Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

                 የትናንቱ ስህተት አይደገምም

0 379

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

                 የትናንቱ ስህተት አይደገምም

ዋኘው መዝገቡ

በአገር ደረጃ ተከስተው የነበሩት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውሶች ሕዝብን ከፍተኛ ስጋትና ጥርጣሬ ውስጥ ከተውት  ነበር፡፡ የሙስና የመልካም አስተዳደር የፍትሕ የመሬት ቅርምት ችግሮች ሞልተው በመፍሰሳቸው በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነግሶ ነበረ ቢሆንም ዛሬ የተሻለ ሀገራዊ ተስፋ በማንሰራራት ላይ ይገኛል፡፡

ኢሕአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲ ችግሮቹን በተለያየ ደረጃ በመገምገም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ቢሆንም ይህን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ሳይችል የቆየበት ሁኔታ ነበር፡፡በተወሰነ ደረጃ እርምጃዎች ለመውሰድ የተሞከረበት ሙሰኞች የታሰሩበት ሁኔታ ቢኖርም ይህም የተፈለገውን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ሳያስችል ቆይቶአል፡፡

የችግሩ መስፋትና ጥልቀት የሕዝብ ቁጣን አስከትሎ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ብዙ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡የመንግስትና የሕዝብ ንብረቶች ወድመዋል፡፡ የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ሕይወት ጠፍቶአል፡፡ሁኔታው አጅግ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ ለማምጣት ሳያስችል የቀረው በራሱ በመንግስት ውስጥ በተሰገሰገው የኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ነበር፡፡

የውስጥ ችግሩን ለመፍታት የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዳግም ጥልቅ ግምገማ በማድረግ ትክክለኛ መንስኤውን አበጥሮ በመፈተሸ እያንዳንዱ አባል ድርጅት ውስጡን በሚገባ እንዲያጠራ በማድረግ የተወሰኑ ለውጦች ቢገኙም በብሔራዊ ደረጃ ላለው የገዘፈ ችግር መፍትሄ ማስገኘት ግዜ ወስዶአል፡፡

እንደገናም ረዥም ቀናት ወስዶ ስራ አስፈጻሚው በመወያየት በግልጽ ለተፈጠሩት ሀገራዊ ችግሮች ሁሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ የተበደለውን ሕዝብ እንደሚክስ በውስጡም ለውጥ እንደሚያደርግ መግለጹ ተስፋን ፈጥሮአል፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ የተነሳው የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልል ድንበር ነዋሪዎች መካከል የተከሰተው ግጭትና መፈናቀል የሰው ሕይወት መጥፋት እጅግ  ከፍተኛ መሆኑ ይህንን ተከትሎም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በአማራው ክልል የተከሰተው ተቃውሞ መቀጠል በሕይወትና በንብረት ላይ ያስከተለው ጥፋትና ውድመት ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋቱን ያደፈረሰ የዜጎችን ሰላማዊ ሕይወት ስጋት ውስጥ የከተተ አደጋ ደቅኖ ቆይቶአል፡፡

የሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት መደፍረስ፤ የዜጎች ሰላም ወጥቶ ሰላም መግባት ጥያቄ ውስጥ መውደቁ፤በንግድ ልውውጡና ዝውውሩ በአጠቃላይ በሕብረተሰቡ ማሕበራዊ ሕይወትና መስተጋብር፤በመንግስት ተቋማት ስራዎች፤ በግሉ ኢኮኖሚ፤ በኢንቨስትመንት በቱሪዝም ስራዎች በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጫና አሳድሮአል፡፡

የተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የንግዱም ሆነ የኮንስትራክሽን ስራዎች መዳከም የተጀመሩ ግንባታዎች መቋረጥ በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ዛሬ ኢሕአዴግ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጡን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጰያ አንድነት ላይ ያተኮረ ንግግር፤ ዘረኝነትን ከኢትዮጰያ ምድር እንዲጠፋ እንሰራለን፤ ሙስናን እንዋጋለን፤ጥቂቶች በዘረፋ የሚከብሩባት ሀገር አትሆንም፤ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር እናደርጋለን በሚል ያደረጉት ንግግር  በሕዝቡ ውስጥ ታላቅ ሰላምና መረጋጋት ፈጥሮአል፡፡

ድሕነትን ተዋግተን ማሸነፍ ሲገባን እርስ በእርስ መጋጨቱ ትርጉም የለውም፤ባለን ላይ መደመር ካልሆነ በስተቀር መለያየቱ መጠፋፋቱ ለማንም አይጠቅም በሚል የተናገሩት  ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔና ገናናነት በማውሳት የበለጠ የታፈረች የተከበረች ያደገች የለማች ሀገር እንድትሆን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡   ይህ ንግግራቸው ሕዝቡ ውስጥ ጠልቆ በመግባቱ ሰፊ ሀገራዊ ሰላም ሰፍኖአል፡፡የደፈረሰው ሰላም ሙሉ በሙሉ ተረጋግቶአል፡፡

ካለፉት ስህተቶች በመማር ሀገራዊ ውድቀት ሊያመጣብን ከጫፍ ደርሶ የነበረው ሁኔታ በመታጠፉ መንግስት የሕዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ በተግባር እንዲመልስ ዜጎችም የየግላቸውን ድርሻ በከፍተኛ ሀገራዊ የፍቅር ስሜት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም መንግስት እንደ መሪ ይምራ እንጂ  የሀገሪትዋ ባለቤት በመልካም ውጤቶች ተጠቃሚው በሚከሰቱ ችግሮችም ተጎጂው ሕዝቡ ስለሆነ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ሂደት የተሻለች የለማች የበለጸገች ሀገር እንገነባለን፡፡

ከስህተቶቻችን እየተማርን በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ እየሰራን በአዲስ የስራ ሂደት ውስጥ ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮችም አስቀድሞ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እየተከላከልን የሁላችንም የጋራ መኖሪያና መከበሪያ የሆነችውን ሀገራችንን መጠበቅ ማልማት ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡መንግስት እንደ መንግስት ይመጣል ይሄዳል፡፡ሀገር ግን ዝንተ አለም ሕያው ሁና ትቀጥላለች፡፡

በአመራር ላይ በነበሩ ግለሰቦች በሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮች በሀገር ላይ ተስፋና እምነት መቁረጥ አይቻልም፡፡ከግለሰቦች ከቡድኖች ጊዜያዊ የጥቅም ፍላጎትና ሽኩቻ በላይ ሀገር ትቀድማለች፡፡

የሀገርን ሰላም መጠበቅ ለሀገር ክብርና ደሕንነት መቆም የሚከሰቱ ችግሮችን ሁሉ በሰላምና በውይይት በመነጋገር መፍታት በጋራ በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በአንድነት ቆሞ መስራት ከጥፋትና ከውድመት ድርጊቶች መታቀብ በዋናነት የሚጠቅመው ለሀገርና ለሕዝብ ነው፡፡

ሀገሪቷ የገነባቻቸው ፕሮጀክቶች ልማቶች ሀብቶች መንገዶች ድልድዮች ፋብሪካዎች ማሽነሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች የምንገለገልባቸው መኪኖች፤ ሆስፒታሎቻችን ክሊኒኮች፤አምቡላንሶች፤የእርሻ መሳሪያዎች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች ወዘተ ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ትውልድ የሚጠቅሙ ታላቅ ሀገራዊ ሀብቶች ናቸው፡፡

በምንም አጋጣሚ በሚፈጠር ችግር በእብደትና በስሜታዊነት በመነሳት ሊቃጠሉ ሊወድሙ ሊነዱ አይገባቸውም፡፡ ነገም ሌላ መንግስት ቢመሰረት የሚጠቅሙት ለሀገርና ለሕዝብ ነው፡፡ባለን ላይ እየጨመርን መሄድ ሲገባን የገነባነውን እያወደምን እያፈረስን ሌላ ግንባታ ማድረግ አይታሰብም፡፡ከስህተቶቻችን መማር ይገባናል፡፡

ከጥላቻ ወጥተን ሀገራችንን የፍቅር የመቻቻል ቀደምት ተምሳሌነትዋን ደግመን ለአለም ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ አለመታደል ሁኖ እንጂ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ከሚባሉትም ቀደምት ሀገራት ተርታ የምትጠቀስ የጥንታዊ ስልጣኔም ባለቤት የነበረች የሆነችም ሀገር ናት፡፡ መጠፋፋቱ መበላላቱ አልጠቀመንም፡፡ ዘረኝነትና መከፋፈልን ከሀገራችን ምድር ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አለብን፡፡ሀገራዊ ውድቀት ከማምጣቱ ሀገሪቱንም ለውጭ ጠላቶች አሳልፎ ከመስጠትና በር ከመክፈት ውጪ የሚጠቅመን አንዳችም ምንም ነገር የለም፡፡

ከብረት የጠነከረ ሀገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ማድረግ፤ በኢኮኖሚ እድገቷ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰች ሀገር መገንባት፤ በሕዝቡ ውስጥ ያሉትን ለዘመናት የኖሩ ባሕላዊ እሴቶቻችንን አጥብቀን መጠበቅ ሁሉም ዜጋ በተሰለፈበት መስክ ለስራ መትጋት ሀገሩን ወደ ላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት ማድረግ የበለጠ  ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy