Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀን ቅዠቱ…

0 295

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቀን ቅዠቱ…

                                                                ታዬ ከበደ

ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ በፓርላማ ያሰሙትን ንግግር ተከትሎ፤ ፅንፈኞችና ትምክህተኞች ይብዛም ይነስም አንዳንድ አደገኛ ፕሮፓጋንዳዎችን እየቀላቀሉ የህብረተሰቡን አመለካከት ለማዛባት ጥረት እያደረጉ ነው። በተለይም ዶክተር አብይ በመመረጣቸው “የህወሓት የበላይነት አለቀለት!“፣ “ዶክተሩን እንዲመረጡ ያስቻላቸው የኦሮሞና የአማራ አንድነት መፍጠር ነው” በማለት የሚነዙትን እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኢትዮጵያ ላይ ማተኮሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የብሄር ብሄረሰቦች ራስን በራስ ማስተዳደር የአገሪቱን አንድነት እንደሚጎዳ አድርጎ ለማራገብ እየሞከሩ ያሉት የተዛባ አስተያየት ትክክል ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ሃቁን የማያንፀባርቅ ጭምር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ህዝብ ያቀፈውን ብሄር ሰለሚወክሉ እንደተመረጡ፣ በአገሪቱ በግላቸው ብዙ ለውጦችን እንደሚያመጡ፣ ለለውጥ ዝግጁ ቢሆኑም መከላከያን እና ደህንነቱን የሚመሩት አካላት እንደማያሰሯቸው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአስቸኳይ ማንሳት እንዳለባቸው ፅንፈኞች የሚያስተላልፉትን መሰረተ ቢስ አሉባልታዎች የገዥው ፓርቲንና የኢፌዴሪ መንግሥትን ባህሪና ማንነት ካለመረዳት የመነጩ ናቸው። በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዩች ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ ማስጨበጥ ይገባል ብዬ አምናለሁ።

በቅድሚያ ዶክተር አብይ ቢመረጡም ባይመረጡም ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለችው ፌዴራላዊ ስርዓት ለየትኛውም ብሔረሰብ የበላይነት የሚሰጥ አይደለም። የትኛውንም ብሔር በበታችነት አይመለከትም። እንዲህ ዓይነቱ የበላይና የበታች አስተሳሰብ ካለፉት ስርዓቶች ጋር አብሮ አክትሟል። እናም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን በመምጣታቸው “ያበቃለታል” የሚባል ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ አይኖርም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን የመጡት እርሳቸው እንዳሉት ሁሉንም የአገራችንን ህዝብ በእኩልነት ለማገልገል ነው። በተለይም በብሔር ላይ የተመሰረተ ጥቃት የሚያከናውኑ አካላትን ለህግ በማቅረብ ይህ ዓይነቱ ተግባር ዳግም እንዳይፈፀም ለማድረግ ይመስለኛል። በአገራችን ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ አካል በመሆን በአዲስ አስተሳሰብ አገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ቃል ገብተው መሆኑን ፅንፈኞቹና ትምክህተኞቹ ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል። ከዚህ ውጭ እነርሱ እንደሚያስቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእነርሱን ሸውራራ አስተሳሰብ ለማራመድ ወደ ስልጣን አልመጡም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሳል፣ ሁሉንም ህዝቦች እንደራሳቸው የሚወዱ ስርዓቱና ድርጅታቸው ኢህአዴግ የወለዳቸው የህዝብ ወገን መሆናቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተመረጡት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ያቀረቡትን የስራ መልቀቂያ ተከትሎ ነው። የነበረውን ክፍተት ለመሙላት ነው። የስራ መልቀቂያውንም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተቀብሎታል።

የኢህአዴግ ምክር ቤትም የስራ መልቀቂያውን ተቀብሎ ክፍተቱን ለመሙላት ከአራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ 180 አባላት በድርጅቱ አሰራር መሰረት በምስጢር በሰጡት ድምፅ ነው። ይህም ማን ለማን ድምፅ እንደሰጠ በማይታወቅበት የምስጢር አሰራር “አገሌና እገሌ ድምፅ ስለሰጡ ዶክተሩ ተመረጡ” የሚያስብል ነገር የለውም።

ፅንፈኛውና ትምክተኛው አካል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለ ኢትዮጵያ የተናገሩትን ጉዳይ በማራገብ እግረ መንገዱን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ሲቃወም ተደምጧል። ይህም በኢትዮጵያዊነት ሰበብ የራሱን ፍላጎት ለማስረፅ ያደረገው ተግባር መሆኑ ግልፅ ነው። እርግጥ ማንም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነትን አይጠላም። ጠቅላም ሚኒስትሩም የትናንቷን ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር በማንሰላሰል ስለ ኢትዮጵያዊነት የተናገሩት ትክክል ነው። ሆኖም ይህ ኢትዮጵያዊነት የህዝቦችን መብቶች የሚጋፋ አይደለም።

እንደሚታወቀው በዴሞክራሲያዊው ህገ መንግስታችን አማካኝነት የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች…ወዘተ ተከብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

እነዚህን መብቶች ሁሉ ያረጋገጠ ህገ መንግስት ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በምንም ምክንያት ሊገነጠሉ አይችሉም። በአገራችን ላይም ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም።

እነዚህን መብቶች የሚቃወሙት ፅንፈኞችና ትምክህተኞች ፍላጎታቸው ቀዳሚዎቹን አሃዳዊ ስርዓቶች ከመናፈቅ የመጣ አሊያም ህገ -መንግስቱን ቀድዶ ለመጣል ከመፈለግ የመነጨ መሆኑ ግልፅ ነው።

እንዲያውም የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሁለንተናዊ መብቶች የአንድነታችን ዋስትና እንጂ የመለያየታችን ስጋት ሊሆኑ አይችሉም። ይህ አንቀፅ የሌላቸው አንዳንድ ሀገራት በብጥብጥና በሁከት እየታመሱ ያሉትም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን ማምጣት ባለመቻላቸው ይመስለኛል።

የአገራችን ፌዴራሊዝም የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያለምንም ገደብ ያረጋገጠ ቢሆንም ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን በሀገሪቱ ላይ ለማምጣት እንደሆነ መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ የምንከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት አባሎቹ የሚናቆሩበትና የሚባሉበት ሳይሆን አብረው በፈቃዳቸው በጋራ የሚያድጉበት ስርዓት መሆኑ ልዩ ባህሪው ነው።

የህገ- መንግስቱን መግቢያ ቆንጥረን ብንወስድ እንኳን “…ጥቅማችንን፣ መብታችንንና ነጻነታችንን በጋራና በተደጋጋፊ ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…” የሚለው ሃሳብ የፌዴራላዊ ስርዓቱ መገለጫ ህብረ – ብሔራዊነት ብቻ ሳይሆን መተጋገዝም ጭምር መሆኑን አመላካች ነው።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነታቸው የስጋት፣ የአደጋ ብሎም የጦርነት ምንጭ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ በመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት ጥላ ስር ሆነው በአስተማማኝ የሰላም ጎዳና ላይ መጓዝ ከጀመሩ እነሆ 23 ዓመታትን አልፈዋል።

በድላቸው ባረጋገጡት አስማማኝ ሰላምም፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ- መንግስቱ ዓላማ ጥላ ስር ሆነው የልማት ተጠቃሚነታቸውን በየደረጃው ይበልጥ ዕውን እያደረጉ ይገኛሉ። ይህም የራሳቸውን መብት በራሳቸው በማረጋገጥ ለአገራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል። ይህን እውነታ ኢትዮጵያን የጠቀማት እንጂ የጎዳት አለመሆኑን ከፅንፈኝነትና ከትምክህተኝነት አስተሳሰብ ወጣ ብሎ መመለክት የሚገባ ይመስለኛል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ሁሉ ይወጣሉ። በርዕሰ መስተዳድርነታቸው የአገሪቱ አስፈፃሚ አካል የበላይ እንዲሁም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በመሆናቸው የአገሪቱን ተቋማት ሁሉ በበላይነት የሚመሩ ናቸው። የደህንነቱም ይሁን የመከላከያ ተቋማት ለእርሳቸው ታዛዥ ናቸው። ጽንፈኞችና ትምክህተኞች ግን በቀን ቅዠታቸውን ህዝቡን ለማደናገር ያልተገባ ስያሜ በመስጠት ከወዲሁ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አሰራር ለማጠልሸት እየሞከሩ ነው። ይህን እውነታ ህዝቡ መገንዘብ አለበት።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሚያስፈፅሙት የድርጅታቸውን መስመር ነው። የኢህአዴግ መስመር ደግሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሲሆን፤  የተፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮችን እየፈቱ ይህን መስመር አጠናክረው በመቀጠል የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን እንደሚያደርጉ ፅንፈኞችና ትምክህተኞች ሊገነዘቡት ይገባል። ከቀን ቅዠታቸውም መውጣት ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy