Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአገራቱ መድን

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአገራቱ መድን

                                                    ይሁን ታፈረ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለታችኛዎቹ አገራት የስጋት ምንጭ ሳይሆን አብሮነትን የሚያለመልም ነው። በዚህም የህዳሴ ግድብ ውሃውን በማይዋዥቅ መልኩ ዓመታዊ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲያገኙ የሚረዳና ከዚህ ቀደም ደለልን ለመቀነስ ያወጡት የነበረውን ወጪ የሚያድን እንደሚሆን ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህም አገራችን የምትገነባው ግድብ የተፋሰሱ አገራት መድን መሆኑን የሚያሳይ ነው።

የአፌዴሪ መንግስት በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ ላለፉት 27 ዓመታት ተጉዟል። በሂደቱም የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት መብቃት ችሏል።

በዚህም ዛሬ ህዝቡን ከጫፍ እሰከ ጫፍ በማንቀሳቀስ ሀገራችን የያዘቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ይህም ሀገራችን ትናንት የነበራትን የአቅም ውስንነት የቀረፈና የተለየ የአስተሳሰብ ዘውግ በመፍጠርም የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራት በአመዛኙ ወደ እኛ እሳቤ ማቅረብ የቻለ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

እርግጥም ኢትዮጵያ ላለፉት 16 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል።

ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረገና ግብፆች አሁን ለደረሱበት የአቋም ለውጥ መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች ስትገልፅ ቆይታለች። እርግጥ ሀገራችን የኢንቴቤውን ስምምነት ስትቀበል በምክንያታዊነት ላይ ተመስርታ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት መብት የሚያስጠበቅና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ፤ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎቹ ስምምነት በጣት ለሚቆጠሩ ሀገሮች መብት የቆመ አለመሆኑን ስለምትገነዘብ ነው።

የሀገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው። በአሁኑ ወቅትም ግንባታው በጥቅሉ 65 በመቶ ሆኗል።

ግድቡ የቀጣናውን ሀገራት የሚጠቅም ነው። የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኤሌትሪክ ሃይልን ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ ይቻላል። ይህም በድህነት ለሚሰቃየው ህዝባችን ህይወትና ኑሮ መሻሻል የሚረዳ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል። እናም ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ለዜጎች ኑሮ መለወጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። በመሆኑም የግድቡ ግንባታ በድህነትና በኋላቀርነት የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ስለሆነ የህልውናችን መሰረት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል።

ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚ የሚያደረግ ነው። መድንም ነው ማለት ይቻላል። ግድቡ የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምር ነው። በመሆኑም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በጥቅሉ በኢትዮጵያ ህዝቦች ሙሉ አቅም በመገንባት ላይ የሚገኘው የህዳሴው ግድብ የአገራችንን ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱን አገራት ጥቅምንም ታሳቢ ያደረገ ነው።

በእኔ እምነት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ሰርታ ለልማታዊ ሥራዎች መጠቀም ብትችል ሱዳንም ሆነች ግብጽ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል መኖሩን በሚገባ ያውቃሉ።

“የአባይ ወንዝን አብረን እንጠቀም” ተብለው ሲጠየቁ ፤የግብፅን ተጠቃሚነት ለማሳጣት ታቅዶ የሚደረግ ነገር ሊኖር እንደማይችል በደንብ ይገነዘባሉ። እንዲያውም ግድቡ ቢሰራ የግብፅ ተጠቃሚነት ከፍ ሊል እንደሚችል ልቦናቸው ያውቃል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድብ ሰራች ማለት የሱዳንም ሆነ የግብፅ ግድቦች ከክምር ደለሎች ስለሚድኑ ነው። ይህ ደግሞ ሀገራቱ ለደለል ማስጠረጊያ በሚል በየዓመቱ የሚያወጡትን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን እንዲያድኑ ያደርጋቸዋል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች በዓባይ ወንዝ ላይ በሚፈጠረው ከፍተኛ ጎርፍ ምክንያትም በመስኖ ፕሮጀክቶቻቸው አካባቢ ሊደርስ የሚችለውን ውድመት የሚታደግላቸው እንደሚሆን አያጡትም። ይሁን እንጂ፤ የቀድሞዎቹ የግብፅ ገዢዎች የዓባይ ውሃን ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሊያተርፉ ከሚችሉት ጥቅም ይልቅ ለአንባገነናዊ ስርዓታቸው ዕድሜ ማራዘሚያነት ሲጠቀሙበት ኖረዋል።

ይህ ሁኔታ ግን በአሁኑ ወቅት የየቀየረ ቢመስልም፤ አልፎ አልፎ የሚታዩች ዝንባሌዎች አሁንም ግልፅ የሆነ መተማመንን ያዳበሩ አይመስሉም። አሁንም ቢሆን ጠንካራ መተማመን ያስፈልጋል። አብሮ ማደግን በፀጋ መቀበል ተገቢ ነው።

ግድቡ ማናቸውንም የተፋሰሱን አገራት የሚጎዳ አይደለም፤ ይበልጥ ተጠቃሚነታቸውን ያረጋግጣል እንጂ። ይህ እውነታ የጋራ መግባባት ሊያዝበት የሚገባ ጉዳይ ነው። እንዲያውም የግድቡ ግንባታ ለተፋሰሱ አገራት መድን መድን መሆኑን አገራቱ በተለይም ግብፅ በእምነት ልትቀበለው ይገባል። ምክንያቱም ኢትዮጰያዊያን የትኛውንም ወንድም አገር የመጉዳት ዓላማና ፍላጎት እንዲሁም ታሪክ የሌላቸው በመሆኑ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy