Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህገ መንግሥታዊው ሥርዓት

0 320

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህገ መንግሥታዊው ሥርዓት

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓትን አቋቁማል፡፡ የዚህ ሥርዓት ዋና መለያ የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር፣ አደረጃጀት እና አሠራር ማቋቋሙ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን በመጠቀም በራሳቸው ነፃ ፍላጎት ባፀደቁት ህገ መንግሥት በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ዕድገቱ እንዲፋጠን ለማድረግ በሕግ የበላይነትና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት ዓላማ ያላቸው መሆኑን በግልፅ ቋንቋ አውጀዋል።

ለዚህ ዓላማቸው መሳካትም በህገ መንግሥቱ የግለሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ኃይማኖቶችና ባህሎች ያለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በፅኑ እምነት ተይዟል። እርግጥም ይህ ፌዴራላዊ ሥርዓት መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በህገ መንግሥታቸው የጋራ ጉዳዮቻቸውን በጋራ ለማስተዳደር፣ የፌዴራል መንግሥት መስተዳድርን ለማቋቋም፣ እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የማስተዳደር መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በሰፈሩበት መልክዓ ምድር ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት መንግሥታዊ ተቋማትን ለማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል መስተዳድሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት ምቹ ተቋማዊ ማዕቀፍን ፈጥሮላቸዋል።

ህገ መንግሥቱ እንደማናቸውም የፌዴራል መንግሥት ሥርዓት እንዳላቸው አገሮች ሁሉ የመንግሥትን ሥልጣን በሕግ አውጪ፣ በሕግ አስፈጻሚውና በዳኝነት አካላት መካከል ብቻ ሳይሆን ብዛት ባላቸው የሥልጣን ማዕከላት ማለትም በፌዴራልና በክልል መስተዳድሮች መካከል ያከፋፍላል። ባለፉት ሥርዓቶች ገቢራዊ ሆኖ የነበረው አሃዳዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ቅራኔንና መካረርን እንዲሁም የመበታተን አደጋን ፈጥሮ ነበር። ላለፉት 27 ዓመታት እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ግን በመፈቃቀድ፣ በየደረጃው ገቢራዊ በሚሆን እኩል ተጠቃሚነትና በክልሎች ሥልጣን ላይ በመመሥረቱ ለልማትና ለዴሞክሲያዊ አንድነት እንዲሁም ለሠላም ዋስትናን ፈጥሯል። እርግጥ በእነዚህ ዓመታት ብሔራዊ ጭቆናንና የአሃዳዊ ሥርዓት አስተሳሰብንና ተቋማዊ አደረጃጀትን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ በማስወገድ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ የፖለቲካ ማዕቀፍ መፍጠር መቻሉ የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ሥርዓት መገለጫዎች ናቸው ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ። እናም ይህን እርዓት እውን ያረገውን ህገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር የግድ ይሆናል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነው። እነዚህ ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በራሳቸው ነፃ ፍላጎት ያፀደቁትም ነው። ዛሬ 23 ዓመታት አልፎታል። ለዚህም ሲባል ነው፤ በህገ – መንግሥቱ መግቢያ ላይ “…እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” በማለት የእምነታቸው ማሰሪያ እንዲሆናቸው ቃል ኪዳን በመግባት ያረጋገጡት። ለዚህም ሲባል ነው፤ እነርሱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማይገሰስ የሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 8 ላይ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን ያወጁት። ለዚህም ሲባል ነው፤ እነርሱ በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ለመረጡት አካል ውክልና እንደሚሰጡ በማወጅ ህገ መንግሥቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑን በማያወላዳ ሁኔታ ያረጋገጡት። እናም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ መነሻ የሆነው ህገ መንግሥት የእነርሱና የእነርሱ ብቻ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ የሚገባ ይሆናል።  

በህገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገሪቱ ዘላቂ ሠላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን ለማድረግ በነፃ ፍላጎታቸው በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት ዓላማ አላቸው። መጪው የጋራ ዕድላቸው መመሥረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት የተቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋፊነት በፍትሃዊና ፈጣን ልማት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ በህገ መንግሥቱ ገልፀዋል።

በህገ መንግሥቱ ለዚህ ዓላማቸው መሳካት የግለሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ኃይማኖቶችና ባህሎች ያለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ አድርገዋል። ኢትዮጵያ የየራሳቸው አኩሪ ባህል ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር መሆኗን፣ የየራሳቸው መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበራቸውና ያላቸውን በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረው አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት አገር በመሆኗ ያፈሩት የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለው የሚያምኑ መሆናቸውንም በህገ መንግሥታቸው ላይ በማያሻማ ሁኔታ ደንግገዋል።

በህገ መንግሥቱ የሥልጣን ምንጭ ማዕከላዊ መንግሥት ሳይሆን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆናቸው ተገልጿል። ለራሳቸው በቂ ሥልጣን አስቀርተው ለጋራ ጉዳይ የሚያስፈልግ ሥልጣንን ለማዕከላዊ መንግሥት ቆርሰው ሰጥተዋል። ታዲያ እዚህ ላይ ኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ልየ ባህሪያት ያሉት መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ህገ መንግሥቱ የብሔሮች የብሔረሰቦችና የሕዝቦች እንደ መሆኑ መጠን፣ የህገ መንግሥት የበላይነትን ለማረጋገጥ ህገ መንግሥቱ በማናቸውም የመንግሥት አካላት ብቸኛ ውሣኔ ሊሻሻል እንደማይችል በማስቀመጥ አንዱ የሌላው የበታች እንዳይሆን ይከላከላል። የክልሎች ሃሳብ በፌዴራል ምክር ቤቶች እንዲወከሉ በማድረግም በፌዴራል የጋራ ጉዳዮች ውሣኔ አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል። ህግ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በመስጠት፣ በህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን የውሣኔ ሃሳብ አቅራቢነት የሚወሰንበትን ሥርዓት ህገ መንግሥቱ ዘርግቷል።

በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት የተመሠረተው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም በመሆኑ በግዛት ላይ የሰፈሩ ብሔራዊ ማኅበረሰቦች የራሳቸውን ጉዳይ በሚመለከት የራስ አስተዳደርና የጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አስተዳደር ሥልጣን እንዳላቸው ያረጋግጣል። ሌላኛው የህገ መንግሥቱ የተለየ ባህሪ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ማጎናፀፉ ነው። ይህም የፖለቲካዊ ሥርዓቱ ምሶሶ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህም መሠረት በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 39 (1) መሠረት ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው። እንዲሁም በህገ መንግሥቱ መግቢያ በመጀመሪያዎች ሁለት ተከታታይ አንቀፆች ላይ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የተስማሙትና ቃል ኪዳን የገቡት በነፃ ፍላጎታቸው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን በመጠቀም ነው። ይህም ስለ ኢትዮጵያ የፌዴራል ፖለቲካ ሥርዓት የሚደረጉ ማናቸውም ህጋዊ ውይይቶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ላይ የሚያጠነጥኑና የሚቆራኙ ውይይቶችን የግድ መጋበዛቸው አይቀርም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy