የአሰያየሙ ሒደት
ደስታ ኃይሉ
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሰየሙበት ሂደት ግልፅና ቀጥተኛ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ነው። በተለይ በቅድሚያ የመሪው ድርጅት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ እንዲሁም ኋላ ላይ የድርጅቱ ማዕከላዊ ምክር ቤት ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲል ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል አንዱ ነበር። ዋናው አጀንዳ አልነበረም። ይህም የአሰያየሙ ሒደት ከድርጅቱ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ያደረገው አንድ ክንዋኔ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ በህገ መንግስቱ መሰረት አብላጫ ድምፅ ያለው በመሆኑ መንግስት መስርቷል። በወቅቱ የነበሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ሲለቁ በህገ መንግስቱ መሰረት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል። በዚህም ተተኪውን መርጧል። ዋነኛ ጉዳዩ ግን በጥልቅ ተሃድሶው የተከናወኑ ጉዳዩችን መገምገም እንደነበር ግልፅ ነው።
የኢህአዴግ ምር ቤት በወቅቱ ባካሄደው ስብሰባ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባቀረባቸው ሁለት ሪፖርቶችና ከድርጅቱ ሊቀመንበር የስራ መልቀቂያ ጋር በተያያዘ የመተካካት አጀንዳ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል። ስብሰባውንም በመግባባትና በአንድነት መንፈስ አጠናቋል። ምክር ቤቱ በቅድሚያ የመከረበት አጀንዳ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በታህሳስ ወር ያካሄደውን ግምገማ መነሻ በማድረግና በየብሄራዊ ድርጅቱ የተካሄደውን ራስን ፈትሾ የማስተካከል እንቅስቃሴ ባካተተው ሪፖርት ላይ እንደነበር ይታወቃል።
በቀረበው ሪፖርት አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት በተጓዘችበት ሂደት የተመዘገቡ ለውጦች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ያጋጠሙን ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎችን በዝርዝር ተመልክቷል። ኢህአዴግ በየምርጫው የህዝብ ድምፅ አግኝቶ አገር የመምራት ኃላፊነቱን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱ ጥረቶች በሁሉም የህይወት መስኮች አገራዊ ተስፋን ያለመለሙ ለውጦች መመዝገባቸው ተወስቷል። ለውጡ የዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ባለቤቶች በመሆናችንና አቅም በፈቀደ መጠን ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችና የህዝቦች መብትና ተሳትፎ የተከበረበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉም ተገልጿል።
አገራችን የሁሉንም ህዝቦች ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን ባፀደቀችው ህገ መንግስት የዜጎችና የህዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተሟላ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በብዝሃነት በተዋቀረችው አገራችን ውስጥ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄ ሆነው የቆዩት የእኩልነት መብቶች ተከብረዋል።
የብሄሮች፣ የኃይማኖቶች፣ የፆታና መሰል የእኩልነት መብቶች ህገ መንግስታዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተዋል። አገራችን የብዙ ፍላጎቶችና ጥቅሞች መናኸሪያ መሆኗን በመቀበል የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ተደርጓል። የፖለቲካ ስልጣንም ህዝቡ በምርጫ ከሚሰጠው ድምፅ ብቻ የሚፈልቅ የህዝብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ እንዲሆን መደረጉም ተወስቷል።
ኢህአዴግ በዚህ መንገድ ወደ ስልጣን የመጣ እንደመሆኑ መጠን በህገ መንግስቱ ላይ ለሰፈሩት ድንጋጌዎች ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። የጠቅላይ ሚኒስትር የመተካካት ጉዳይን የፈፀመውም ይህን ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት ለመወጣት ሲል ነው።
እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር ማስታወስ ይገባል። እርሱም ምንም እንኳን ግለሰቦች በፓርቲው ውስጥ የራሳቸው አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም ድርጅቱ ግን ጠንካራ መስመር ያለውና በህዝብ ድጋፍ የቆመ ስለሆነ የግለሰቦች መሄድና መምጣት በፓርቲው ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ይኖራል ብዬ አላስብም።
እንዲያውም ድርጅቱ በመተካካት መርህ የሚያምን በመሆኑ ከታች ጀምሮ ይዞት የመጣው ባህሪ አለው። ይኸውም ጠንካራ መስመር፣ ግልፅና ውጤታቸው በገሃድ የሚታዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ባለቤት እንዲሁም የህዝብ ፓርቲ በመሆኑ ህልውናው በግለሰቦች ላይ የተመሰረተ ሊሆን አይችልም።
እርግጥ ግለሰቦች በድርጅቱ ውስጥ የራሳቸው ሚና አላቸው። ግለሰቦቹን የፈጠራቸው ግን በህዝቡ ትግል የተፈጠረው ፓርቲ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። የግለሰቦች ሚና በአንድ ድርጅት ውስጥ ቢኖርም ኢህአዴግ ግን የህዝብ ድርጅት በመሆኑ ከግለሰቦች ጋር መቀያየር ጋር የሚዋዥቅ ፓርቲ አይደለም። የሚያጋጥሙትን ጉዳዩች ሁሉ እየፈታ ዛሬ የደረሰ ድርጅት ነው። ጥቂት ያለፉ ጉዳዩችን ከዚህ አኳያ መመልከት አንችላለን።
ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ጊዜያዊ ተግዳሮቶች እየፈታ የመጣ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ ከአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል።
እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል። ዛሬም በአዲሱ አመራር አገራችን የተጋረጡባትን ፈተናዎች በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚፈታ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
ኢህአዴግ በጠንካራ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በጠንካራ አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች የሚመራና የሚደገፍ ድርጅት ነው። በህዝብ እየታረመ ለህዝብ የሚሰራ ድርጅትም ነው። እናም ይህ ህዝብ እስካለ ድረስ ኢህአዴግም መኖሩ አይቀርም።
ገዥው ፓርቲ ባለፉት 27 ዓመታት መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ችሏል። በዚህም በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለችው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያድግ ማድረግ የቻለ ነው።
በተለያዩ ቅቶች የህዝቡን አመኔታ የሚሸረሽሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ላይ እንደ ሁልጊዜው ከህዝቡ ጋር በመሆን ተገቢውን የእርምት ርምጃ ወስዷል። ይህም የድርጅቱን ህዝባዊነት የሚያሳይ ነው።
ድርጅቱ በመተካካት የሚያምን ነው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአመራር አባላቱ በገዛ ፈቃዳቸው ለተለያዩ ደረጃዎች ላለመወዳደር ሲወስኑና ይህም ይሁንታ ሲያገኝ የሚፈፀም የአመራር መተካካት አሰራር ነው። በውጪው ዓለም እምብዛም ያልተለመደው ይህ ዓይነቱ አሰራር በግምገማና በአባላት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚፈፀም የአመራር መተካካትን አሊያም ሽግሽግን የሚተካ ባይሆንም፤ ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር በመሆን ይህን ማሳካት ችሏል።
ኢህአዴግ ጥበትንና ትምክህትን የሚሸከም ጫንቃ የለውም። አገራችን ውስጥ ያሉት የጠባብነት፣ የትምክህተኝነትና እነርሱን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ የመንግስት ስልጣንን ለግል ኑሮ መገልገያነት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መኖሩ የግድ ነው።
እነዚህ ችግሮች ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡና እዚህ ሀገር ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት የተገኙት የልማት ትሩፋቶች የፈጠሯቸው አውዶች በመሆናቸው በአንድ ጀንበር ሊወገዱ የሚችሉ አይመስሉኝም። ሆኖም ችግሮቹ ገዥ እንዳይሆኑና የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ እጅግ አነስተኛ ማድረግ ይቻላል። በመተካካት ወደ ስልጣን የሚመጡት አዲስ አመራሮች ይህን በማድረግ ፋና ወጊ እንደሚሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።