Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የቀዩ መስመር” ቅላት

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የቀዩ መስመር” ቅላት

                                                      ዘአማን በላይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካቢኔያቸውን በአዲስ መልክ ሲያዋቅሩ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት ካቢኒያቸው ማለፍ የማይገባውን “ቀይ መስመር” ግልፅ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔው አባላት የአቅም ክፍተት ካለባቸው ጉዳዩ በሂደት መስተካካል የሚስተካከል ቢሆንም፣ “ቀይ መስመሩን” የሚያልፉ በትዕግስት እንደማይታለፉ አሳስበዋል። ይህ “ቀይ መስመር” ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በፅናትና በቁርጠኝነት አለመታገል ነው።

በሚኒስትርነት የተሾሙት አመራሮች በሙስና ከተዘፈቁ፣ በሚመሯቸው መስሪያ ቤቶች ውስጥ ሙስናን ለማስወገድ ካልጣሩ እንዲሁም አስተሳሰቡንና ተግባሩን ለማስወገድ የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት ተግባሩን ለመቀነስ ካልሰሩ “የቀዩ መስመር” ጉዳይ መነሳቱ አይቀሬ ነው። “ቀይ መስመሩ” ይበልጥ ይቀላል። ሙስናን መጠየፍ፣ ብክነትን ማስወገድ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎትን መስጠት እንዲሁም ተገልጋይን ማክበርና ሌሎች ሰናይ ተግባሮችን አለማከናወን “ቀዩን መስመር” ይበልጥ ያቀላዋል። እናም አዲሱ ካቢኔ ድርድ ድርብርብ ኃላፊነት ፊት ለፊቱ ተደቅኖ የሚጠብቀው አመራር ነው ማለት ይቻላል። ነባሮቹ የካቢኔ አባላትም እንዲሁ።

የ“ቀይ መስመሩን” ቅላት ይበልጥ የሚጨምረው አንዱ የሙስና አስተሳሰብና ተግባር ነው። ሙስና መቀበል ብቻ አይደለም። መስጠትንና የደላላዎችን እንቅስቃሴንም ይጨምራል። አላግባብ በስልጣን ለመገልገል መፈለግንም ያካትታል። ሙስና በመጠቃቀም የትስስር ሰንሰለት (patronage network) ሊቆራኝ አሊያም በተናጠል ሊከናውን ይችላል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ካቢኔ ይህን ጥቂቶች “የሚነግሱበትንና” አብዛኛውን ዜጋ የበይ ተመልካች እንዲሆን የሚያደርግን የለየለት ዘረፋ በቁርጠኝነትና በጽናት በመታገል ብሎም በማታገል ያለማወላወል ሊታገሉት ይገባል። ታግለውም በማታገልም ከየስራቸው ባህሪ አኳያ ለውጥ ማምጣት የሚገባቸው ይመስለኛል።

የሙስና አስተሳሰብና ተግባር በማንኛውም ሀገር ውስጥ ነባራዊ ክስተት ነው። ሊቀር አይችልም። በዓለም ላይም ቢሆን ዜሮ በመቶ (0%) የደረሰ ሙስና የለም። በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ በመሆኑ፤ ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳና ጉድለቶች የማይኖሩት “ሙሉዕ ነው” ተብሎ የማይታሰብ ብቻ አይደለም። ካለፍንባቸው ስርዓቶች ምልከታና በሀገራችን ውስጥ የተፈጠረው ዕድገት እንዲሁም ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ መንግስት የሚያከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ሙስና እንዲገነግን ምክንያት ሆኗል።

እንደ እኛ በማደግ ላይ የሚገኝ ሀገር ሙስናን ያለ ርህራሄ መዋጋት ካልቻለ፤ እመርታው የቁልቁለት ላይ ሸርተቴ መሆኑ አይቀርም። ዕድገቱ እንደ ካሮት ቁልቁል ይሆናል። ይህም ፍትሐዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ደብዛውን በማጥፋት የህዝብን ምሬት ማናሩ አይቀርም። ምሬት በበዛ ቁጥር ደግሞ እንዳለፍንባቸው ሶስት ዓመታት ሰላማችን አደጋ ላይ ይወድቃል። የሰላም አደጋ ላይ መውደቅም፤ የሰው ልጅን ህይወት ይቀጥፋል፤ አካልን ያጎድላል፤ ንብረትን ያወድማል። በአላስፈላጊ ትርጉም ሳቢያ ዜጎችን እንዲጋጩ ያደርጋል። በሰላም ወጥቶ መግባት ወደ ‘ነበርነት’ ይቀየራል።

ምን ይህ ብቻ— አንድነትም ይናጋል። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማሰብ ቀርቶ፣ ሁሉም በየፊናው ተለያይቶ እንደ ባቢሎን ግንብ ገንቢ “ውሃ” ሲባል “እሳት” አቀባይ ይሆናል። ቋንቋውና ኢትዮጵያዊ ዘዬው ይጠፋል።…ሌላ ሌላም ሀገራዊ ጣጣዎችን ይፈጥራል። በእኔ እምነት ሙስና የ“ቀዩ መስመር” ቅድመ ሁኔታ ሆኖ የሚታየው ከእነዚህ ሀገራዊ እውነታዎች በመነሳት ይመስለኛል። ዕይታው ተገቢ በመሆኑ የካቢኔው አባላት ይህን “ቀይ መስመር” ሳያልፉ የሙስናን አስተሳሰብና ተግባርን ለመቅረፍ በሚደረገው ሀገራዊ የለውጥ ጥረት ውስጥ ፋና ወጊ ሆነው በቁርጠኝነት መሰለፍ ይኖርባቸዋል።

አዲሶቹ ሚኒስትሮች ማንኛውም የፀረ-ሙስና ትግል የፖለቲካ ትግል መሆኑን በመገንዘብ ከየተመደቡበት የስራ ስምሪት አኳያ ጉዳዩን መፈፀም ያለባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም የሙስና ተግባር በአንድ ሀገር ህዝብና መንግስት ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ በቀጥታ ከስርዓቱ ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ አሰራር ጋር የሚገናኝ ስለሆነ ነው። እንዲሁም አስተሳሰቡና ተግባሩ በአመዛኙ በአንድ ሀገር የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ትግሉን ፖለቲካዊ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኒያቸውን ሲያዋቅሩ ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብተው ይመስለኛል።

ርግጥ ስርዓቱ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ፤ አመለካከቱና ተግባሩ የስርዓቱን ፍላጎት በመፃረር የሚስፋፋ ከሆነ የተገነባውን መናዱ አይቀርም። ይህም ስርዓቱን የገነባው መንግስት ለህዝቡ “በለውጥ ሂደት ላይ ነኝ፤ ግን ትዕግስት ያስፈልጋል” በማለት ለህዝቡ የገባውን ቃል በአስተማማኝ ሁኔታ እንዳይፈፅም እንቅፋት ይሆናል። በሌላ አገላለፅ፤ ስርዓቱ ይበልጥ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳይሆንና በህዝቡ ዘንድም አመኔታ እንዲያጣ ምክንያት ይሆናል።

ስለሆነም ከሙስና ጋር የሚደረገው ትግል ፖለቲካዊ መሆኑ የግድ ይመስለኛል። የካቢኔ ሹመት ፖለቲካዊ እንደመሆኑ መጠን፤ ሚኒስትሮቹ ሙስናን መዋጋት የሚኖርባቸው ከዚህ እውነታ ተነስተው ነው። ይህን ሲከውኑም “ቀዩ መስመር” ሳይቀላ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ከስርዓቱ ፍላጎትና ከህዝቦች አመኔታ አኳያ በብቃት ሊወጡ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።

በእኔ እምነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካቢኔ የገዥው ፓርቲ መገለጫ ነው። እንደሚታወቀው ኢህአዴግ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ አባላቱን በኃላፊነት ላይ የሚያስቀምጣቸው፤ በግልፅ መርህ ላይ የተመረኮዘ ባህል በመመራት ነው። ብቃት ያለውና ስራውን ይመጥናል የተባለ ማንኛውም አባል በድርጅቱ እስከታመነበት ድረስ በተፈላጊው ቦታ ላይ ሊቀመጥ ይችላል። ጉዳዩ ከግለሰባዊ ፍላጎት ሳይሆን፣ ከድርጅታዊ የስራ ስምሪት አኳያ የሚታይ ነው። ይህ የስራ ስምሪት ሙስናን ለማዳከም ጠንካራ አቋም የያዘ ብቻ ሳይሆን፣ “ከቀይ መስመር” ማለፍና አለማለፍ ጋርም ተያይዟል። የካቢኔው አባላት “ቀይ መስመሩን” ሳያልፉ ወይም እንዲቀላ ሳያደርጉ ሀገራቸውን የማገልገል ኃላፊነትና ግዴታቸውን በታማኝነት ይወጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

“ቀዩ መስመር” እንዳይቀላ የህዝቡን ምሬትና እሮሮ መቀነስ ብሎም ማስወገድ ያስፈልጋል። በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚታዩ የስልጣን አጠቃቀምና የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታን መፈተሽ ይገባል። የፍተሻው ቀንዲል አዲሶቹ ሚኒስትሮች መሆን አለባቸው። በየመስሪያ ቤታቸው በየደረጃው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች ‘ወንበር’ ላይ የተቀመጡት ህዝብን ለማገልገል እንጂ በህዝቡ ለመገልገል አለመሆኑን የበጠ እንዲገነዘቡ ማድረግ ይገባል። ስልጣን ህዝብን መጥቀሚያ እንጂ የተሿሚዎች የኑሮ ማደላደያ እንዳልሆነ አሁንም በግልፅ ማሳወቅ ያስፈልጋል። “ቀይ መስመር” እንደሆነም እንዲሁ። በእኔ እምነት አዲሶቹ ሚኒስትሮች በየስራ ስምሪቶቻቸው ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ብልሹ አሰራሮችን ከህዝቡ ጋር ሆነው ቢሰሩ ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ይችላሉ።

ማንኛውንም ስራ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ዕውን ሊሆን አይችልም። ስለሆነም ከህዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ህዝቡን አማክለው በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል። ቅንጅታዊ አሰራር በመመካከር ላይ ተመርኩዘው የሚሰሩ በመሆናቸው የሚታዩና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ በመቅረፍ ረገድ የላቀ ሚና አላቸው። ህዝቡ የሚገለገልበትን ተቋም የራሱ አድርጎ ስለሚቆጥረውም በተቋሙ ላይ የሚታዩ ህፀፆችን አስቀድሞ በማረም የበኩሉን ሚና ይጫወታል። ይህም በየቦታው የሚስተዋሉ ህዝባዊ ምሬቶችን ከማስቀረት ባለፈ፤ የዚያን መስሪያ ቤት ተግባር ያሳልጣል። “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ አበው።

በየደረጃው ያለ አመራርም ሆነ ሰራተኛ ለማን ተጠሪ እንደሚሆን፣ የተጠያቂነት ሁኔታውንና የዕዝ ሰንሰለቱን ተገንዝቦ ስለሚሰራ በስራው ላይ ውጤታማ መሆኑ አይቀርም። ስለሆነም ይህን ቅንጅታዊ ስራና የተጠያቂነት መንፈስን የሚያጎለብት ስለሆነ፤ በተለይ አገልግሎት ሰጪ በሆኑ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ስራን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙ ሚኒስትሮች፤ ለታይታ ሳይሆን ከምር ህዝብን በማማከር መስራት የሚኖርባቸው ይመስለኛል። “ቀዩ መስመር” ከቅላቱ ባሻገር ይህን መሰል ጠቀሜታን የሚያጎናፅፍ መሆኑንም እግረ መንገዱን መረዳት አስፈላጊ ይመስለኛል።

ስለሆነም በእኔ እምነት የእያንዳንዱ አስፈፃሚ መስሪያ ቤት የምደባ መስፈርት በሰራተኛውና በህዝቡ በግልፅ እንዲታወቅ ብቻ ሳይሆን፣ የመስሪያ ቤቱ ባለቤት የሆነው ግብር ከፋዩ ህዝብ እንዲተችበት ማድረግ ይገባል። ይህም በህዝብና በመንግስት መካከል ማናቸውን ተግባራት ተመካክሮ ለመስራት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፤ ህዝቡ በመንግስት ላይ ይበልጥ አመኔታ እንዲያሳድር የሚያደርግ ነው።

“የቀዩ መስመር” መቅላትና አለመቅላት የሚወሰነውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ “መስመሩ” ጋር ሳይደርስ በግንባር ቀደምትነት በሚያከናውናቸው ሀገራዊ ኃላፊነቶች የሚወሰን ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን ከፍተኛ የመነቃቃት ስሜት አጎልብቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ነበርንበት አስተማማኝ ቦታ ለመመለስ ተሿሚዎችም ይሁኑ ህብረተሰቡ “ከቀዩ መስመር” ወዲህ በትጋት መስራት ይኖርባቸዋል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy