Artcles

…የበላይም ሆነ የበታች ህዝብ የለም!

By Admin

April 12, 2018

…የበላይም ሆነ የበታች ህዝብ የለም!

ገናናው በቀለ

ህዝብ እንደ ህዝብ የበላይ ወይም የበታች ሊባል አይችልም። ሁሉም ህዝብ እኩል ነው። የአንድ ብሄር የበላይነት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ የለውም። በተለይ የትግራይ ተጠቃሚነት አለ እየተባለ በተሳሳተ ግንዛቤ ሳቢያ የኢኮኖሚ- ፖለቲካ ወደ ወለደው ግጭት የማምራት አዝማሚያዎች መስተዋላቸው ተቀባይነት የለውም። የትግራይ ክልል እንደ ማንኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ የመሰረተ ልማት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ይህን እውነታም በቅርቡ በመቐለ በተካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ ተሳታፊዎች ሲናገሩና ትዝብታቸውን ሲገልፁ በመገናኛ ብዙሃን ተከታትያለሁ።

እርግጥም እዚህ አገር ውስጥ የበላይም ይሁን የበታች ህዝብ የለም፤ ሊኖርም አይችልም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች በፍትሐዊ ተጠቃሚነትና በእኩልነት መንፈስ እያደጉ የሚገኙ እንጂ፤ አንዱ የበላይ ሌላው ደግሞ የበታች እንዲሆን የሚፈቅድ አይደለም።

የትግራይ ክልል ህዝብ የአኗኗር ዘይቤ እጅግ አሳዛኝ ነው። ምንም እንኳን አካባቢው ለእርሻ የሚመች ባይሆንም፤ አርሶ አደሩ በላቡ ጥሮ ግሮ የሚኖር ነው። እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ አርሶ አደር አፈር ምሶ ድንጋይ ንዶ የሚኖር ህዝብ ነው። እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል በዚያ ክልልም ዛሬም ድህነት አለ። ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው። ሆኖም ህዝቡ ታታሪና ከተፈጥሮ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ የሚኖር በመሆኑ በተለያዩ ስራዎች አካባቢውን እየለወጠ ነው።

ያም ሆኖ ክልሉን የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የክልሉን ህዝብ ከደርግ የአፈና እና አምባገነናዊ አገዛዝ ቢያላቅቀውም፤ የህዝቡን ኑሮ በመሰረታዊነት የለወጠለት አይመስለኝም። እንዲያውም ባለፉት ዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግርና ‘የኔት ወርክ ትስስር’ በከፋ ሁኔታ ከሚታይባቸው የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ አንዱ የትግራይ ክልል መሆኑን አንድ ጥናት ማረጋገጡን በመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርቦ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ሌላው ቀርቶ የህወሓት የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ እንደሚያመለክተው፤ በክልሉ ውስጥ የከፋ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ የቡድንተኝነት ስሜት እንዲሁም ቀደም ሲል የነበሩ የህዝባዊነት መንፈስ መቀዛቀዝና የአደርባይነት መገንገን መፈጠራቸውን በግልፅ አመልክቷል። ይህም በትግራይ ውስጥ ምን ያህል የከፋ የአስተዳደር በደል እንዳለ የሚያሳይ ይመስለኛል። ለዚህ ችግር ተጠያቂው የክልሉ ከፍተኛ አመራር መሆኑ ግልፅ ነው።   

የትግራይ ህዝብ አንደ ማንኛውም ለኢትዮጵያዊያን ክብርና ፍቅር ያለው ነው። ያ ህዝብ ድህነት ይዞት ነው እንጂ፣ ምንም ነገር ከመስጠት የሚቆጠብ አይደለም። የሌላውን ባላውቅም እኔ በበኩሌ በኢትዮጵያዊነቴ የምኮራው ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሳቀና ነው። ያኔም የትግራይ ህዝብ ትዝ ይለኛል። እናም በዚያ ታታሪና ኢትዮጵያዊ ህዝብ መሃል ሁሌም ብገኝ ደስታዬ ወደር አይኖረውም።

