Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኮንፈረንሱን እውነታዎች በጨረፍታ

0 261

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኮንፈረንሱን እውነታዎች በጨረፍታ

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

መቐለ። ሰሜናዊት ኮከብ። ፅዱና ውብ ከተማ። ሰሞኑን አንድ ህዝባዊ ኮንፈረስ አካሂዳ ነበር። ይህ ኮንፈረንስ በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የመጠራጠርና የመቃቃር ስሜት በመቅረፍ ወደ ጠንካራ አንድነት ለመመለስ ያስቻለ ነበር ማለት ይቻላል። ከተለያዩ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተወጣጡ የኮንፈረንሱ ታዳሚዎች የአብሮነትን ዝማሬዎች አብረው አዚመዋል። እንግዳ ወይም በትግርኛ “ጋሻ” በዚያ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ነፍሱ በሚወደው ህዝብ መሐል ምን ያህል ክቡር እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ሲናገሩ ማድመጥ ልብ ይነካል።

ወደ ትግራይ እግር ጥሎት የሄደ ሰው ባይተዋርነት አይሰማውም። ርግጥ ለስራ ጉዳይ ወደ ትግራይ ስመላለስ ከታዘብኳቸው ጉዳዩች ውስጥ ህዝቡ ከሌላ አካባቢ ለመጣ ኢትዮጵያዊ የሚሰጠው ወደር የማይገኝለት ፍቅር ነው። የትግራይ ህዝብ ያለውን ነገር ያካፍላል። ማጀቱን ከፍቶ፣ ድስቱን ገልብጦ፣ ጮጮውን አንጠፍጥፎ የሚያበላና የሚያጠጣ ህዝብ ነው። በማናቸውም ጉዳዩች ላይ ከሀገሬው ህዝብ ይልቅ “ጋሻ” (እንግዳ) ቅድሚያ ይሰጠዋል። ይህን እውነታ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ሲጠቅሱት

ትግራይ ውስጥ ለስራ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የክብር ካባን ደርቦ ደራርቦ ይጎናፀፋል። ያ ህዝብ ድህነት ይዞት ነው እንጂ፣ ምንም ነገር ከመስጠት አይቆጠብም። የሌላውን ባላውቅም እኔ በበኩሌ በኢትዮጵያዊነቴ የምኮራው ወደ ትግራይ ሳቀና ነው። የፍቅሩና ሌላውን ኢትዮጵያዊ የመውደዱ ምስጢር ሁሌም ከፊቴ ድቅን ይልብኛል። የኢትዮጵያዊነት ምንጭና ኩራት መሆኑንም ያስታውሰኛል። እናም በዚያ ታታሪና ኢትዮጵያዊ ህዝብ መሃል ሁሌም ብገኝ ደስታዬ ወደር የለውም።

በዚህ ህዝብ መሐል መገኘት ያኮራል። ኮንፈረንሱ ከሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች “ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው። ለአራት ቀናት በተካሄደው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ከ2500 በላይ ታዳሚዎች ተገኝተዋል። ታዳሚዎቹ ከትግራይ ክልል፣ ከመላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ከተለያዩ ማህበራት የተውጣጡ ናቸው።

እነዚህ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በዚህ ሀገራችን ያጋጠማትን ችግሮች መነሻ በሚገባ በመረዳት መፍትሔዎችን  ማስቀመጥ የቻሉ ናቸው። በዚህም መላው መላ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ማጠናከር የሚያስችል ለዮና ታሪካዊ ኮንፈረንስ አካሂደዋል።

ታዳሚዎቹ በኮንፈረንሱ ላይ ያነሷቸው ጉዳዩች አራት ናቸው። እነርሱም የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ማዕከል በማድረግ፤ የክልሉ መሪ ድርጅት ህወሓት/ኢህአዴግ፣ የውስጠ-ድርጅት ሁኔታና የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች አፈፃፀም፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚሉ ናቸው። በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዩች ዙሪያ ሰፊ ግምገማና ውይይት በማድረግ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በሚያመጡ ጉዳዩች ላይ ምክከር አድርገው የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል። በዚህ ፅሑፍ ላይ በታዳሚዎቹ አቋም በተያዘባቸውን ሁለት ጉዳዩች ላይ ለማተኮር እወዳለሁ።  

በዚህ በትግራይ ክልል ጋባዥነት በተካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ታዳሚዎቹ በወቅቱ ባወጡት የአቋም መግለጫ፤ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተወከሉ ተሳታፊዎች ከሰጡት ገንቢ ሃሳብ በመነሳት የሀገራችን ህዝቦች ህይወትና ልማት በጋራ መተጋገዝና መረዳዳት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህም በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። ለወደፊቱም ሀገራዊ ጥቅማቸውንና አንድነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። በተለይም የህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማጨናገፍ ላይና ታች የሚሉ ፀረ ህዝብ ሃይሎችን በጋራ ለመታገል ቃል ገብተዋል።

ርግጥ ርግጥ ከአንዳንድ ፅንፈኞ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይን ህዝብ የሚጠላ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም። ያ ህዝብ ከአማራው፣ ከኦሮሞው፣ ከአፋሩ፣ ከቤኒሻንጉሉ፣ ከደቡቡ…ወዘተ. ጋር በደምና በአጥንት የተሳሰረ ነው። የትግራይ ህዝብ ወግና ባህል በሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። እንግዳ አክባሪነትና ተቻችሎ መኖር የትግራይም ይሁን የሌላው ኢትዮጵያዊ መለያ ነው።

ይህ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንና እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሀገሩን የሚወድ ነው። ይህን ከጥንት ከጠዋቱ ይዞት የመጣውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ማንም ሊፍቀው አይቻለውም። ይህ ህዝብ ‘ሀገሪቱ ሲያልፍላት እኔም ያልፍልኛል’ በማለት በመንግስት ዕቅድ እየተመራ የዕድገት ባበቡር ላይ ተሳፍሮ ህዳሴውን አውን ለማድረግ በመትጋት ላይ የሚገኝ ነው። ይህ ህዝብ የርሱ ማደግ በአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያሳርፍ የሚገነዘብና ከዚህ አኳያ ተግባሩን እየተወጣ የሚገኝ ነው።

እናም ይሀን ታታሪና ከተፈጥሮ ጋር የሚታገል ህዝብ ማንም ሊጠላው አይችልም። ይህን የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሆነን ህዝብ ሊጠሉ የሚችሉት ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ብቻ ናቸው። ከጥንት ከጠዋቱ ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር ሲማስን የነበረን ህዝብ ሊጠሉት የሚችሉት በፌስ ቡክና በሌሎች የትስስር መረቦች ላይ በአላዋቂ ሳሚነት የሚዘላብዱ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው።

 

ኮንፈረንሰኞቹ የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ያካሄዱት እልህ አስጨራሽ ትግልና የከፈሉት መስዕዋትነት አዲሲቷን ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጫወቱት ሚና መተኪያ እንደሌለው አስምረውበታል። አዎ! ይህ ህዝብ ዛሬ ለተፈጠረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሲል የሞተ፣ የቆሰለ፣ ንብረቱን ያጣ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን ሊወሩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የመጡ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ቅሌታቸውን ተከናንበው እንዲመለሱ ያደረገ ነው። ከሁለት የቅርብ ጊዜያችን ትውስታዎች እንነሳ—ከደርግ ጋር የተደረገውን እልህ አስጨራሽና መራር ትግል እንዲሁም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከሻዕቢያ ጋር በተደረገው ትንቅንቅ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ያደረገው ተጋድሎ።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የትግራይ ህዝብ ያላየው የፍዳ ዓይነት የለም። ሞቷል፣ ቆስሏል፣ ደምቷል፣ ንብረቱን አጥቷል። በእውነቱ በትግሉ ወቅት እንደ ትግራይና አካባቢው አበሳውን የበላ ህዝብና አካባቢ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም። ምክንያቱም ይህ ህዝብ ከሚኖርበት አካባቢ ባሻገር በመላ ሀገሪቱ እንደ ጠላት ተቆጥሮ ሲታደን የነበረ በመሆኑ ነው።

ርግጥ አምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጉጠት ባላቸው ሹል ጥፍሮቹ ያልቧጠጠው፣ ስለት ባለው ቢላዋው ያልሸረካከተው፣ በብረት ለበስ ታንኮቹ ያልደፈጠጠው የህብረተሰብ ክፍል የለም። ያም ሆኖ፤ እንደ ትግራይ ህዝብ የደርግ የአፈና አገዛዝ እንደ መርግ የተጫነበት የህብረተሰብ ክፍል ያለ አይመስለኝም። ሁሉም የብሔረ ትግራይ ተወላጅ ሊባል በሚችል መልኩ በደርግ ጥቁር መዝገብ (black list) ውስጥ የነበረ ነው ማለት ይቻላል። መቼ ታፍኖ እንደሚወሰድ አያውቅም። እስር ቤት የታጎረውም ቢሆን በየትኛው ለሊት ስሙ ተጠርቶ የጥይት አረር እንደሚበላው የሚያውቅበት አንዳችም መንገድ አልነበረውም። ጉዞው የሰቀቀን መንገዱም አሜኬላ እሾህ የበዛበት ነበር።

እናም ይህ ፈታኝ የጭቆናን አገዛዝ መቋቋም ስላቃተው ዱር ቤቴ ብሎ ከ70 ሺህ የሚልቁ ልጆቹ ደደቢት በረሃ ላይ በተለኮሰው የትግል ችቦ አማካኝነት ህይወታቸውን አጡ። ለዛሬዋ ኢትዮጵያም መሰረት ሆኑ። ይህ ሁሉ የሆነው የትግራይ ህዝብ በራሱና በሌላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ የተጫነው አምባገነናዊ ስርዓት እንዲወገድ ካለው ፍላጎት በመነሳት ነው።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ቢሆን፤ ጦረኛው የአስመራ መንግስት በእብሪት ባድመንና አካባቢውን በወረረበት ወቅት፣ ሁለተኛው የትግራይ ህዝብ ከአካባቢው ሚሊሻ ጎን በመሆን በሜካናይዝድ የተደራጀውን የሻዕቢያ ጦር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ተጠናክሮ ወደ አካባቢው እስኪደርስ ድረስ እንዴት አድርጎ መክቶና ገትቶ ባለበት ቦታ እንዳቆመው ማንም የሚዘነጋው አይመስለኝም።

በወቅቱ በርካታ የትግራይ ሚሊሻዎች ህይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል። ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፤ ከሚኖሩበት ቀዬና መንደር ተፈናቅለዋል። በወቅቱ በሻዕቢያ የተወረሩት አካባቢዎች ጥቂት ቢሆኑም ቅሉ፤ በወቅቱ ሁሉም የክልሉ ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል በላይ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ተደርጎ ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ከትተዋል።

በህዝብ የሚደገፈው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ተጠናክሮ ወደ አካባቢው ከዘለቀ በኋላም፤ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ዳር ድንበራቸው ከተነካባቸውና ከተቆጡት ከሌሎቹ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ወራሪውን ጦር አከርካሪውን ሰብሮ ወደ መጣበት እንዲፈረጥጥ ሲያደርገውም የትግራይ ህዝብ ያለውን ጥሪት አሟጦ ተረባርቧል። አዋቂ፣ ህፃንና ሴት እንዲሁም በትጥቅ ትግሉ ወቅት አካላቸው የጎደለ ታጋዩች ሳይቀር በየፊናው ያሰለፈና ያኔም እንደ ትናንቱ ጠላትን ያሳፈረ ህዝብ ነው። ዛሬም ቢሆን ከሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ዴሞክራሲያዊ አንደነቱን እያጠናከረ ነው።

በአጠቃላይ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የተካሄደው ውይይት ዴሞከራሲያዊ አንድነቱን ማጠናከር የቻለበት ነው። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ኮንፈረንሶች የአንድ ጊዜ ስራ መሆን የለባቸውም። ተከታታይ ስራ መሆን ያለባቸው ይመስለኛል። እናም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy