CURRENT

 የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደስታ መግለጫ ልከዋል።

By Admin

April 12, 2018

የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደስታ መግለጫ ልከዋል።

የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አልዎት መልእክት ከላኩት መሪዎች ውስጥ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በመልእክታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በተጨማሪም የአልጀሪያው ፕሬዚዳንት አብድላዚዝ ቡቶፍሊካ፣ የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ፣ የብራዚል ፕሬዚዳንት ማይክል ቴመር፣ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓውሎ ጌንቲሎኒ፣ የኔዘርላንድሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ፣ የሞሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ያህያ ኦልድ ሃዴማይ እና የጆርጂያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂ ክቭሪካሽቪሊም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የደስታ መግለጫ ልከዋል።

መሪዎቹ በመግለጫቸው ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለፁ ሲሆን፥ በቀጣይም በኢትዮጵያ እና በሀገራቸው መካከል ያለን ግንኙነት ለማጠናከር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር በቅርበት እንሰራለን ብለዋል።

የአልጄሪያው ፕሬዚዳንት አብድላዚዝ ቡቶፍሊካ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ እና በአህጉሩ ሰላምና ልማት ላይ ለመስራት ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀል ገልፀዋል።

የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉም እንዲሁ፥ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብሮች የበለጠ እንዲጠናከሩ እና በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን በጋራ እንሰራለን ብለዋል::

የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ በበኩላቸው፥ 700 ሚሊየን ዩሮ ኢንቨስት ያደረጉ 130 የሀገሪቱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መኖራቸወን ጠቅሰው፤ እነዚህም 75 ሺ የስራ እድል የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ የኢኮኖሚ ትስስር ከዚህ በበለጠ እንዲጠናከር እንሰራለን ብለዋል፡፡

የሞሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ያህያ ኦልድ ሃዴማይንም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጤንነትንና ስኬታማ የስራ ዘመንን መመኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።