Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላማቸው፣ ሰላማችን…

0 240

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላማቸው፣ ሰላማችን…

ዳዊት ምትኩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአጎራባች አገራት በማካሄድ ላይ ያሉት ጉብኝቶች በአካባቢያችን ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሁም ልማታችንንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችንን የሚያግዝ መሆኑን የሚያስረዳ ነው። ጉብኝቶቹ የአገሮችን የጋራ ተጠቃሚነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ከማጠናከር አኳያ የጎላ ፋይዳ ያላቸው ናቸው።

ጉብኝቶቹ ከአገራችን የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አኳያ ታቅደው የተከናወኑ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎበኟቸው አገራት ሰላማቸው፣ ሰላማችን፤ ልማታቸው፣ ልማታችን በመሆኑ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። እንዲሁም ጉብኝቶቹ ተደማሪ አቅም ፈጣሪዎች ናቸው።   

የኢፌዴሪ ህገ- መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሠላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ኢትዮጵያ በምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጠንካራ የትብብር ምዕራፎችን የከፈተ ነው። ይህም በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተወሰደ ርምጃ ነው፡፡ ተግባሩም ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ወዳድ ህዝቦች መልካምና ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡

የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር ተመርኩዞ የተዘጋጀውና በአሁኑ ወቀት ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ላይ ብሎም ሀገራዊ ህልውናችንን እያረጋገጠ ብሎም ለጎረቤቶቻቸን መድን የሆነው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ የውስጥ ችግሮቻችንን በመቅረፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በጋራ ጥቅም እና ሰላም ላይ እንዲመሰረት ያደረገ ነው። በመሆኑም በቅርብ ጊዜ ካጋጠመን ጊዜያዊ ስንክሳር ውጭ አገራችን ሰላማዊ ልትሆን ችላለች።

በዚህም ምክንያት የኢፌዴሪ መንግስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀጣናው ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ ልማታዊ ትስስር እንዲጎለብት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ውጤትም እያገኘበት ነው።

በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በየብስ፣ በባቡርና በሌሎች የመሰረተ-ልማት አውታሮች ቀጣናውን ለማስተሳሰር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ተጠቃሽ ናቸው። እናም መንግስት የቀጣናው ህዝቦች መቸገር አገራችን እንዲኖር የምትሻው ቀጣናዊ የልማት ትስስር እንዳይኖር ያግዳል ብሎ ስለሚያምንም  ጭምር ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን የትስስር ሁኔታ ሲከውን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው ሁለት መሰረታዊ ሁነቶችን ተከትሎ ነው፤ ውሰጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን። መንግስት አገራዊ ህልውናን የማስጠበቁ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል።  

በከፍተኛ ኋላ ቀርነትና የድህነት አዘቅት ተዘፍቃ ለቆየችው ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታና ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ላለፉት 27 ዓመታት ተጉዟል።

ባለፉት 16 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም የማስፈን፣ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን እውን የማድረግ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ተግባሮችን ከውኗል።

አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ መንግስት ለአገራችን ሰላምና ልማት እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ፅኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ የአገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ ይህ እንዲሆን መንግስት ከራሱ አገር ህዝቦች አልፎ ለአጎራባች አገራት ህዝቦች ማሰብ ይኖርበታል። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበት ሰፊ ጥረት አድርጓል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የቀጣናውን ዜጎች በስደተኝነት ተቀብላ በማስተናገድ ጊዜያዊ እፎይታን እንዲያገኙ ትብብር በማድረግ ላይ ትገኛለች።

የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተላቸው ማናቸውም ፖሊሲዎች ህዝብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ቅድሚያም ለህዝብ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሚሰጡና የሚጨነቁ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ውስጥ አድጎ በህዝብ የሰላ ትችት እየተመራና ራሱን በራሱ እያረመ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ ህዝባዊ ወገንተኛ ነው።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል። ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል። በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከርም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲጨምር እየሰራች ነው።

የአገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 27 ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል። በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረትም በቀጣናው ካሉት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራ መንግስት በበዓለ ሲመታቸው ላይ የሰላም ጥሪን ቢያቀርቡም ወትሮም ከሁከትና ከብጥብጥ ትርፍ ማግኘት በሚፈልገው የተሰጠው ምላሽ ቀና አይደለም። ያም ሆነ አገራችን ለሰላም ከምትሰጠው ዋጋ በመነሳት አሁንም ከኤርትራ ጋር ለሚኖራት የሰላም ግንኙነት ጠንክራ ትሰራለች።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy