የዴሞክራሲ ምህዳር የሚሰፋው በተፎካካሪዎችም ነው
ለሚ ዋቄ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስራቸውን በይፋ መጀመራቸውን ተከትሎ ለውይይትና ለመቀራረብ በተዘጋጁ መድረኮች ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝተዋል። በመጀመሪያ ወደኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ነበር የሄዱት። በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መሃከል ድንበርን መነሻ ያደረገ አለመግባባት ተቀስቅሶ፣ ሁኔታው የቀውስ አባባሽ ምክንያት ሆኖ እንደነበረ ይታወሳል። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ተገኝተው ያስተላለፉት መልዕክት በሁለቱ ክልል ህዝቦች መሃከል ተፈጥሮ የነበረውን የሻከረ ግንኙነት በማደስ የመተማማን መሰረት ጥሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደአምቦ አቅነተው ከአምቦ ከተማና አካባቢው ህዝብ ጋርም ተገናኝተዋል። አምቦና አካባቢው በተለይ በኦሮሚያ ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞ ከተካሄደባቸው ከተሞች አንዱ እንደነበረ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአምቦ ተገኝተው ያስተላለፉት መልዕክት ለአምቦና አካባቢው ብቻ ሳይሆን በመላ ሃገሪቱ በህዝብና በመንግስት መሃከል የመተማመን ድልድይ ዘርግቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተመንግስት በተዘጋጀ የእራት ስነስርአት ላይ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችንና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችንም አግኝተዋል። በመድረኩም ላይ ያስተላለፉት መልዕክት በገዢው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መሃከል መተማመንና መቀራረብ እንዲኖር የሚያስችል መንገድ ጠርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደትግራይ ክልልም አቅንተዋል። በዚያ ከመቀሌና አካባቢው ህዝብ ጋር ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ መልዕክት ማስተላለፋቸው በህዝቡ ዘንድ ልዩ የአንድነት ስሜት አሳድሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመጨረሻ ከሁሉም የሃገሪቱ ክልሎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተወጣጡ 25 ሺህ ገደማ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በሚሊኒየም አዳራሽ መልዕክት አስተላልዋል። መልዕክቱ ለመላው ኢትዮጵያውያንም የተላለፈ ነበር።
በአጠቃላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በእነዚህ መድረኮች ያስተላለፏቸው መልዕክቶችና ከህዝብ ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች በተለያዩ ሰበቦች እየላላ መጥቶ የነበረውን ሃገራዊ አንድነት ለማጠናከር፣ ለመተማመንና ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል መሰረት ጥሏል። በእነዚህ መድረኮች ላይ በርካታ መልዕክቶችየተላለፉ ሲሆን፤ በዚህ ጽሁፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተለይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር በነበራቸው ቆይታ ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰኑ ጉዳዮችን ከነባራዊው ሁኔታ አኳያ ለመመልከት ወድጃለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ሰላማዊ መሆን እንደሚገባው፣ በሃይልና በአመጽ መንግስት እየተገለበጠ በየጊዜው ከዜሮ እየጀመሩ መሄድ ሃገሪቱን የሚያስከፍል መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ጉዳይ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በመገንባት ሂደት ውስጥ ወሳኝ ነው። አሁን በሃገሪቱ ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲ አለ። ይህን በህገመንግስት የተረጋገጠ ዴሞክራሲ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ግን ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ክፍተቶች በአመዛኙ ከጸረዴሞክራሲያዊነት ወይም ህገመንግስቱን ካለመቀበል የመነጩ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ዴሞክራሲን ካለመለመማድ፣ ዴሞክራሲ ጎልብቶ ባህል ካለመሆኑ የመነጩ ናቸው። በመሆኑም፣ እነዚህን ከዴሞክራሲ ባህል አለመጎልበት የመነጩ ችግሮችን ያለወጉ በማራገብ መንግስትን በሃይል ለማስወገድ አመጽ መቀሰቀስ፣ ስርአቱን ለማፍረስ ከሃገሪቱ ጠላቶች ጋር እስከማበር የዘለቀ ክህደት መፈጸም የጎደለውን ከመሙላት ይልቅ የተገኘውንም የሚያጠፋ መሆኑን ማሰብ ብልህነት ነው።
መንግስታዊ ስርአትን በሃይል መናድ የህይወት መስዋዕትነት ይጠይቃል። የሃገር ሀብት ያወድማል። መንግስት በሃይል ሲወገድ የነበረው ፈርሶ ሁሉም ነገር ‘ሀ’ ተብሎ ነው የሚጀመረው። በዚህ መንገድ ቀጣይነት ያለው የዴሞክራሲና የልማት እድገት እውን ማድረግ የማይታሰብ ነው። መንግስት በሃይል ሲወገድ፣ በሃይል ከስልጣን የተወገደው ወገን ደጋፊዎች አዲሱን ገዢ በጸጋ አይቀበሉትም። አዲሱን መንግስት በተለመደው የሃይል መንገድ ለማስወገድ መንቀሳቀሳቸው አይቀሬ ነው። በመሆኑም በሃይል ስርአት ሲወገድ ይህ ሁኔታ የመደጋገም እድሉ ሰፊ ነው። በየግዜው የነበረው እየፈረሰ እንደአዲስ ሲጀመር ሃገር በዴሞክራሲም ሆነ በልማት ጅምር ሆና ትቀራለች። በእርስ በርስ ግጭት መልሶ መገንባት በማይቻልበት ሁኔታ ፈራርሶ የመቅረት አደጋም አለ። የሃይል እንቅስቃሴ ሰብአዊ ቀውስ – ሞት፣ መፈናቀልና ስደት፣ ረሃብ ወዘተ የማይለየው መሆኑም መታወቅ አለበት።
እናም፣ ሰፋም ጠበበ ባለው የዴሞክራሲ ምህዳር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ምህዳሩን ለማስፋት እየታገሉ በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መዝለቅ ምትክ የሌለው አማራጭ ነው። ለዚህ ደገሞ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ በራሳቸው ውስጥ ዴሞክራሲን መለማመድ ይኖርባቸዋል። በራሱ ውስጥ ዴሞክራሲ ያልገነባ የፖለቲካ ፓርቲ በሃገራዊ ዴሞክራሲ ውስጥ መንቀሳቀስ አይችልም። በዚህ ረገድ የሃገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎቸ ችግሮች አሉባቸው። ብዙዎቹ ፓርቲዎች ከአመራር ምርጫ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ነው የሚታየው። ራሳቸው ላዘጋጁት መተዳደሪያ ደንብ አለመገዛት፣ በምርጫ ከአመራርነት ሲወገዱ ይህን ተቀብሎ ሃላፊነትን ከማስረከብ ይልቅ ደጋፊዎችን ሰብስቦ ፓርቲውን መሰንጠቅ፣ ሌላ ፓርቲ አደራጅቶ መሪ መሆን ወዘተ የብዙዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎቸ መለያ ነው። በራሱ ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማካሄድ ያልቻለ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ህገመንግስት አክብረው ይንቀሳቀሳሉ፣ ሽንፈትን ተቀብለው በህዝብ ድምጽ በሚገኝ የስልጣን ውክልና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ይፈቅዳሉ . . . ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። እናም የሃገሪቱን የዴሞክራሲ ምህዳር ለማስፋት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርዎች ራሳቸውን በሚገባ ማከም ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባል።
በሌላ በኩል፣ በአንድ ሃገር ውስጥ ርዕዮ-ተዓለም፣ አማራጭ ፖሊሲ . . . ላይ ተመስርተው የተደራጁ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ለሌላው ጠላቱ አይደሉም። ሁሉም ለአንድ ሃገር ልማትና ሰላም የተሻለው አማራጭ የእኔ ነው በሚል የሚቀርቡ ለሃገርና ህዝብ መልካም ራዕይ ያላቸው ተደርገው መወሰድ ይገባቸዋል። በመሆኑም በመሃከላቸው መተማመንና መከባበር ሊኖር ይገባል። ለዚህ ደግሞ በሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መቀራረብ፣ መመካከር፣ መወያየትና መደራደር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
በዚህ ረገድ፣ ከዚህ ቀደም በርካታ ሙከራዎቸ ተደርገዋል፤ የተሳኩም አሉ። በ2001 ዓ/ም በሃገሪቱ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የምርጫ ስነምግባር ደንብ ለመቅረጽ የተካሄደው ድርድር ስኬታማ ከሆኑት መሃከል አውራው ነው። ይህ ድርድር የስነምግባር ደንቡን በስምምነት በመቅረጽ አልተገደበም። በድርድሩ ላይ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከድርድሩ ያገኙት ልምድ ላይ በመመስረት፣ ሌሎች ሃገራዊ ጉዳዮችም ላይ ድርድርና ውይይት በማካሄድ ሁሉም የሚስማሙበት መፍትሄ ለማበጀት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲቋቋም ተስማምተዋል። ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሃገር አቀፍና በክልል ደረጃ በሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተመስርቶ እየሰራ ይገኛል። የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሃገሪቱ የፖለቲካ መህዳር መስፋት የተወሰነም ቢሆን አስተዋፅኦ አበርክቷል። አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን በምርጫ ስነምግባር ደንቡም ላይ መደራደር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል መሆንንም እንደ ሽንፈት ቆጠርው ራሳቸውን አግልለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መስራትን በተመለከተ በቤተመንግስት ተዘጋጅቶ በነበረው መድረክ ላይ፤
ከፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ የወጣችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወደመድረኩ እንድትመለሱና ያሉብንን ችግሮች በጋራ ለመፍታት የያዝነውን ቁርጠኛ አቋም እንድትደግፉ። ሰላማዊ መንገድን ተከትለው መደራደር ለሚፈልጉ ሌሎች ወገኖቻችንም ኢህአዴግ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ።
በማለት የድርድርና ምክክር ጥሪ አስተላልፈዋል።
በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ያደረጓቸው ጉዳዮች ላይ ድርድር አካሂደው መተማመን መፍጠራቸው የፖለቲካ ምህዳሩን ለመስፋትና ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ወሳኝ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከድርድር በመውጣት የመንግስትን ገጽታ በማጠየም ሊገኝ የሚችል ድጋፍ ፍለጋ ከመሸሽ መቆጠብ አለባቸው። ወደድርድር ገብተው ሰፊና መተማማን ያለበት የዴሞክራሲ ምህዳር በመፍጠር የሚያገኙት ድጋፍ ከድርድር በመሸሽ ከሚያገኙት የተሻለና ጠቃሚ መሆኑንም ማሰብ አለባቸው።
በአጠቃላይ፣ የአንድ ሃገር የፖለቲካ ወይም የዴሞክራሲ ምህዳር የሚሰፋው በመንግስትና ስልጣን ላይ ባለው የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ አይደለም። የፖለቲካ ወይም የዴሞክራሲ ምህዳርን መስፋት የሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድርሻ ነው። በመሆኑም፣ የሃገሪቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጠ-ዴሞክራሲያቸውን ከመገንባት ጀምረው በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በድርድርም ይሁን በምርጫ ላይ ሰላማዊ ተሳትፎ በማድረግ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ ወርቃማው እድል አሁን ነው።