Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የእነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ልፈፋ ግልባጭ

0 661

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የእነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ልፈፋ ግልባጭ

                                                                 ዘአማን በላይ

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ውስጥ አንድ የተለመደ አሰራር አለ። ይኸውም አባላቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን (እንደ ሁኔታው ሚሊዮኖችም ሊሆን ይችላል) እየተቀበሉ የሚፈልጉትን ወገን ለመጥቀም ሲሉ ቤታቸው ቁጭ ብለው ለምክር ቤታቸው የሚቀርብ የውሳኔ ሃሳብ ማርቀቃቸው ነው። መነሻው ያው የፈረደባቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው። ከዚያም የኮንግረስ አባሉ ገንዘብ ከፋዩ በሚፈልገው ልክ ቤታቸው ያረቀቁትን የውሳኔ ሃሳብ ለሌሎች የኮንግረሱ አባላት በማቅረብ ለማሳመን የውትወታ ስራቸውን ይጀምራሉ። በዚህ ሂደትም ጉዳዩን ወደ ኮንግረሱ በመውሰድ ድምፅ ያሰጡበታል። የስራው ጥልቀትና ፍጥነት የሚመዘነው የኮንግረስ አባሉ በተቀበሉት የገንዘብ መጠን ልክ የሚወሰን ይሆናል። የውሳኔ ሃሳቡ በምክር ቤቱ ፀድቅም ላይፀድቅም ይችላል። ግና የኮንግረስ አባሉ ለውትወታ (lobby) ስራ ገንዘብ ተቀብያለሁ በማለት ለመንግስታቸው ግብር ይከፍላሉ። እንግዲህ ጉዳዩ ንግድ መሆኑ ነው።

ወትዋች ግለሰቦችንና ቡድኖችን (lobby Persons and Groups) ቀጥሮ ማሰራት በሀገረ አሜሪካ ውስጥ የተለመደ አሰራር ነው። ምክንያቱም በአንድ በኩል የገቢ ማግኛ ምንጭ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሽፋን በአንድ ሀገር ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ፍልስፍና ውስጥ ሰተት ብሎ ለመግባት በር የሚከፍት ስራ ነው። የኮንግረስ አባሉ ህጉን ሲያረቅቁ ህጉ በሚረቀቅበት ሀገር ውስጥ ያለውን ተጨባጭ እውነታ በአካል ሄደው አይመለከቱም። ቀዳሚ መረጃቸው የሚያደርጓቸው በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጭንብል ከሚንቀሳቀሱትና ለዚሁ ዓላማ ከተቋቋሙት እንደ “ሂዮማን ራይትስ ዎች”፣ “አምንስቲ ኢንተርናሽናል”፣ “ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ”፣ “ፍሪደም ሃውስ”፣ “ሲፒጄ”፣ “ኢንተርናሽናል ሪቨርስ”፣ “ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ”…ወዘተ. ከመሳሰሉ ቡድኖች ነው። እነዚህ ቡድኖች በዚያች ሀገር ቢሮ ባይኖራቸውም ችግር የለውም። ግን ከእነርሱ ያገኙትን የስሚ ስሚ መረጃ ለህግ ማርቀቁ ስራ ይጠቀሙበታል።

እነዚህ ቡድኖች ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጋር የሚያገናኛቸው አንዳችም ጉዳይ የለም። አክራሪ ኒዮ ለበራሎች ናቸው። ዋነኛ ዓላማቸውም ከኒዮ-ሊበራል አስተሳሰብ ውጭ በራሱ ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ፍልስፍና የሚያድግና ለሌሎች ሀገራት አርአያ ሊሆን ይችላል ብለው የገመቱትን ሀገርና ህዝብ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ስም በሪፖርት ጋጋታ ውርጅብኝ እየወረዱባቸው ስማቸውን ማጥፋት ነው። ለዚህ ተግባራቸው ይረዳቸው ዘንድ “የርዕዩተ ዓለም ትግል” በሚያደርጉት ሀገርና ስርዓት ጋር የማይስማሙ አለያም ተቃዋሚ ናቸው ከሚባሉ ቡድኖች ጋር ጥምረት ይፈጥራሉ። ከፍ ሲልም ያ መንግስትና ስርዓት “ወይ ፍንክች” ማለቱን ከተገነዘቡ የቀለም አብዮትን እስከ ማቀነባበር የሚደርስ ሉዓላዊነትን የሚፃረር ተግባር ይከውናሉ።  

የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ከላይ የጠቀስኳቸውና በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በተናጠልና በዘመቻ መልክ በሀገራችን ላይ ያላወጡት የሪፖርት ጋጋት እንደሌለ የሚገነዘብ ይመስለኛል። በተለይ ራሱን “ሂዮማን ራይትስ ዎች” እያለ የሚጠራው አክራሪ ኒዮ ሊበራል ቡድን የቤተ ክርስቲያን ስዕለት ያለበት ይመስል እየመላለሰ በሀገራችን ላይ በሚነዛው አሉባልታ የሚታወቅ ነው። እርሱንና መሰል አክራሪ ኒዮ ሊበራል ተቋማትን በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ፈፅሞ አይወዷቸውም። ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ወቅት እየደጋገሙ “ከአክራሪ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች ጋር ፈፅሞ አንዋደድም” ሲሉ የነበሩት ለዚሁ ነው።

በእኔ እምነት ሰሞኑን በኒውጀርሲው ምክር ቤት አባል ክሪስ ስሚዝና በኮሎራዶው የምክር ቤት አባል ሚክ ኮፍማን አርቃቂነት ቀርቦ በአሜሪካ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ያለፈው ኤች አር 128 የተባለው የውሳኔ ሃሳብ የተገለበጠው ከ“ሂዮማን ራይትስ ዎች” እና መሰሎቹ ልፈፋ በቀጥታ የተወሰደ ነው። በተለይ የኒውጀርሲው ኮንግረስ ማን ክሪስ ስሚዝ አሜሪካ ከሚገኙ የዲያስፖራ ፅንፈኞችና በሀገራችን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጁት ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ይታመናል። በተለያዩ ፀሐፍት “አሜሪካዊው አና ጎሜዝ” እየተባሉ የሚጠሩትም ለዚሁ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ኤች አር 128 በውስጡ የያዘው ጉዳይ ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ፤ የምናገኛቸው ጉዳዩች የኢትዮጵያ መንግስት የፈፀማቸውና እየፈፀማቸው የሚገኙ ሃቆች ናቸው። አሊያም መንግስት ወደፊት ከህዝቡ ጋር እየተመካከረ የሚከውናቸው በዕቅድ የተያዙ ጉዳዩች ናቸው። ዳሩ ግን አቀራረቡ እነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” እና ፅንፈኛ ዲያስፖራዎች በሚያነሷቸው አሉባልታዎች በተያዙ ግንዛቤዎች ላይ የተመሰረቱ ሆነው እናገኛቸዋለን። ከዚህ ፅሑፍ አኳያ የውሳኔ ሃሳቡን ጉዳዩች በጥቂቱ በመውሰድ መመልከት ሃቁን እንድንገነዘብ ያስችለናል።

የውሳኔ ሃሳቡ የፀደቀው የኢትዮጵያ መንግሥት የተሃድሶ ርምጃ እንዲወስድ ለማስገደድ ነው የሚል ሃሳብ እናገኛለን። በቅድሚያ ማንም ማንንም ሊያስገድድ አይችልም። የኢትዮጵያ መንግስት ሊያስገድደው የሚችለው ህዝቡ እንጂ የአሜሪካ ኮንግረስ አይደለም። የኢፌዴሪ መንግስት አለቃው፣ አዛዡና ናዛዡ የሀገሩ ህዝብ እንጂ ሌላ አካል አይደለም።

ለነገሩ የውሳኔ ሃሳቡ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ በሀገራችን ላይ የሚፈጥር አይደለም። አሁን ካለበትም በላይ መሄድ አይችልም። የአሜሪካ ሴኔትም ይሁን ዋይት ሃውስ የሚያውቀው አይደለም። ምናልባትም ወደ ሴኔት ይተላለፋል የሚሉ ሰዎች ካሉ ይህ ፈፅሞ ውሸት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ተራ ምክር መስጫ ብቻ ነው። ምናልባት አሜሪካ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኮንግረሱ ሃሳብ የሰፈረበት ደብዳቤ ሊደርሰው ይችላል። ከምክር ያለፈ ነገር ስለሌለውም አስገዳጅ አይደለም። ህግ የመሆን አቅምም የለውም።

ያም ሆኖ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አንዱ “ጌታ” ሌላው ደግሞ “ሎሌ” አለመሆኑን የዲያስፖራ ፅንፈኞች ሊያውቁት ይገባል። አሜሪካና ኢትዮጵያ የ120 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው። ግንኙነቱ ኢትዮጵያን እንደ አንዲት ሉዓላዊት ሀገር የሚያከብርና በውስጥ ጉዳይዋም ጣልቃ የመግባት አካሄድን የሚፈቅድ ቀዳዳ የለውም። መንግስት የሚከተለው አካሄድም ሀገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርግና በማናቸውም የውስጥ ጉዳዮች የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ አይደለም። ይህ እውነታም በአሜሪካኖቹ ዘንድ በደንብ ይታወቃል። ዋሽንግተኖች የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሲመሰርቱም በኢትዮጵያ ላይ ፍላጎታቸውን በኃይል መጫን እንደማይችሉ ተገንዝበው ይመስለኛል። ለዚህም የራሳቸው ምክንያቶች እንዳሏቸው ግልፅ ነው። እነርሱም ሀገራችን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትና በልማት ላይ ማተኮርዋን ስለሚገነዘቡ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ጂኦ- ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ስለሚያውቁ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተች ያላችውን የላቀ ሚና ስለሚረዱ እንዲሁም በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ስለሚያጤኑ መሆኑን በምክንያትነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። እነዚህ የመንግስታችንና የህዝባችን የማንነት መገለጫዎችና ቁልፍ ተግባራት የአሜሪካ መንግስትም ፍላጎቶች በመሆናቸው፤ የሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነት ግንኙነቱ የማዕዘን ድንጋይ ናቸው።

እነዚህ የግንኙነት መሰረቶች በእኩልነት ላይ በተመረኮዘ ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያጠነጥኑ እንጂ፤ በአዛዥና ታዛዥነት የሚከናወኑ አይደሉም። ሀገራችን በአሜሪካ የውስጥ ጉዳይ እጇን ለማስገባት እንደማትፈልግ ሁሉ፤ የዋሽንግተን ሰዎችም ከፖሊሲ አንፃር በውስጥ ጉዳያችን እጃቸውን የሚያስገቡበት ምንም ዓይነት ምክንታዊ አመክንዩ ሊኖራቸው አይችልም። ስለሆነም የግኝኑነቱ መሰረት “የቄሳርን ለቄሳር…” በሚል መርህ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

ይህን ሃቅ በውል የማይረዱት ፀንፈኛ ዲያስፖራዎች ግን፤ ሁልጊዜም ቢሆን የአሜሪካ መንግስት ጫና የሚያሳድርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሀገራችን ውስጥ ያለ የሚመስላቸው ናቸው። የሀገራቱን የእኩል ተጠቃሚነት ቁርኝት ምስጢር ስለማይገባቸውም፤ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ አንዳች ተፅዕኖ አሳርፋ፣ የፀረ ህዝብነት ህልማቸውን ለማሳካት ሰርክ “ሱባዔ” እንደገቡ ነው። በየአደባባዩ እንደለፈፉ ናቸው።

ያም ሆኖ ግን በኤች አር 128 ላይ የሰፈረው “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ” እና ሌሎች አዋጀችን የማንሳት ጥያቄዎች ከላይ በጠቀስኳቸው እንዲሁም ሌላው ሀገር ሲያደርግ ምንም ዓይነት ሃሳብ ያልተሰጠበት በመሆኑ ምክንያት ተቀባይነት የለውም። ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ናት። እንዲሁን ግብፅ ለሶስት ወራት አውጃው የነበረችውን ያስቸኳይ ጊዘዜ አጅ ለቀጣዩቹ ሶስት ወራት አራዝማዋለች።

እናም የአሜሪካ ኮንግረስ የተለየ ምክንያት ከሌለው በስተቀር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባወጡት በፈረንሳይና በግብፅ ላይም ተመሳሳይ የውሳኔ ሳብ ማቅረብ ነበረበት። ጉዳዩ በኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ምን አዲስ ነገር እንደተገኘበት ለማንም ግልፅ አይደለም። ያም ሆነ ይህ አዋጁን ያፀደቀው የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት እንጂ የአሜሪካ ኮንግረስ አይደለም። እናም አዋጁን የማንሳትም ሆነ ያለማንሳት መብት የሀገራችን ፓርላማ እንጂ ማንም አይደለም። ሌሎቹንም አዋጆች የማንሳት መብቱ የዚሁ የህዝቡ እንደራሴዎች የሚገኙበት ፓርላማ ብቻ ነው። እናም የ“አዋጆችን አንሱ” ጥያቄ የአንድን አገር ሉዓላዊት በገሃድ መጋፋት በመሆኑ ምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም።

የውሳኔ ሃሳቡ የዴሞክራሲ ህዳሩ እንዲሰፋ ይጠይቃል። እርግጥ በሀገራችን ውስጥ ዴሞክራሰ እንዲሰፋ የማይፈልግ የለም። መንግስትም ከሁለት ዓመታት በፊት ዴሞክራሲውን ለማስፋት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። ሌላው ቀርቶ የውሳኔ ሃሳቡ መንግስት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከሚወክሉት የፖለቲካ ፓርተዎች ጋር እያደረገ የሚገኘውን ድርድር እንኳን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም።

ምንም እንኳን የዴሞክራሲ ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚከናወን ባይሆንም፤ የኢፌዴሪ መንግስት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ እያደረገ ነው። ይህን ተግባሩን ሊያጠናክሩ የሚችሉትን እንደ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶች የዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋማትን በማቋቋም ራሱን በራሱ እያረመ ይገኛል። የኮንግረሱ ውሳኔ ይህን ሁሉ እውነታ የካደ አሊያም የማያውቅ ነው።

የውሳኔ ሃሳቡ የሰብዓዊ መብት ማክበርን መደገፍና አሳታፊ የአስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ለመደገፍ የወጣ መሆኑን ይገልፃል። ሀገራችን ታዳጊና ለመብቶች መከበር ገና አዲስ በመሆኗ የትኛውም ወገን በሰብዓዊ በምት አያያዝ በኩል ቢደግፋት ቅር የሚሰኝ ሰው የለም። ተገቢ ነውና። ይሁንና አሁንም የውሳኔ ሃሳቡ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን በማክበር ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዛለች። መብቱን በህገ መንግስቱ ላይ ከማፅደቅ ጀምሮ እስከ መተግበር ድረስ ረጅም ርቀት ተጉዛለች። እንደ እውነቱ ከሆነ ሰብዓዊ መብት ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚት ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ በምቶች ሲሟሉ ሰብዓዊ መብትም ይረጋገጣል። ከዚህ አኳያ ሀገራችን በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማት…ወዘተ በርካታ ስራዎችን አከናውናለች። ዓለምም መስክሮላታል። ይህም በህገ መንግስታችን ላይ የሰፈሩትን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ከመፈፀም ባሻገር፤ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮችም ሰብዓዊ በምቶችን እያረጋገጠች ለመሆኑ እማኝ ነው። ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝ ፍፁም ናት እያለኩ አይደለም። እንኳንስ መብቶች ማስከበር ከጀመርን 27 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠርነው እኛ ቀርቶ፤ በዘርፉ ከ250 ዓመታት በላይ የተጓዘችው የኮንግረሱ አባላት ሀገር አሜሪካም ብትሆን በርካታ ስንክሳር ያለባት ሀገር መሆኗ ማንም የሚያውቀው የጠራራ ፀሐይ እውነታ ነው።

ያም ሆኖ ግን ዛሬም ይሁን ነገ አሜሪካና ኢትዮጵያ በትብብር ይሰራሉ። የጋራ ተጠቃሚነት እስካላቸው ድረስ ኮንግረሱ ምክስ ሰጠ አልሰጠ የሚያመጣው ለውጥ የለም። በውሳኔ ሃሳቡ ምክንያት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚፈጠር አንዳችም ነገር የለም። ከላይ የጠቀስኳቸው የኮንግረሱ የውሳኔ ሃሳብ እነ “ሂዪማን ራይትስ ዎች” ዶክተር አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በተሰየሙ ማግስት “ማድረግ ይገባቸዋል” ብለው ለማዘዝ በመሞከር ጭምር ሲለፍፉት የነበረው ጉዳይ ማሳያ እንጂ፤ በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት የሚሰራውን የአሜሪካን መንግስት ፈፅሞ የሚመለከት አይደሉም። በመጨረሻም የአሜሪካ ኮንግረስ እዚህ ሀገር ውስጥ መጥተው ባለዩት ነገር “ምክር” ለመስጠት መሞከራቸው ተገቢ ባይሆንም፤ ለወደፊቱ ግን ከእነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ሪፖርት ገልብጦ እንደ ትክከለኛ ሰነድ የመውሰድ አካሄድን በመተው ተጨባጭነት ባላቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዘው ሰብዓዊንም ይሁን ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሊደግፉ በሚችሉ ጉዳዩች ዙሪያ  ከመንግስት ጋር ተቀራርበው ቢሰሩ ትክክለኛውን “ምክር” መስጠት የሚችሉ ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy