Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ደብዛቸው እንዳይጠፋ

0 298

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ደብዛቸው እንዳይጠፋ

                                                        ታዬ ከበደ

ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ መሰረቱ የህግ የበላይነት መሆኑ ግልፅ ነው። የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላምን በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአካባቢና በአገር ላይ ማረጋገጥ አይቻልም። ልማት የሚባል ነገርም አይኖርም። እንዲያውም ቀደም ሲል የተገኘው ልማት የኋሊት እንደሚጎተት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ደብዛቻው ሊጠፋ ይችላል። እናም መብቶቻችን ደብዛቸው እንዳይጠፋ የህግ የበላይነት መከበር ይኖርበታል።

በአሁኑ ወቅት ህዝብና መንግስት ይህን ተግባር እያከናወኑ ያሉት ሰላምና መረጋጋት ለአንድ አገር ልማት ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ ስለሚገነዘቡ ነው። በመሆኑም ሁሉም ክልሎች ሰላማቸውንና መረጋጋታቸውን አሁን ካለው በላይ ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ ለአገራቸው ልማት ቀጣይነት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ያለባቸው ይመስለኛል።

ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ጉዳዩች ናቸው። ሰላም ከሌለ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ ዋጋ የሌለው ይሆናል። እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከድህነት ለመውጣት የምትታትር አገር ሰላምና መረጋጋቷን ማስጠበቅ ወሳኝ ተግባሯ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ህዝቦች አሁን የተገኘውን ሰላም ለማምጣት በአያሌው ታግለዋል። ሰላምን ጨምሮ የዘመናት ጥያቄያቸው የነበሩትን ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በርካታ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል። በቀደምት ስርዓቶች በርካታ ግፎች ቢደርስባቸውም፤ በመስዕዋትነታቸው በደላቸውን መሻር ችለዋል።

እናም በሰላምና መረጋጋት እጦት ይህ ትግላቸው እንዲቀለበስባቸው አይፈልጉም። መላው የአገራችን ህዝቦች በተለይም ያለፈው አምባገነናዊና ‘የሁሉም ችግሮች መፍትሔ ጦርነት ነው’ የሚለው ስርዓት የፈጠረውን እልቂት በሚገባ ስለሚገነዘቡ የሰላምን ዋጋ ያውቃሉ።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ እንደ ትናንቱ ጦርነት ያንዣበበትን የሰቆቃ ህይወት አይመሩም። በጆሯቸው ላይ የጥይት አረሮች አይጮሁም። ለአቅመ-አዳም የደረሱ ልጆቻቸው በግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ወደ ጦርነት አይላኩም። እነዚህ ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት የነበሩት ትውስታዎቻቸው በሰላም ትሩፋቶች ተሞልተዋል። ይህ አስተማማኝ የሰላም ምህዳርም የኋሊት እንዲቀለበስባቸው አይፈልጉም። እናም በልማትና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታቸው ላይ አተኩረዋል።

በተገኘው አስማማኝና ዘላቂ የሰላም ቁመና ታጅበውም ህዳሴያቸውን ዕውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል። በሰላማቸውና በመረጋጋታቸው ከፍታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ ሆነዋል። እናም እዚህም ሆነ እዚያ ይህን የሰላምና የመረጋጋት መንገድ ለመዝጋት የሚፈልጉ የውስጥም ይሁን የውጭ ሃይሎችን አይታገሱም።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተባብረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም ዕውን ሊሆን አይችልም።

እርግጥ የአገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም። ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ነው። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም።

የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሰላምነትን ማንገስ አይቻልምና። እናም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም። ይጠብቃቸዋል። ለፀረ ሰላም ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የዜጎች ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም።

ወጣቶች እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን ይሻሉ። ተጠቃሚነታቸውን ግን ማሳካት ያለባቸው በህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ማወቅ አለባቸው።

አገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል። ይሁን እንጂ ተጠቃሚነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ ከሁከትና ከብጥብጥ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ስለማይኖር በሰላም ጉዳይ መደራደር እንደማያስፈልግ ማሳወቅም ይኖርባቸዋል።

ሰላም ከሌለ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚመኘውን ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችልም። ሰላም ከሌለ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ማስፋትና ማረጋገጥ አይቻልም። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ከእነዚህ መሰረታዊ መብቶች ባሻገር ዋነኛውና በህይወት የመኖር ዋስትና ሊኖር አይችልም።

የሰው ልጅ በህይወት መኖር ካልቻለ ደግሞ ስለ ሌላው መሰረታዊ መብቶች ማሰብ ከጉንጭ አልፋነት የዘለለ ሚና ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። እናም ሁሉም ዜጋ ስለ አገሩ ሰላም ይበልጥ ማሰብና መጨነቅ ይገባዋል።  

እርግጥ ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለልማት መጠናከር ወሳኝ የሆነውን ሰላምን በጋራ ለማቆም መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ የውይይት ባህልን እየገነቡ መሄድም ያስፈልጋል።

እርግጥ ሰላምና ልማት ወዳዱ የአገራችን ህዝብ የእነዚህን አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች እኩይ ሴራን ጠንቅቆ ያውቃል። ከዚህ በፊትም ሰላሙን ለማናጋትና በሀገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በየደረጃው ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላትን አይፈልግም።

ሰላምን ተጻረረው በአገራች ላይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉ ሃይሎች ፍላጎታቸው የሰላም ሳይሆን የብጥብጥና የሁከት፣ የመብት ተጠቃሚነት ሳይሆን የመብት አዋኪነትና የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሁሉም በየደረጃው የሚጠቀምበት ሳይሆን የዜሮ ድምር ፖለቲካ መጫወትን፣ የመከባበርና የመቻቻል ሳይሆን የጠባብነትና የትምክህተኝነት እንዲሁም የነጻነት መንገድ ሳይሆን የባርነት ቀንበር መሆኑን ከአገራችን ህዝብ የሚሰወር አይደለም።

በመሆኑም አሁን የተገኘው ልማት በሰላምና መረጋጋት የመጣ መሆኑን ይበልጥ በማወቅ ለዚሁ የሰላም አውድ መትጋት ያስፈልጋል። ይገባልም። በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የሰላም እጦት በመንግስትና በህዝብ ቅንጅታዊ ስራ በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው።

ይህ ሁኔታም ወደ ተለመደው የልማት መንገድ ይወስደናል። ዴሞክራሲያችንንም ያፋፋል። እንደ አገር መቀጠል ያለብንን የህዳሴ ጉዞ ለማሳለጥ ያገለግላል። መጪው ጊዜያችንም ብሩህ እንዲሆን ያደርጋል። የልማት ስራዎቻችን ደብዛቸው እንዳይጠፋ በማድረግም የአፍሪካ አርአያ እንድንሆን ያደርገናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy