Artcles

…ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል!

By Admin

April 06, 2018

…ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል!

በዚህ ወቅት የሕዝቡንና የመንግሥትን ትግል ለማኮላሸት ታጥቀው የተነሱ ፀረ ሠላምና ጥገኛ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ርብርብ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ርብርባቸው ዳገት የማይወጣና የመጨረሻ መፍጨርጨር መሆኑ የታወቀ ቢሆንም የተወሰኑ አካላትን አሳስተው ወደ ችግር መክተታቸው አልቀረም።

በተለይ እስካሁን ድረስ ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ በነበረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ሂደት ሁለት ቦታ ረግጠው የነበሩ አካላት በየጊዜው ከየተቀበሩበት ሁሉ ሳይቀር ነፍስ ዘርተው እንዲነሱ አድርጓቸዋል፡፡ አሁን ግን ሕዝብና መንግሥት አንድ ሆነው የመረረ ትግል ለማድረግ እንደወሰኑ ገብቷቸዋል፡፡ ይህ የተደራጀ የሕዝብና የመንግሥት የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደማይለቃቸውና እንደሚጠራርጋቸው ሲገነዘቡ የአልሞት ባይ ተጋድሏቸውን ሞክረዋል፡፡  

በ1999 ዓ.ም በወጣው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ስትራቴጂ ላይ በፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ከሚገጥሙ ፈተናዎች አንዱ በኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ውሰጥ የሚደበቁ ትምክህትና ጠባብነት መሆናቸው በግልፅ ተቀምጧል፡፡

ሕዝቡ ከኪራይ ሰብሳቢነት ተጠቃሚ ባይሆንም ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ተፅዕኖ ውጭ ስለማይሆን ለመንግሥትና ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ባለህ ቀረቤታ ፍርፋሪ ይገኛል የሚል እምነት እንዲይዝ በሚያደርጉ ኃይሎች አስተሳሰብ ሥር እንዲወድቅ ስለሚደረግ በአካባቢ፣ በኃይማኖት፣ በብሄር ወዘተ…”ላንተ ቆመናል” በሚሉ አካላት አዝማሚያ ይኖረዋል ይላል፡፡

አሁን ባለንበት ወሣኝ ወቅት ላይ ኪራይ ሰብሳቢነትን የማድረቅና መልካም አስተዳደር የማስፈን ትግል ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ እዚህ ላይ ኢሕአዴግን ዕድለኛ ሊያሰኘው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ሕዝቡ እያንዳንዷን ክፍተት ለይቶ የመናገር ድፍረቱ በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ሕዝቡ በግልፅ እንዲናገር ህገ መንግሥቱ ያጎናፀፈው መብት ቢሆንም እንዲናገር ያስገደደው ግን ለአገሪቷ ልማት ካለው ቀና አስተሰሰብ  መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በየደረጃው በሚታዩ መድረኮች በሕዝቡ ውስጥ የሚስተዋለው ግልፅ አቋም በፍርፋሪ ሳይሆን በሥራና ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ ብቻ የአገሪቱ ዕድገት እንደሚረጋገጥ ግልፅ አቋም መያዙ ነው፡፡ ይህ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ለያዘ ድርጅት የሕዝብን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ አገር ለመምራት ስለሚረዳ ነው ኢሕአዴግን ዕድለኛ ነው ለማለት የሚቻለው፡፡

በዚህ ሂደት ግን ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሉ ያለ የሌለ አቅሙን በመጠቀም መሸሸጊያ ለማግኘት እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡ ለዓመታት ሕዝብን ከሕዝብ የማለያየት አጀንዳ ሲያራምዱ የቆዩ፣ በመካከላቸው ከፍተኛ ቅራኔ ያላቸው ትምክህተኛና ጠባብ ኃይሎች ሳይቀሩ አንድ ግንባር ላይ የተሰለፉበት ሁኔታ የመፈጠሩ ጉዳይ ለዚህ ሁነኛ ማሣያ ነው፡፡

መንግሥትና ሕዝብ በያዙት ቁርጠኛ አቋም የተደናገጡና በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ ሆኖ የነበሩ አካላት በትግሉ ሂደት ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ በመሆኑ ከወዲሁ ትግሉ እንዳይፋፋም ሣንካ በመሆን የመንግሥት ትኩረት ለማስለወጥ ሆን ብለው ያቀነባበሩት አጀንዳ ነው።

እነዚህ ፀረ ሠላም ኃይሎች በተለይ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ግብ የሌለው ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተለይ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ኃይሎች የጠባብነትና የትምክህት ያልተሳካ ጋብቻ በመፍጠር በሕዝብ አመኔታ ወደሥልጣን መውጣት ሲያቅታቸው የመጨረሻ ዕድላቸው በዚህ አመፅ ለማሳካት የሚሞክሩ ናቸው፡፡ ዋና መንደርደሪያቸው በየትኛውም መልኩ ሥልጣን በመያዝ አገሪቷን ለኒዮ ሊበራል ኃይሉ አሳልፎ በመስጠት የራሳቸውን የግልና የቡድን ጥቅም ማደለብ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢዎች አጀንዳ ለሕዝቡ ምንም ጥቅም ባይሰጥም ሕዝቡ በአካባቢና በኃይማኖት ወይም በሌላ ስሜት ሰለባ በማድረግ እነሱ ወደቀረፁት አጀንዳ በማስገባት መጠቀሚያ ለማድረግ በየጊዜው ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በሚቀይሱት መሰሪ አጀንዳ የሚወድመው ንብረትና ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች መኖራቸው እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም ተሳክቶላቸው ግን አያውቅም፡፡

ሁሌም አንግበው የሚይዙት አጀንዳ የሕዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ ባለመሆኑ ወደፊትም ቢሆን ይሳካላቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ መንግሥት የማረጋጋት ሥራውን እያከናወነ ለችግሩ ተጠያቂ የሚሆኑ ኃይሎችን ለሕዝብ በማጋለጥ ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። የሐሳቡ ጠንሳሽና አራማጆች በየምሽጋቸው ተደብቀውም አይቀሯትም፤ ለዚህም ነው ሕዝቡም እነዚህን ፀረ ሠላም ኃይሎች ዋጋቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዲያገኙ እየጠየቀ ያለው፡፡

የነዚህ የጠባብ ኃይሎች ዋና ዓላማ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ትግሉን መስተጓጎል ነውና ከማረጋጋት ሥራው ማግሥት መንግሥት ሕዝብን አሳትፎ እነዚህን ኃይሎች የማጋለጥ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ተግባርም ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን የልማቱን እንቅፋቶች ለመጠራረግ ተዘጋጅቷል፡፡ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሊገነዘቡት የሚገባ ነገር ቢኖር መቼውንም ቢሆን ከልማት ጉዟችን እንደማያስቆሙን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የህይወትና የአካል ጉዳት የጠየቀውን እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ዜጎቿ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሰፈነባት አገር መፍጠር ችለዋል፡፡ የምልዓተ ሕዝቡ የትግሉ ውጤት ደግሞ አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት በማስወገድ ዋነኛ ጠላታቸው ከሆነው ድህነት ፊት ለፊት በመግጠም የድላቸውን ውጤት ማጣጣም ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡

ገጠርን ከከተማ ያስተሳሰሩ ሰፋፊ የመሠረተ ልማትና የማህበራዊ ግልጋሎት አውታሮችን ግዙፍ ሃብት በመመደብ ልማትን ማፋጠንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውና የማህበራዊ ተቋማት መስፋፋታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ስትገለፅበት ከነበረው የድህነትና ኋላ ቀርነት ተምሣሌትነት ቀስ በቀስ  እያላቀቃት ይገኛል፡፡

በመጀመሪያው አምስት ዓመታት የተተገበረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ራዕይን ታሳቢ ያደረጉ ሁኔታዎች የተመቻቹበት ነው። የዕቅዱን የሁለተኛ ምዕራፍ ለመተግበርም ሌላ ዕቅድ ተነድፎና የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቅቆ ወደተግባር ከተገባ ሁለት ዓመት ተኩል አልፏል።    

በዚህ ዕቅድ መጠናቀቂያ ዘመን አገሪቱ ወደ ዝቅተኛው የመካከለኛ ገቢ ላይ ትደርሳለች ተብሎ ይገመታል። ይህም በ2017 ዓ.ም ትደርስበታለች ለተባለው የመካከለኛ ኢኮኖሚ የዕድገት ደረጃ መደላድል ይፈጥራል፡፡

በዚህ አመርቂ ጉዞ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የድል ታሪክ ግን አሁንም ዋነኛ ጠላቶች ከፊት ለፊቱ ተጋርጠውበት ይገኛሉ፡፡ ድህነት ዋነኛ አጀንዳ ነው። ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ኪራይ ሰብሳቢነት በተለይ በከተሞች ከባድ ፈተና እየሆነ መምጣቱ የሚደበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦችም በእያንዳንዷ የድህነት ማስወገድ ጉዟቸው ውስጥ ጉልበታቸውን ወደ ኋላ የሚጎትተውን አካል በጠላትነት ፈርጀው በጠላታቸው ላይ የተባበረ ክንዳቸውን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሕዝቡ የተቀናጀ የፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ወደ ኋላ የሚጎትቱ አመለካከቶችና ተግባራትን ለማስወገድና ሕዝቡ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ለመምራት አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ ጀምሯል።  በአጀንዳው ዙሪያም ሕዝቡ በሙሉ አቅሙ ለመሳተፍ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡ ሂደቱም ቀጥሏል። ውሾቹ ይጮሃሉ፤ ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል! አይደል የሚባለው።