እኔ እስከማውቀው ድረስ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበላይ ሆኗል ከተባለ፤ ምናልባትም በዚያ ክልል በሚታየው የከፋ ድህነትና ለሌሎች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለው ወደር የለሽ ፍቅር ብቻ ነው። በተረፈ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በልጦ ከፌዴራል መንግስት የሚመደብለት ሰባራ ሳንቲም የለም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች የሚሰጠውና ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ገቢራዊ የሚሆነው የበጀት ቀመር ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይፋ አድርጎ ነበር። በወቅቱ ምክር ቤቱ እንደገለፀው፤ ክልሎች የሚያገኙት ድጎማ የተለያዩ ጉዳዩችን ታሳቢ ያደረገ ነው። እነርሱም ለሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት፣ ለጤና፣ ለውሃ፣ ለከተማ ልማት፣ ለትምህርት፣ ለገጠር ልማትና ለመሳሰሉት የወጪ ፍላጎቶች ናቸው። እንዲሁም የክልሎች ገቢ የማመንጨት አቅም ሌላው የበጀት ቀመሩ መመዘኛ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ መሰረትም የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የኢትዮጰያ ሶማሌ ክልሎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ አራተኛ ድረስ ድጎማ አግኝተዋል። በአምስተኛ ደረጃ ድጎማ ያገኘው የትግራይ ክልል ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የቀመሩ ዋነኛ ጉዳይ የሆነው የህዝብ ብዛትና ቀደም ሲል የገለፅኳቸው ሌሎች ፍላጎቶች አኳያ የተቃኘ ስለሆነ ነው። እርግጥ ክልሎች የራሳቸውን በጀት በአግባቡ ህዝቡን ባማከለ መንገድ አብቃቅተው መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ይህን ሳያደርጉ ቀርተውና በጀቱም በኪራይ ሰብሳቢዎች ተዘርፎ ሲያበቃ፤ ህዝቡ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይን ካነሳ ችግሩ የሚኖረው በራሳቸው በክልሎቹ ጫንቃ ላይ ብቻ ነው። ሌላው ክልል ባላየውና ባልሰማው ምክንያት ጣት መቀሰሪያ ሊሆን አይገባውም።   

ያም ሆነ ከላይ ያነሳሁት ማሳያ እዚህ አገር ውስጥ የበላይ ወይም የበታች ህዝብ እንደሌለ አስረጅ ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይም ይሁን የሌላ ብሔርና ብሔረሰብ የበላይነትም ይሁን የበታችነት የለም። ሊኖርም አይችልም። በስርዓቱ ውስጥ አንዱ “ልጅ” ሌላው ደግሞ “የእንጀራ ልጅ” የሚሆንበት ህጋዊ አሰራር የለም።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም የሀገራችን ህዝብ በፍትሃዊነት እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታን የፈጠረች እንጂ፤ አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች በማድረግ የምታበላልጥ  አይደለችም። ጭቆናን፣ ኢ-ፍትሃዊነትንና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን ሲታገሉ የመጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ምንም ዓይነት ቦታ የላቸውም። እንደ ሌሎቹ ህዝቦች ሁሉ የትግራይ ህዝብም ከዚህ የተለየ ምልከታ የለውም። እናም የበላይም የበታችም ሊሆን አይችልም።

ታዲያ እዚህ ላይ በየብሔሩ ውስጥ ጥገኞች የሉም ማለት አይቻልም። ልክ በኦሮሞ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በጋምቤላ ወይም በሌሎች የሀገራችን ብሔሮች ስም የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ጥገኞችና ኮንትሮባንዲስቶች እንዳሉት ሁሉ፤ በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግዱ ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች መኖራቸው አይቀርም።

እነዚህ ጥገኞች ግን የትግራይንም ይሁን ሌላውን የአገራችንን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ጥገኞቹ በዜሮ ድምር የፖለቲካ ስሌት የሚንቀሳቀሱ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው። ጥገኞቹ በሀገራችን ህዝቦች ስም እየማሉ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ኮንትሮባንዲስትነትን የሚያካሂዱ “ነጋዴዎች” ናቸው። እነዚህን ሃይሎች ከህዝብ መለየት ይገባል። እነርሱ ሊጠየቁ የሚገባቸው በራሳቸው ተግባር እንጂ ህዝቡን በመወከል አይደለም። የየትኛውም ሀዝብ ውክልና ያላቸው አይደሉምና።  

ይህን መሰሉን የህዝብ ጥላቻን ለማንገስ የሚሯሯጡት ፅንፈኞች ናቸው። ፅንፈኞቹ መቼም ቢሆን ምንም ነገር ከማውራት የሚመለሱ አይደሉም። የትግራይ ሀዝብን በማያውቀው ጉዳይ የሚያጠለሹት ፅንፈኞች ህዝቡን ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ማጋጨት ከቻልን ስርዓቱን ማፍረስ እንችላለን ብለው የሚያምኑ ቀቢፀ-ተስፈኞች ናቸው።

አዲሲቷ ኢትዮጰያ የተገነባችበት ስርዓት ግን በድቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አይደለም። መላው የሀገራችን ህዝቦች አንደ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት በፈቃዳቸው ያቋቋሟትና ጠንካራ መሰረት ያላት ቤታቸው ናት። በአሉባልታ የምትፈርስ አይደለችም። እናም በህዝቦች በጎ ፈቃድ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው ህገ መንግስታዊው ስርዓት በእኩልነትና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚመራ እንጂ የትኛውንም ህዝብ የበላይ አሊያም የበታች የሚያደርግ አለመሆኑን የትኛውም ወገን ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል።