሰረት በሌለው ስርዓት ውስጥ ሊኖር የሚችለው የስልጣን ፍልሚያ ነው። ፍልሚያው ደግሞ የህዝቦችን ሰላምና መረጋጋት ከማሳጣት ባሻገር ፍልሚያው የሚካሄድበት አካባቢ የሚገኙ ህዝቦችም ለእንግልትና ለስደት ይዳረጋሉ። የስቃይና የሰቆቃ መናኸሪያ በመሆንም ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። በእነዚያ ሀገራት የሚካሄደው የስልጣን ሽግግር በጦርነት ብቻ የሚገኝ ነው። ሆኖም ምስጋና ስርዓቱን ላመጡት ውድ የህዝብ ልጆች ይሁንና አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባለቤት ሆናለች።

ከታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መስዕዋትነት በኋላ ክፍተቱን ለመሙላት ቦታውን የተኩትና በአሁኑ ወቅት በራሳቸው ፈቃድ ስልጣናቸውን የለቀቀቁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሀገራችን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ አንዱ ማሳያ ይመስሉኛል። የእርሳቸውን ፈቃዳዊ ስልጣን መልቀቅ ተከትለው በቅርቡ በፓርላማ የተሰየሙት ዶክተር አብይ አህመድም ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ መሰረት ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባቱና መሰረት ለመጣሉ ሁነኛ ማሳያ ናቸው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያችን ያለፈቻቸው ቀደምት አስከፊ ጉዞዎች በህዝቦች መስዕዋትነት ተገትተዋል። ጨቋኙ አምባገነናዊ ስርዓት በህዝቦች ክንድ ዛሬ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።

ዛሬ በህዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጥጦ መንገስ አብቅቷል። የመንግስት ስልጣን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚሸጋገሩባት ሀገር መፍጠር ተችሏል። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ሰላምና ዴሞክራሲ መሰረት በማድረግ ከልማቱ በፍትሃዊነትና በእኩልነት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የፀና እምነት ተይዟል፡፡ ፍሬውንም መቋደስ፣ ፅዋውንም ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ መነሻ መሰረቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በደም ቀለም በተጻፈ ቃል ኪዳን ያፀደቁት ህገ መንግስት ነው።

የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካይነት ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ውሎ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በተወካዮቻቸው አማካኝነት እየፀደቀ መሪን መምረጥ የዚህች ሀገር አዲስ ክስተት ሆኗል።

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው መስመር እየተቀላጠፈ ነው። ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በመደረጉ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እየሰደደ እንዲሄድ ማድረግ ተችሏል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዝሃነት የዴሞክራሲያዊ አንድነት ምንጭ ሆኗል። ዛሬ የብዝሃነት አስተሳሰብ ተቀይሯል። የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ታሪክ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች እየተጠናከሩ ነው። የደርግ መንግስት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው ታሪክ መሰረት አልባ ሆኗል።

ዛሬ ኢትዮጵያ እንደ ዶክተር አብይ አህመድ ያሉ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጰያዊነት የሚገልፁ ውድ ልጆችን አፍርታለች። ለዚህም እርሳቸውን ለዚህ ታሪካዊ መድረክ ያበቃቸው ኢህአዴግ መመስገን ያለበት ይመስለኛል። ያም ሆኖ በሀገራችን የተካሄደው የስልጣን ሽግግር ሀገራችን የመሰረተችው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምን ያህል በተረጋጋ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑን ማሳያ ነው።

በሌላ በኩልም የስልጣን ሽግግሩ ከጊዜው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝ እንዲሁም በህዝብ ፍላጎትና ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ስርዓት ለመገንባታችን አስረጅ ይመስለኛል። ጊዜው እየተለዋወጠ ነው። በፖለቲካ ረገድ ሁሉም ህዝብ ድምፁ እንዲሰማ ይፈልጋል። ምንም እንኳን ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ከአንድ እድገት ወደ ሌላኛው በፍጥነት ብትረማመድም ቅሉ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩ ልዩ ችግሮች እያጋጠሟትና ችግሮቹንም በፍጥነት መፍታት ባለመቻሉ የተነሳ ለሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ስትጋለጥ ቆይታለች። የመጀመሪያው ዋነኛ ችግር ሆኖ የተከሰተው መልካም አስተዳደር የማስፈን ጉዳይ ነው።

ምንም እንኳ በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት የተጓዘችበት ሂደት የህዝብን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገና ለፈጣን እድገት ያበቃት ቢሆንም፤ በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን የመልካም አስተዳደር ችግር እየተባባሰና የሀገራችንን ህዝቦች እያስመረረ ለችግር ዳርጎናል።

የተደራጀ ሙስናም እየተበራከተና የህዝብን ልማታዊ ጥረትና ተጠቃሚነት በእጅጉ እየጎዳም ሲሄድ መቀየቱ ግልጽ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎችም ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ የርስ በርስ ግጭቶች እየተስፋፉ የዜጎችን ህይወት አጥፍተዋል። እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በጽኑመሰረት ላይ የቆመና ራሱን በራሱ የሚያርምበት አሰራር ያለው በመሆኑ ችግሮቹን በአስቸኳይ መቅረፉ አይቀርም። የስርዓቱ ጥንካሬም በችግር ውስጥ ሆነንም የስልጣን ሽግግር እንድናካሂድ አድርጎናል።

በሌላ በኩልም በተለይ ላለፉት 16 ዓመታት በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አማካኝነት የተፈጠረው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት በህዝቡ ውስጥ ፍላጎቶችን መጨመር ችሏል። እነዚህ ፍላጎቶች አንዳንዶቹ በፍጥነት የሚፈቱ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከአቅም አኳያ የጊዜ ዑደትን የሚጠይቁ ናቸው። ለምሳሌ በሀገራችን በተፈጠረው የኢንዱስትሪ ዕድገት ሳቢያ የተፈጠረውን የሃይል እጥረትና መቆራረጥ ለመፍታት ድርጅታዊ መፍትሔ የሚሰጥ አካል ያስፈልጋል።

ርግጥ ሁሉንም ችግሮች በአንዴ መፍታት አይቻልም። ጊዜን፣ በጀትንና የማስፈፀም አቅምን የሚጠይቁ ችግሮች በርካታ ናቸው። ያም ሆኖ እነዚህን ችግሮች ዕቅድን አውጥቶ ቅሬታ በማይፈጥሩበት መንገድ በአግባቡ መመለስ ያስፈልጋል። ይህን የሚመራና የችግሮቹን መፍትሔዎች የሚያመነጭ እንዲሁም በተግባር የሚፈፅም ራሱን በጥልቀት የፈተሸ ድርጅትና መሪ ማግኘት የግድ ይላል። ይህን ማከናወን ተችሏል። ድርጅቱ እምነት የጣለባቸውን ዶክተር አብይ አህመድን የመረጠውና የስልጣን ሽግግሩ እንዲካሄድ ያደረገው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል።

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላለፉት 27 ዓመታት በህዝቦች መካከል የነበሩትና ከታሪክ የተወረሱ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይህም በሀገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሀገራችን ህዝቦች መካከል እጅግ መልካም ግንኙነት ተፈጥሮ ህዝባዊ አንድነቱም በዚያው ልክ እየተጠናከረ እንዲሄድ ያደረገ ይመስለኛል። ዳሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ ደረጃ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያሻክሩ ዝንባሌዎችና ግጭቶች እየተስፋፉ ሲመጡ ተስተውሏል። የእነዚህ ግጭቶች ምክንያት ፌዴራላዊ ስርዓቱ አይደለም። በየአካባቢው የሚገኙ ጠባቦች፣ ትምክህተኞች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው።

አልፎ አልፎ የተከሰቱት እነዚህ የቅርብ ጊዜ ግጭቶቸ በህዝብ ላይ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትለዋል። በግጭቶቹ የተነሳ ከየብሄረሰቡ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለተለያዩ ማህበራዊ ምስቅልቅሎች ተጋልጠዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ የመጡ የእርስ በርስ መጠራጠሮችና አንድን ማህበረሰብ ነጥሎ በማጥላላት ላይ የተመሰረተ አካሄድ ተፈጥሯል።

ይህን ሁኔታ በፅናት የማስተካከል እንቅስቃሴ ማካሄድ አስፈላጊ ነው። እነዚህን ውስብስብ ሁኔታዎች መፍታት የሚችል፣ ራሱን በጥልቀት የፈተሸ መሪ ድርጅትና አስፈፃሚ ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሔ ነው። በፅኑ መሰረት ላይ የቆመው ህገ መንግስታዊ ስርዓት ደግሞ በህዝቦች የሚቀርቡ ማናቸውንም ጉዳዩች የመፍታት አቅም ያለውና በህዝብ የሚታዘዝ በመሆኑ ለጊዜያዊ ችግሮች መፍትሔ ይሰጣል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም በድርጅታቸው መሪነት ለእነዚህ ችግሮች አስተማማኝ መስጠት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።