Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሰላም የተዘረጉት እጆች

0 283

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለሰላም የተዘረጉት እጆች

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሳለጠ ያለው ስርዓት በድቡሽት ቤት ላይ የተገነባ የሚመስለው የኤርትራ መንግስት በሀገራችን ውስጥ ተከስቶ የነበረውን ጊዜያዊ ችግር ተመልክቶ “የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳይ አበቃለት” በማለት ሲናገር ነበር። እንዲያውም በጊዜያዊ ችግሩ ወቅት በጉያው አቅፏቸው የነበሩ አሸባሪዎችንና ፀረ ሰላም ኃይሎችን “ስልጣን የምትይዙበት ወቅት አሁን ነው፤ ሄዳችሁ በሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች ጦርነት ክፈቱ” በማለት ምክር ሰጪ ሆኖ እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይናገራሉ።

ይህ የአስመራው አስተዳደር ግምገማ ግን የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እንዲሁም በፈቃዳቸው የመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት ጊዜያዊ ችግሮችን የመፍታት አቅም ያላቸው መሆኑን ካለመገንዘብ የመነጨ ነው። የኤርትራ መንግስት ይህን መሰሉን የማይሳካ ህልም ቁጭ ብሎ ከማለም ይልቅ፤ በአዲሱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበለትን የሰላም ጥያቄ መቀበል በተገባው ነበር።

ግና የኤርትራ መንግስት በባህሪው ጠብ አጫሪና ከሁከትና ከብጥብጥ ማትረፍ የሚፈልግ ነጋዴ በመሆኑ ለሰላም ቦታ ባይኖረው የሚደንቅ አይደለም። ምክንያቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተሾሙ ወዲያውኑ ላቀረቡት የሰላም ጥያቄ ላለፉት 20 ዓመታት በምክንያትነት ሲያቀርበው የነበረውን የድንበር ማካለል ጥያቄ አሁንም በማንሳት በሁለቱ ሀገራት መካከል መምጣት የሚገባውን ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር “በመጀመሪያ ባድመን መልሱልኝና ቀጥሎ እነጋገራለሁ” በማለት የልጅ ምላሽ በማቅረቡ ነው። የሰላሙን ሁኔታ አልተቀበለም። ይባስ ብሎ በተለያዩ ወቅቶች የኢፌዴሪ መንግስት ሻዕቢያን በኃይል ለማስወገድ ፍላጎት እንዳለው አድርጎ ሲገልፅ ይስተዋላል።

ምንም እንኳን የኢፌዴሪ መንግስት አቅሙ ቢኖረውም ሻዕቢያ አሁን ካለበት ዓለም አቀፋዊ መገለልና ውስጣዊ ድክመት ተነስቶ ‘የኤርትራ መንግስት ስለተዳከመ መወገድ አለበት’ የሚል አቋም የያዘበት ጊዜ የለም—ሊይዝም አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዴሞክራሲን በፅናት የሚከተል ሀገር መንግስት ሳይሆን የፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አቀንቃኞች ፍላጎት ነው። ለነገሩ በአንድ ሀገር ያለውን መንግስት የመቀየርም ይሁን እንዲቀጥል የማድረግ መብት የሀገሬው ህዝብ እንጂ፤ የጎረቤት ሀገር መንግስትና ህዝብ ተግባር ሊሆን አይችልም።

የኢትዮጵያ መንግስትም እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የጎረቤት ሀገር መንግስትን የማስወገድ ባህሪ ሊኖረው አይችልም። ይህ መንግስት ካፈጣጠሩ ጀምሮ በህዝብ ውስጥ ያደገ፣ የተፈጠረና ለህዝብ የቆመ በመሆኑ፤ ለኤርትራ ህዝብ ልዩ ከበሬታ አለው። ይህን ከበሬታውንም ያ ህዝብ በሻዕቢያ ችግር ሲደርስበት መጠለያ በመስጠትና ኢትዮጰያ ውስጥ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማሩ በማድረግ እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ድጋፎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሰርቷል፤ ዛሬም እየሰራ ነው። እናም ይህ መንግስት የዚህን ህዝብ መብቶች ይደግፋል እንጂ ያ ወንድም ህዝብ መስራት የሚገባውን መንግስቱን የመለወጥ ስራ ተክቶ ሊሰራ አይችልም።

እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ከምንም በላይ መንግስት በአስመራው አስተዳደር ላይ ዘመቻ እንዲያካሄድ ፍላጎታቸውን ሲገልፁ ይስተዋላሉ። አንዳንዶቹም መንግስት የሌላን ሀገር ሉዓላዊነት እንዲጥስና ‘ለምን አሰብን ወስዶ የወደብ ባለቤት አያደርገንም?’ እስከሚል ድረስ የዘለቀ አስገራሚ ጥያቄዎችን በመገናኛ ብዙሃን ሲያቀርቡ ይስተዋላል። እነዚህ ተቃዋሚዎች ብዙም ስለ ዓለም አቀፍ ህግና ከጎረቤት ጋር በሰላም በመኖር ስለሚገኙት የጋራ ጥቅሞች ብሎም አንድ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መከተል ስላለባቸው መርሆዎች እምብዛም ግንዛቤ ያላቸው አይመስሉም።

የአንድ ሀገር መንግስት ጎረቤቱ ምንም ያህል ፀረ-ዴሞክራሲያዊ  ቢሆን እንኳን እርሱን የማስወገድ መብት የለውም። ዓለም አቀፍ ህጉም አይደግፈውም። አንድ ሀገር የመጨረሻው አማራጭ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ሀገር ላይ ጦርነት በመክፈት ወረራ ከፈፀመ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ልክ እንደ ሻዕቢያ የመገለል ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት በመስራት ላይ የሚገኘው የኢፌደሬሪ መንግስት አቋም ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።  

የኢፌዴሪ መንግስት ለአካባቢው ሀገሮች ሰላም የቆመ ነው። የሰላምን መርህ በመከተል ከሰላም ከሚገኘው ጥቅም ሀገራትን በጋራ ተጠቃሚነት አቋም ለማስተሳሰር የሚሰራ ነው። ይህን ጥቅም የኤርትራ ህዝቦችም ሊጋሩት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ያለው ጠብ አጫሪ መንግሥት ቢያንስ ለሁለቱ ሀገሮች ፍላጎት ሲል ለሰላም የተዘረጉ እጆችን መጨበጥ ያለበት ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ምክንያቱም የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ይህን የዕድገት ትሩፋት የኤርትራ ህዝብም በመጋራት እንደ ቀጣናው ህዝቦች ተጠቃሚ መሆን ያለበት ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ የኤርትራ መንግስት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበውን ቀናዒ የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ቀጣናው ሀገራት የትብብር ምዕራፍ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

ሁከትና ብጥብጥ ለኤርትራ መንግስት ሹማምንቶች ካልሆነ በስተቀር ወንድም ለሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ ምንም የሚፈይድለት ነገር የለም። የኤርትራ ህዝብ ተጠቃሚነቱ በሰላም ውስጥ ብቻ እንደሚረጋገጥ የሚያውቅ ነው። ይህ ህዝብ ሌላው ቀርቶ እዚህ ሀገራችን ውስጥ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ መማር የቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሰላም ምክንያት እንደሆነ ጠንቅቆ ይገነዘባል። እናም ይህ ህዝብ የኤርትራ መንግስት የሚከተለውን የጠብ አጫሪነት ተግባር በመተው ወደ ሰላማዊ የድርድር ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ መጠየቅ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ።

የኢትዮጵያ መንግስት ሻዕቢያ አሸባሪ በመሆኑ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሃገሩ ህዝብ አይጠቅምም፤ ይህን መንግስት ልጨርሰውና እፎይታን እናግኝ ብሎ አልተንቀሳቀሰም። ግና ከማተራመስ እንቅስቃሴው እንዲታቀብ የዲኘሎማሲያዊ ስራዎች ላይ አተኩሮ በርካታ ተግባሮችን ከውኗል።

የኢፌዴሪ መንግስት ሁል ጊዜ ለሰላማዊ ድርድሮች ቅድሚያ መስጠቱ ታጋሽነቱንና አርቆ አሳቢነቱን የማያሳይ ነው። በአሁኑ ወቅት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያቀረቡት የሰላም ጥሪም የዚህ ባህሩው መገለጫ ይመስለኛል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቀረቡት የኢትዮጵያ የሰላም እጆች ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ትክክለኛው መንገድ ነው።

ከሰላም ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለም። በሰላም ውስጥ ሁለቱ ሀገሮች ሊጠቃቀሙ፣ በጋራ ሊያድጉና ሊበለፅጉ ይችላሉ። ሰላም ካለ የአንደኛው ዕድገት የሌላኛውም ይሆናል። የአንዱ መጠቀም ሌላውን ይጠቅማል። የሚጎዳ ወገን አይኖርም። እናም የኤርትራ መንግስት ለሰላም የተዘረጉትን የኢትዮጵያን እጆች ሊቀበል ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy