NEWS

 የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጣናን ከእንቦጭ ለመታደግ የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ወሰነ።

By Admin

April 15, 2018

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጣናን ከእንቦጭ ለመታደግ የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ወሰነ።

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አለምነው መኮንን ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ማዕከላዊ ኮሚቴው ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባው ጣናን ከእንቦጭ የመታደግ ሀገራዊ ሀላፊነት ላይ በመምከር የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ውሳኔ ማሳለፉን ገልፀዋል።

አቶ አለምነው፥ ብአዴን ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ልማት በተለይም በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ ውስጥ ወንዞችን የመንከባከብና በዘላቂነት ለልማት የማዋል ስራ ላይ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ በውሃ ሀብት እንክብካቤ ረገድ የታላላቅ ወንዞችንም ሆነ ሌሎች ገባር የሆኑ ወንዞች ምንጮች እና ሀይቆች እንዲጠበቁ እና በዘላቂነት ከብክለት፣ ከደለል እና ከተለያዩ መጤ አረሞች እንዲጠበቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተው እና እየተስፋፋ የመጣውን የእንቦጭ አረምንም ለመከላከል ህብረሰተሱ የተለያዩ ስራዎችን በጉልበት ሲሰራ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ አለምነው፤ ይህ ያስገኘው ውጤት አንዳለም ይናገራሉ።

አረሙ በሀይቁ ላይ እንዳይስፋፋ እና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስም ህብረተሰቡ በቀናነት እና በሀገር ፍቅር መንፈስ ላደረገው ብርቱ ጥረተም ብአዴን እና የክልሉ መንግስት ምስጋናውን እንደሚያቀርብም ገልፀወዋል።

በቀጣይም ይህ ጥረት ፍሬያማ ውጤት እንዲያመጣ በቅርቡ የጣና ፈንድ የሚል ድርጅት መቋቋሙን ያነሱት አቶ አለምነው፤ አረሙን ለማስወገድም በፈንዱ አማካኝነት ገንዘብ እየተሰባሰበ ይገኛል ነው ያሉት።

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ለሁለት ቀናት ባደረገው ስብሰባም የጠና ጉዳይ ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልገዋል የሚለው ላይ መወያየቱን አቶ አለምነው ጠቅሰዋል።

በዚህ በመነሳትም አረሙን በማሽን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን የተረዳው ማእከላዊ ኮሚቴው የ10 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኑንም አስታውቀዋል።

የገንዘብ ድጋፉም በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን አምቦጭ አረም ለማስወገድ የሚረዳ ዘመናዊ ማሽል ለመግዛት የሚውል መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል።

በውሳኔውም መሰረት ለአማራ ክልል አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን 10 ሚሊዮን ብር ቼክ ርክክብ አድርጓል፡፡

አቶ አለምነው አያይዘውም፥ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰሞኑ በኢህአዴግና ብአዴን ደረጃ የተከናወኑ ውይይቶች የደረሱበትን ክንዋኔ አስመልክቶ ከሚያዝያ 4 ጀምሮ ለ2 ቀናት መወያየቱን አንስተዋል።

ለሁለት ከናት በተካሄደው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ሀገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት መምከሩን ያነሱት አቶ አለምነው፥ ማእከላዊ ኮሚቴው ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ውይይትም ማጠናቀቁን አንስተዋል።