Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“በመደመር…”

0 366

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“በመደመር…”

ገናናው በቀለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል ለመላው ኢትዮጵያውያን “በመደመር አገራችንን እናልማ” ካሉበት ጊዜ አንስቶ የመጣው ለውጥ እጅግ የሚያስገርም ነው። የላቀ የአንድነት መንፈስ እየመጣ ነው። ሰላም እየተረጋገጠ ነው። ዴሞክራሲውም በውጭ የሚኖሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጭምር በመጋበዝ እየተጋጋለ ነው። ፈር ቀዳጅ ጅምሮች በርካታ ናቸው።

በንግዱ ዘርፍም የነበረው መቀዛቀዝ እየተስተካከለ ነው። በገቢና ወጪ ንግዱ መካከል ያለው አለመመጣጠን የሚታወቅ ቢሆንም እርሱንም ለመፍታት እየተሰራ ነው። በአገራችን እየተከሰተ ያለው የዋጋ የዋጋ ንረት መንስኤ ቢኖረውም፣ ይህንንም ለመካላከል ተግባራዊ ጥረት እየተደረገ ነው።

እርግጥ መንግስት የዋጋ ንረትን ለመፍታት ጥረቶችን እያደረገ ነው። እንደሚታወቀው መንግስት ከመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ስርጭት አኳያ ስንዴን፣ ዘይትንና ስኳርን ጨምሮ እና የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት የዋጋ ቁጥጥር እያደረገ ነው። የምንዛሬ ማሻሻያውን ተከትሎ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክና የውሃ ታሪፍ ጭማሪም እንዳይደረግም እየተቆጣጠረ ይገኛል።

ቀደም ሲል ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች  ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። እርምጃ የመውሰድ ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ገበያውን ለማረጋጋት የጅምላ መሸጫ ሱቆች መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብ ይደረጋል።

ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ህዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። እርግጥ ለዜጎቹ ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል መቼም አጥፎ ስለማያውቅ ይህንንም በማድረግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተለያዩ ጊዜያት የፈፀማቸው ተግባራት ህያው ምስክር ናቸው።

ያም ሆኖ የመንግስት የገንዘብ ምንዛሬ ለውጥ የወጭ ንግድ ላይ መነቃቃት ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት ምጣኔ ሃብታችን በፍጥነት እያደገ ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ በኤክስፖርትና በኢምፖርት መካከል ክፍተት መኖሩ ግልፅ ነው። ጉድለቱ እየሰፋ መጥቶ የተጠቀሰው ደረጃ ላይ መድረሱ ግን ያሳስባል፡፡

በእነዚህ ዓመታት የታየው ደካማ የኤክስፖርት አፈፃፀም አስተማማኝ የውጪ ምንዛሪ ግኝት በማረጋገጥ ለፈጣን ዕድገታችን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ዕድገታችን ለማስቀጠል አና ከውጪ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ማነቆ ሆኗል፡፡

በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ ሰፋፊ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደዚሁም በመንግስት የሚካሄዱ ትልልቅ የመሠረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የማህበራዊ ልማት ኘሮግራሞች ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚፈልጉ በመሆናቸው የኤክስፖርት መዳከም እየተፋጠነ ያለውን ልማት ሊያደናቅፍ እነደሚችልም ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

እርግጥ ይህ የሆነው ለኤክስፖርት ገቢ አፈፃፀም መዳከም ዋናው ምክንያት የማምረት አቅማችን በሚፈለገው ደረጃ አለማደግና በዚህም ምክንያት የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ሸቀጦች በከፍተኛ መጠን፣ በተለያየ ዓይነትና በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ማቅረብ አለመቻሉ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍ የኤክስፖርት ሰብሎች የሆኑት አበባ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡናና ሰሊጥ እንዲሁም የጥራጥሬ ሰብሎች ኤክስፖርት የተደረገው መጠን ይደረጋል ተብሎ ከታቀደው በእጅጉ ያነሰና በማኑፋክቸሪንግ ነባሮች ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ አቅማቸውና በጥራት እንዲያመርቱና በተጨማሪም አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በስፋትና በጥራት መልምሎ ወደ ሥራ ማስገባት በታቀደው ልክ ባለመቻሉ ለኤክስፖርት የማምረት አቅማችን ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ የምንዛሬ ለውጥ ተደርጓል፡፡

በግብርናም ምርታማነቱ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ ለኤክስፖርት የምናቀርባቸው የግብርና ውጤቶች በመጠን፣ በጥራትና በዓይነት ውሱን ሆነው ቆይተዋል፡፡ እናም እነዚህን ሁኔታዎች መቀየር ያስፈልጋል፡፡

የኤክስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም የዕድገታችንን ዘላቂነት መረጋገጥ የሚወስን ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ለኤክስፖርቱ የሚደግፉ ግብዓቶችን ከውጭ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ የገንዘብ ምንዛሬ ለውጡ የወጪ ንግድን እያነቃቃው በመሆኑ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የሚታየው ትርፍ አምራችነትም የዋጋ ንረትን መከላከል የሚችል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት የማስፋት ስትራቴጂን በመጠቀም በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

ይህም በአነስተኛ ማሳ ላይ ብዙ ምርት ማግኘት ያስቻለ፣ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የላቀ ሚና ተጫውቷል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በግብርና ላይ እንደመሆኑ መጠን፤ የአርሶ አደሩ የአመራረት ዘይቤ መለወጡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።

በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት ተችሏል። ይህም አጠቃላይ የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍ አድርጓል። በተለይ ባለፉት ዓመታት የተገኘው ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የምርታማነት ማደግ ውጤት ነው።

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም በመጀመሪያው የዕቅድ ዓመት ላይ የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ ነው።

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ የአርሶ አደሩ ህይወት በአያሌው ተለውጧል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙት አርሶ አደሮች ትርፍ አምራች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ይህ ትርፍ አምራችነታቸውም ከተጠቃሚነታቸው ባሻገር ሌሎች አካባቢዎች በተፈጥሮአዊው የድርቅ አደጋ በሚጠቁበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት እየሞሉ ነው። ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ ከፍተኛ ምርት ተሰብስቧል። ይህም የዋጋ ንረትን በመከላከል አገራዊ ልማትን የሚያሳልጥ ነው። ውጤቱ የተገኘው ሁሉም እንደ አንድ ሆኖ በመስራቱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በመደመር አገራችንን አናልማ” ያሉት እነዚህን ውጤቶች የሚያመጡ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy