Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምን ያህል ጥናት ተካሂዶባቸዋል?

0 358

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምን ያህል ጥናት ተካሂዶባቸዋል?

                                                         ታዬ ከበደ

በአገራችን ውስጥ አንድ ኢንቨስትመንት በሆነ አካባቢ ሲገነባ ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። እስካሁን ባለው ሂደት ግን በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ‘ተጠቃሚ አልሆንም’ ከማለት ባለፈ፤ ‘ከመሬታችንም አፈናቅለውናል፣ ጤናችንን ጎድተውናል’ በሚል ከተቃውሞ እስከ ሁከት የደረሱ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ መጥተዋል።

ይሁን እንጂ፤ ምንም እንኳን የኢንቨስትመንት ሥራዎች አገርን የሚለውጡ ቢሆኑም፤ ምን ያህል ጥናት ተካሂዶባቸው ለባለ ሃብቱ ፈቃድ እንደሚሰጥ ማረጋገጥ ይገባል። በመሆኑም መንግሥት በአገር ውስጥ የሚከናወኑ ማናቸውም የኢንቨስትመንት ተግባሮች ባለ ሃብቶችን በማያሸሸ ሁኔታ ጥናት እያደረገ ልማትን ማከናወን ይኖርበታል። ይህም የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲጎላና ተጎጂነት እንዳይኖር እንዲሁም የአገርን ልማት በእኩል መንገድ ለማስኬድ ያስችላል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንቨስትመንትን በመሳብ ቀዳሚ እየሆነች ነው። በሀገር ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለሃብቶች ለተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎችን ወጣቶች ተደራጅተው ግብዓት እንዲያቀርቡ የተደረገው ጥረት ፍሬ ማፍራት ጀምሯል።

መንግስት በአገራችን እያካሄደ ባለው የኢንቨስትመንት ተግባር ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ተፈላጊ እንድትሆን ያደረጋት ነው። ሀገራችን የምትከተለው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ለተፈላጊነቷ መጨመር ምክንያት የሆነ ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል። ልማታዊ ዲፕሎማሲውም እየተጠናከረ ነው። በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር እየሰራች ነው።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል።

ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እንዲሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። ሀገራችን የምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አሁን ለተገኘው የኢንቨስትመንት አመቺነት ምህዳር ወሳኙን ሚና መጫወቱ ግልፅ ነው።

መንግስት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ። ከመመስከር ባለፈም፤ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ አጢነው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ በልማት እግሮቻቸው ወደ ሀገራቸን እየተመሙ ነው።

እንደ እኔ እምነት በሀገራችን ውስጥ እየደገ የመጣ፣ ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመሩ፣ ፈጣን የከተሞች ዕድገት መታየቱና ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር መኖሩ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው።

በተጨማሪም ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ስለሆነችና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ ፈጣን ምጣኔ ሃብት ውስጥ የፋይናንስ፣ የቴሌኮም እና የጅምላ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች የተከለከለ ነው። ይህም የሀገራችን የፋይናንስና ለሌሎች ተቋማት ራሳቸውን እስኪያጎለብቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ተወዳዳሪ እስኪሆኑ ድረስ እንዲሁም መንግስት በተመረጠ አኳኋን በልማት ስራው ላይ ስለሚሳተፍ ነው።

ይሁንና የውጭ ባለሃብቶች በማዕድንና ኢነርጂ፣ በሲሚንቶ፣ በቡና፣ በወይን እና በብስኩት ማምረት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መገኘታቸው ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

አገራችን ያላት የተረጋጋ ሥርዓት እና ርካሽ የጉልበት ክፍያ እንዲሁም ለባለ ሃብቶች የተዘጋጀው የተሻለ የታክስ ድጎማና የእፎይታ ጊዜ ብሎም በታዋቂው አየር መንገዷ የዓለም ገበያን በቀላሉ ለመድረስ መቻሏ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን አድርጓታል።

እንደሚታወቀው ከውጭ የምናስገባው ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሀገራችን ውስጥ የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው። የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንንም ያጎለብተዋል። ይህ ግኝታችን የሀገር ኢኮኖሚን በማጎልበት ኢትዮጵያ ላለመችው መካከለኛ ደረጃ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ ዕቅድ በር ይከፍታል።

በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ተግባሮችን መንግስት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

መንግሥትና የግሉ ባለሃብት በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች በመከተል ላይ ይገኛል። መንግሥት የገበያ ጉድለቶችንና ተያያዥ የኪራይ ምንጮችን ለመዝጋት በመሰረተ ልማት እና በሰው ሃብት ልማት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

እርግጥ ለአገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

በመንግስት በኩል መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል።

መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየታየባቸው መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ነው።

የመንግሥት ደጋፊ ተቋማት አቅም ለማሳደግ የፋብሪካዎች የቴክኖሎጂና የማኔጅመንት አቅም ካደገ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከባለሃብቱ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውና ለመፍትሔውም በጋራ መሰለፋቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ግልፅ ነው።

በማዕድንና ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ፕሮግራም ላይ የሚፈሰው ገንዘብ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር እየሆነ ነው። ለዚህ ስራ አመቺነትም በመሰረተ ልማት ዘርፍ የሀገሪቱን የመንገድ አውታር ለማሳደግና ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት ሳይጠቀስ አይታለፍም። እነዚህ ሁሉ ተግባራት በአሁኑ ወቅት ወደ አገራችን የሚፈሰውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚያጠናክሩ ናቸው።

ይሁን እንጂ አገራችን እያስመዘገበች ያከችው የኢንቨስትመንት እመርታ እንዳይስተጓጎል ብርቱ ጥረት ማድረግ ይገባል። በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የማያደናቅፉ ተግባሮችን መከላከል ያስፈልጋል።

ማንኛውም ኢንቨስትመንት የሚከናወነው የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው። ኢንቨስትመንቶች ሲሰጡ የአካባቢውን ማህበረሰብ ምን ያህል እንደሚጠቅሙ፣ በሰውና በአካባቢ ላይ ሊያስከትሉት የሚችሉት ጉዳትና ተፅዕኖ በቅድሚያ መጠናት ይኖርባቸዋል። ከዚያም በኋላ በሳይንሳዊ መንገድ የሚመለከታቸው አካላት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። ይህም የአገራችንንና የህዝቧን ተጠቃሚነት እንዲሁም ሰላሟን ለማረጋገጥ ሌላኛው እርምጃ ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy