Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለችግሮቹ እልባት…

0 265

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለችግሮቹ እልባት…

ዳዊት ምትኩ

እንደ ማንኛውም አገር ኢትዮጵያ ውስጥም አልፎ…አልፎ ግጭቶች ይፈጠራሉ። የግጭቶች መኖር ነባራዊ ክስተት ነው። ግጭቶች ስለፈለግናቸው ወይም ስላልፈለግናቸው የሚከሰቱ አይደሉም። እርግጥ አንዳንዴ ከተለመደው ወጣ ያሉ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ።

ለችግሮቹ እልባት ግን የህግ የበላይነትን ተመርኩዞ መፍትሔ መሰጠት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ጠቅለል ባለ መልኩ ሰላማዊ ብትሆንም፤ በማንኛውም ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮችን ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ባማከለ መልኩ ከህግ የበላይነት አኳያ መፍታት ይቻላል።

በአሁኑ ሰዓት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ ባለቤቶችና ለሌሎች አፍሪካውያን አርአያ የሚሆን ዕድገት በሁሉም መስኮች እያስመዘገቡ ነው። በዚህም የህዳሴያቸውን ጉዞ ቅርብ ለማድረግ ግስጋሴያቸውን ተያይዘውታል።

ይሁን እንጂ በዚህ ሂደት ውስጥ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት ይበልጥ መስፈን ይኖርበታል። የመንግስት አሰራሮች ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መንፈስ እውን መሆን አለበት። ይህ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሀገሪቱ ህዝቦች መንግስት እንደያከናውነው የሚፈልጉት ጉዳይ ነው።

በመሆኑም መንግስት ሁሌም በአሰራሮቹ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም ስለሆነ በየጊዜው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የየወራት ስራዎቹን ያቀርባል። ያስገመግማል። መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላል።

የመንግስት የተጠያቂነት አሰራር የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው። በዴሞክራሲ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው።

ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው።

ስለሆነም የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 26 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ጅምር በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም። አሁን የምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም።

አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል። የአሰራሩን ተጠያቂነትና ግልፅነት በዚያኑ ልክ ለህዝቡ ማረጋገጥ ይኖርበታል።

ህገ መንግስታችን ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው። በመሆኑም ማንኛውም አዋጅ ሲወጣ ሁሉንም ዜጋ ይመለከታል እንጂ ለተለየ የህብረተሰብ ክፍል ተለይቶ አይደለም። ሁሉም ዜጋ አገሪቱ ያወጣችውን ህግ የማክበርና በእርሱም የመመራት ግዴታ አለበት።

በመሆኑም አንድ ግለሰብ ባለሙያ አሊያም የተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ ሙያውን ወይም የተቃዋሚ ፓርቲ አባልነቱን እንደ መከላከያ ምሽግ በመጠቀም ህገ ወጥ ተግባርን መፈፀም የህግ የበላይነት ገቢራዊ እንዳይሆን የሚያግድ አይደለም።

እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና አይኖረውም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ ወጥ ተግባርን ከፈፀመ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ መሆኑ ግልፅ ይመስለኛል።

ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው። ይህም የህገ መንግስቱን አንቀፅ 56 ላይ ተገልጿል። በአንቀጹ መሰረት በምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅት የፌዴራሉን መንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ተመልክቷል።

ይህም የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚፈጽማቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

አገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች የህግ የበላይነት ልዕልናን በማስጠበቅ  እልባት መስጠት ይቻላል። ቅሚያ ግን የህግ የበላይነት ልዕልና በማስጠበቅ በአገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ተግባራዊ ማድረ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች እንዲሸረሸሩ በር ሊከፍቱ ይችላሉ።

እንደዚህ ዓይነቶች የመብት መሸራረፍ ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ ያደርገዋል። ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል። ይህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል።

በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍ የህግ የበላይነት ሳይሸራረፍ መተግበር አለበት። ማንቸውም ግለሰብ ይሁን ቡድን የህግ የበላይነትን ተላልፎ ለፈፀመው ተግባር ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ ይገባል።

የህግ የበላይነትን ተጠያቂነትና ግልፅነት በሰፈነበት ሁኔታ መተግበሩ የዜጎችን አመኔታ ያተርፋል። ህግ ለሁሉም መስራት አለበት የሚለው ሁሉን አቀፍ ድንጋጌ በተጨባጭ መረጋገጥ ይኖርበታል።

ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ይህን የማድረግ አቅምና ብቃት አለው። በአፈፃፀም ረገድ የተስተዋሉት ችግሮች እንዳሉ ሆነው፤ ወደፊት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ መንግሥት ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ የገባውን ቃል ይተገብራል የሚል እምነት አለኝ።

አገራችን ውስጥ ማናቸውንም ችግሮች የህግ የበላይነትን በሚያረጋግጥ ሁኔታ በግልፅነትና በተጠያቂነት መንፈስ እልባት የማይሰጥበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ምክንያቱም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ይህን ማድረግ የሚያስችሉትን አሰራሮች ላለፉት 27 ዓመታት ያጎለበተ ስለሆነ ነው።

ይሁን እንጂ መንግሥት ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም። የህብረተሰቡ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ህብረተሰቡን አልባ ምንም ዓይነት የህግ የበላይነት ተግባርን ሊያረጋግጥ አይችልም። ህብረተሰቡ የመንግሥት ማናቸውም ክንዋኔዎች በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ እንዲከናወኑ የሚሻውን ያህል የህግ የበላይነት በአገሪቱ ውስጥ እንዲረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የተለመደውን እገዛውን ይበልጥ አጠናክሮ መገኘት ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy