Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጋራ ቁርኝት—ለአገር ዕድገት

0 256

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጋራ ቁርኝት—ለአገር ዕድገት

ዳዊት ምትኩ

በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዶክተር አብይ አህመድ ሚና እንደ አመራር ከፍተኛ ነው። ይሁንና ሁሉንም ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም መሪ ድርጅታቸው ብቻ ይሰሩታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ሁሉም ነገር በእነርሱ ብቻ መፈፀም አለበት የሚል እሳቤ ህዝቡ መያዝ የለበትም። ምልዓተ ህዝቡ ከእሳቸውና ከመሪ ድርጅታቸው ጎን ተሰልፎ የራሱን ሚና መጫወት ይኖርበታል። በአገራችን ውስጥ የታሰበው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በዚህ ዓይነቱ የጋራ አሰራር ነው። ይህ የህዝቡ፣ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና የድርጅታቸው የጋራ ቁርኝታዊ አሰራር ለአገር እድገት ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም።

በየትኛውም አገር ውስጥ የህዝብ ተሳትፎን የሚተካው ነገር የለም። መንግስት ያለ ህዝቡ ድጋፍ ብቻውን ሊያደርገው የሚችለው አንዳችም ነገር የለም። ታዲያ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ተግባሩን መወጣት ካልቻለ፤ በፖለቲካል-ኢኮኖሚው ምህዳር ውስጥ ሊመጣ የሚችል ለውጥ አይኖርም። እንደሚታወቀው ሁሉ ገዥው ፓርቲና መንግስት እዚህ አገር ውስጥ ያለው ችግር የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር መሆኑን ገልፀዋል። ህዝቡ ይህን የህዳሴያችንን ጉዞ አደናቃፊ ተግባር ከመንግስት ጋር በመሆን አመለካከቱንና ተግባሩን ለመቀነስ ብሎም አቅም በፈቀደ መጠን ለመቅረፍ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መረባረብ ይኖርበታል።

ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ህዝቡን በሰላማዊ መንገድ የማታገል ሂደትን ሊከተል ይገባል። ህዝቡ እዚህ ሀገር ውስጥ በሚከናወኑ መንግስታዊ ስራዎች የሚያሳየው ያለመርካት ስሜትና በዚህም ሳቢያ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ለሰላማዊ ትግል በር የተከፈተለት ነው። ታዲያ ይህን ስሜት በሰከነና በተደራጀ እንዲሁም ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም ስሜት መምራትና የሚጠናከርበትንም መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል። በተለይም ይህን ህዝባዊ ስሜት በፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ላይ በማዋል ውጤት ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ማንኛውም ዜጋ ጥያቄዎችን በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚያቀርብበትን አሰራርና መብት እንዳስቀመጠ በሚገባ ይገነዘባሉ። በተለያዩ ጊዜያትም ይህን መብታቸውን እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ይህም ጠያቂ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል መፍጠር መቻሉን የሚያሳይ ነው።

ሆኖም ይህን መብታቸውን በሰላማዊ ትግል የሚያጠናክሩነትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም የህዝቡን ፍላጎት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ጋር ነጥሎ በመመልከት ሰላማዊ ትግሉን ማጎልበት ከማንኛውም ጊዜ በላይ ጊዜ ዛሬ ትርጉም ያለው ስራ ማከናወን ያስችላል።

የጠያቂውን ህዝብ ስሜት በአግባቡ በመገንዘብ የሚያቀርባቸውን ችግሮች በፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ላይ ማዋል ከተቻለ ውጤቱ የትየለሌ ሊሆን እንደሚችል ግልፅ ይመስለኛል። በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ መብትን ያጠናክራል፤ በሌላ በኩልም የህዳሴ ጉዟችን ደንቃራ ሆኖ ሊያደናቅፈን የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን በተቻለ መጠን ለመቅረፍ ያስችላል።

ርግጥ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና ህገ መንግስታዊ መፍትሔ መሻት የዜጎች ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ታዲያ ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በፅንፈኞች እንዲሁም በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች ተጠልፎ ህገ ወጥ በሆነ መስመር እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ፅንፈኞችና ፀረ-ሰላም ሃይሎች ዛሬ ጠያቂ ለሆነው ህዝብ ያስገኙለት አንዳችም ዓይነት ፋይዳ የለም።

እነዚህ ሃይሎች ሰላሙን አጥቶ የየዕለት ተግባሩን እንዳያከናውን እንዲሁም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ አማካኝነት በተለይም ባለፉት 16 ተካተታይ ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ከማስተጓጎል ውጪ ያመጡለት ነገር የለም። ይህ ሃቅ ከጠያቂው ህዝብ የሚሰወር አይደለም።

በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ላይ ይህን ጠያቂ ህዝብ በበለጠ ማሳተፍ የትናንት የልማት ስኬቶችን አቅቦ ከመቀጠል እንዲሁም መጪውን የህዳሴ ጉዞ ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ ነው። ይህን ደግሞ ጠያቂው ህዝብ በሚገባ ያውቀዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የሀገራችን ህዝብ የዛሬ 16 ዓመት በፊት የተቀጣጠለው የተሃድሶ ንቅናቄ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ፈጣን በሆነ ሁኔታ የተቀየሰና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደነበር የሚያውቅና ለዚህ ዕውን መሆንም የተንቀሳቀሰ ነው። ለውጥ ማምጣትም ችሏል።

የለውጡን ትክክለኛነትና ጥንካሬን ለማረጋገጥም በ50 ዓመት ታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ አጋጥሞን፤ ይህ ነው የሚባል የውጭ ድጋፍ ሳይገኝ በራስ አቅም መቋቋም መቻሉ ማሳያ ይመስለኛል።

በተለይም በሶስተኛው ሚሊኒየም መባቻ ባሉት 10 ዓመታት ውስጥ በከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረቶችን ማስፋፋት መቻሉ ከህዝቡ የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። በተለይም በከተሞች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮግራሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። ምንም እንኳን በከተሞች ያለው የተጠቃሚነት ሁኔታ በተለያዩ ስንክሳሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ባይቻልም፣ ከፕሮግራሞቹ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደተቻለ ህዝቡ በሚገባ ያውቃል።

ከህዝብ የተሰወረ ነገር ባለመኖሩ ባለፉት 10 ዓመታት ዜጎች ከልማቱ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማህበራዊ መስክ ውጤት የተገኘባቸው ስራዎች መከናወናቸውን የሀገራችን ህዝብ የሚዘነጋቸው አይደሉም።

በተለይ በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ-ልማት አቅርቦት ዘርፍ የተከናወኑት ወሳኝ ስራዎች ለዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው። ከእነዚህ ማህበራዊ መስኮች ህዝቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ በአኗኗር ዘይቤው ላይም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ተደርጓል። ስኬቶችም ተመዝግበዋል።

እነዚህ ስኬቶች የተገኙት ህዝቡ ባደረገው ርብርብ ነው። ስኬቶቹ በኪራይ ሰብሳቢዎች ምክንያት ግለታቸውን ጠብቀው እንዳይጓዙ እንዲሁም መጪውን ዘመን የከፍታ ማማ ላይ ሆኖ እንዳይመለከት የጠራራ ፀሐይ ግርዶሽ እንዲሆኑበት አይሻም። እናም ይህን ህዝብ በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ላይ በበለጠ ሁኔታ ማሳተፍ ውጤቱ የህዳሴውን ችቦ በአስተማማኝ ሁኔታ ማቀጣጠል መሂኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርታል።

እርግጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አስተሳሰብ በአንድ ጀንበር የሚቀረፍ አይደለም። ትግልንና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማረም የሚጠይቅ ነው። ሆኖም የልማቱና የህዳሴው ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ህዝብ በፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው በቁርጠኝነት እስከተሳተፈ ድረስ ችግሩን መቅረፍ የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም።

አገራችን በምትከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች በሁሉም ዘርፎች የተገኙት መልካም ውጤቶች ለህዳሴ ጉዟችን ፅኑ መሰረት እየጣሉም ናቸው። እናም ፖሊሲዎቹን ተመርኩዞ የተዘጋጀው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ የሶስተኛ ዓመት ትግበራ በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር መጓተት አይኖርበትም። ይህን እውን ለማድረግም ህዝቡ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ቀዳሚ ተዋናይ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ይገባል።

ችግሩን በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወይም በመሪ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ላይ ብቻ መጣል ምንም ዓይነት ውጤት አያመጣም። ዛሬም ይሁን ነገ የህዝቡ የጠያቂነት ስሜት መጎልበት አለበት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም ኢህአዴግን ህዝቡ በማገዝ ለአገራዊ ዕድገት በጋራ መስራት ያለበት በእንዲህ ዓይነቱ የህዳሴ ጉዞ አደናቃፊ ተግባር ላይ ርብርብ በማድረግ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቱ የጋራ ቁርኝት ሲኖር፤ አገር ታድጋለች፤ ትበለጽጋለች። በአሁኑ ወቅት እየገነባነው የመጣነው አገራዊ የገፅታ ግንባታም ሳይስተጓጎል ግለቱን ጠብቆ ይጓዛል።      

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy