Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያልተገነዘብናቸው ቁም ነገሮች

0 369

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያልተገነዘብናቸው ቁም ነገሮች

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

በዚህ ፅሑፍ ሁለት ቁም ነገሮችን አነሳለሁ። በፌዴራሊዝም ውስጥ ስላገኘናቸው፣ ግን በቅጡ ስላልተገነዘብናቸው ጉዳዩች። አንደኛው ስርዓቱ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጡን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሀገራችን ህዳሴ ውስጥ ያሳረፈውን የማይፋቅ አሻራ የተመለከተ ነው።

ፌዴራሊዝም በዋነኛነት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የኃይማኖቶች እኩልነትን አረጋግጧል፡፡ ዜጎች ቋንቋቸው፣ ባህሎቻቸው፣ ታሪኮቻቸውና የማንነት መገለጫዎቻቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው እኩል እድል መፍጠር ማለት ነው፡፡   

ያለፉት ሥርዓቶች በሕዝቦች መካከል የፈጠሩት ጥርጣሬና መራራቅን በማስወገድ ኢትዮጵያ ሁሉም ማንነቶች እኩል የሚስተናገዱባት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቤተሰብ እንድትሆን በዓይነቱ የተለየ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከታሪካቸው የወረሱትን በጎ ትስስር በማጎልበት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አዲስ የሕዝቦች ግንኙነት መፍጠር ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ መሠረታዊ አስተሳሰቦች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በአዲስ የግንኙነት መሠረት የመገንባት ጉዳይ የሁሉም ማንነቶች የጋራ እቅድ ነው፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲኖራቸው በማድረግ በኢትዮጵያ እድገትና ሥልጣኔ ላይ እንዲረባረቡ የሚያስችላቸው ምህዳር መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አዲስ ግንኙነት ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሰፊ አቅምና ጠንካራ ጉልበት እንዲኖር ያስችላል፡፡ የጋራ አስተዳደር የተፈጠረበት አንዱ መነሻ እምነትም ሁሉም ማንነቶች የኢትዮጵያ ባለቤቶች ለማድረግ ነው፡፡ እንዲሁም ማንነቶች በአካባቢ ጉዳዮችና እነሱን በሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ወሳኞቹ እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእለት ተእለት አኗኗራቸውንና የወደፊት ሕይወታቸውን በሚወስኑ አጀንዳዎች ላይ የሚወስንላቸው ከላይ የሚጫን ኃይል እንዳይኖር አደርጓል፡፡

ባለፉት መንግሥታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ የተነሳበት ዋናው መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓት ልዩ ባህሪያት የሚባሉት ያለፉ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማስተካከል የተደነገጉ የአገሪቱን ተጨባጭ ህብረተሰባዊ መዋቅሮች የሚያንፀባርቁ ወይም ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱን አወቃቀር የሚወስኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የሰፈሩ የሥርዓቱ ልዩ ባህሪያት የመነጩበት አስተሳሰብ የሕዝብ ልዕልና ወይም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዕልና መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፉት የዘውድና ወታደራዊ አገዛዝ ዘመናት በአገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ የተቆጠሩበት ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶችን አሳልፈዋል፡፡ የወቅቱ ገዥዎችና አገልጋዮቻቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዕድል ለመወሰን የተቀመጡ አምባነገኖች ነበሩ፡፡ ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚጠበቅ አንድ መሠረታዊ ጉዳዮ የጥቂቶችን ልዕልና ያሰፈነውን ያለፈውን ሌጋሲ በማስወገድ የሕዝቦችን ልዕልና ማረጋገጥ ነው፡፡

አገሪቱ የምትመራባቸው መሠረታዊ መርሆዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች የሚመነጩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎቶችን ለማሟላት በመሆኑ እያንዳንዱ የመንግሥት እንቅስቃሴ ከዚህ አንፃር የሚቃኝ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን፣ መንግሥት የሚያራምዳቸው እምነቶች፣ የሚከተላቸው መርሆዎችና ፓሊሲዎች ምንጭ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡

በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት እየተተገበረ ነው፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የግል መብቶችን ለማረጋገጥ ወሣኝ ነው፡፡ የግል መብቶችን በማረጋገጥ ብቻ የቡድን መብቶችን ማረጋገጥ እንደማይችል፣ የቡድን መብቶችን የሚከለክል ሥርዓት የግለሰብ መብቶችን ብቻ በማስከበር የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊሆን እንደማይችል ይከራከራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ያደጉ የዴሞክራሲ አገሮች የቡድን መብቶችን በተሟላ መልኩ ባለመረጋገጣቸው ምክንያት የቡድን መብት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ የአገራቱን ውስጣዊ ሠላም በማናጋት ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት ልትሆን የቻለችው የቡድን ማንነቶች ማፈን ዋነኛ የጭቆና መገለጫ ስለነበር ነው።

ይህን ጭቆና በትግል በማስወገድ የራስ አስተዳደር መብትን በማረጋገጥ ብቻ የሚመለስ አልነበረም። ህገ መንግሥቱን በማፅደቅ ሂደት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችና ክርክሮች ይህንን ግልፅ ያደርጋሉ። የአንዳንድ ብሔሮች የፖለቲካ ድርጅቶች ከጅምሩ የመገንጠል ጥያቄ አንስተዋል፤ አንዳንዶች ደግሞ ነባሩ የተዛባ ግንኙነት በፈጠረባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና ምክንያት በሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አመራረጥ ሳይቀር በስፋት ተከራክረዋል።

ይህ የሚያመለክተው ከመገንጠል በመለስ ያለውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማረጋገጥ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእርግጥ የሚያረካ እንዳልነበረ ነው። በኢትዮጵያ ካለፉት 27 ዓመታት ተጨባጭ ተሞክሮ የምንረዳው ጉዳይ የመገንጠል መብት የብሔርና ተጓዳኝ ጭቆናዎችን ለማስወገድ ዋስትና ተደርጎ እንደታየ፤ ይህ መብት በህገ መንግሥት ከተደነገገ በኋላ ጥያቄውን ሲያነሱ የነበሩ ኃይሎች በህብረቱ መቀጠል መቻላቸውን ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አንዱ ልዩ ባህሪው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት በማረጋገጥ ህብረትን ማስቀጠል መቻሉን ነው።

ርግጥ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት የአመሠራረት ሂደት ሁለት ባህሪያት ያካተተ ነው። የደርግ ሥርዓት እንደተወገደ የነበሩና ቀጥሎ የተፈጠሩ የፖለቲካ ፖርቲዎች በመሠረቱ በብሔራዊ ማንነት የተደራጁ ሆነው የያዟቸው ዓላማዎችና ፍላጎቶች የተራራቁ ነበሩ። የአመሠራረቱ ሂደትም እነዚህን የተራራቁ ፍላጎቶች የነበሯቸው የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበውና ተሰባስበው በህብረቱ እንዲቀጥሉ የተስማሙበት፤ የሥርዓቱ ባለቤትነት፤ ቅርፁና መሠረታዊ መርሆዎቹ በድርድርና በስምምነት የወሰኑበት ሂደት ነበር።

የሥልጣን ክፍፍሉ በድርድርና በስምምነት ሲወሰን ማዕከላዊ መንግሥት እንዲኖርና ሥልጣኑም በህገ መንግሥቱ የተዘረዘረውን እንዲሆን የወሰኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካይ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች የሚያሳዩት አዲሱን ሕብረት የመሠረቱ ኃይሎች ከዳር ወደ ማዕከል በመሰባሰብ ፌዴሬሽኑን የመሠረቱ መሆናቸውን ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ በኢትዮጵያ ቀድመው ህልውናቸውን ያረጋገጡ መንግሥታት ስላልነበሩ ሥልጣን ከላይ ወደ ታች በማውረድ የተመሠረተ ሕብረት እንደሆነ የሚያሳይ ባህሪ አለው። እነዚህ የሥርዓቱ ባህሪያት በምሥረታው ወቅት ከነበሩ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች የመነጩና አገሪቱን ከማፈራረስ ያዳኑ ናቸው። ይህን እውነታ በተገቢው መንገድ መገንዘብ ይገባል።

እናም ይህ ሀገራችን ከብተና እንድትድን ያደረገ ሥርዓት ዕውን ከሆነበት ካለፉት 23 ዓመታት ወዲህ መቻቻልንና መከባበርን በመፍጠር ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ሆኖም በዚህ ጉዞው ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች በጥቂት ወገኖች አማካኝነት እዚህም እዚያም ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች አይኖሩም ተብሎ የሚታሰብ አይመስለኝም።

ሀገራችን ያለፈችባቸው ፊውዳላዊና አምባገነናዊ አገዛዞች በህዝቦች አብሮ የመኖር ባህል ውስጥ የፈጠሩት ስንክሳሮች ባሳለፍናቸው የጥቂት የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ዓመታት ብቻ ሊፈቱ አይችሉም። ተከታታይና  ትምህርት ያስፈልጋል። በተለይም የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታን በእጅጉ ማጎልበት ይገባል። ጊዜን ይጠይቃል። ለገዥው ፓርቲም ይሁን ለአመራሮቹ ተገቢውን ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። ያም ሆኖ በፍጥነት በመጓዝ ከስርዓቱ ያገኘናቸው ጥቅሞች እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy