Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቀል የሠላም መንገድን …

0 261

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በቀል የሠላም መንገድን

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢትዮጵያ ህዝቦች  ከምንም በላይ ለሰላም  ዋጋ ይሰጣሉ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝቦች   የሰላም እጦት ጦስ ምን እንደሚያስከትል ከማንም በላይ ያውቁታል።  የኢትዮጵያ ህዝቦች የሰላም እጦት የሚያስከትለው ጣጣ የሚያውቁት በሌሎች ሲደርስ ተመልክተው ወይም ሰምተው ሳይሆን  በራሳቸው ላይ በገጠማቸው መከራ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ለሠላም ባላቸው ቀናዒነት በየትኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ይቅር ባይነት ትልቅ ቦታ አለው።  ህገመንግስታችን ለአገራችን ስኬቶች መሰረት እንደሆነው ሁሉ ለችግሮቻችንም መፍቻ ቁልፍ አለው። ይሁንና ህገመንግስታችንን ጠንቅቆ ያለመረዳት አለፍ ሲልም በአግባብ መተግበር ያለመቻላችን ለችግር ዳርጎን ሰንብቷል። የፌዴራል ስርዓታችን የህገመንግስቱ አንዱ ውጤት ነው። ይህ ስርዓት ባለፉት 27 ዓመታት አገራችንን በስኬት ላይ ስኬት እንድትደርብ አድርጓታል።   

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በአመራሩ በተለይ በበላይ አመራሩ እንዝህላልነት በርካታ ዜጎች ለሞትና እንግልት ተዳርገዋል።  አንዳንድ አካላት ሆን ብለው በአገራችን የተከሰቱ ሁከቶች ምክንያታቸው የፌዴራል ስርዓቱ እንደሆነ በማስመሰል ለማቅረብ ሲሯሯጡ ታይተዋል።    እውነታው ግን ይህ አይደለም። የፌዴራል ስርዓቱ 27 ዓመታት ያስገኛቸውን ስኬቶች በማሳነስ በተቃራኒው ትናንሽ ግጭቶችን በማጎን አገሪቱ ችግር ውስጥ እንደሆነች አድርገው ለማቅረብ ሲሯሯጡ ነበር። ይህ አይነቱ ሴራ  ያለምክንያት ሳይሆን ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው ነበር። በእርግጥ የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ገና ለጋና ጅምር ነው። ፌዴራሊዝም ደግሞ ያለዴሞክራሲ እጅግ ፈታኝ ነው። ህገመንግስታችን ለአገራችን ችግሮች ሁሉ በቂ ምላሽ መስጠት እንዲችል ተደርጎ  የተቀረጸ ቢሆንም በመተግበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶች አሉ። እንደእኔ እንደኔ ህገመንግስታችንን በአግባብ አለማወቅና በአግባብ አለመተግበር ይመስለኛል አገራችንን ለቀውስና ለሁከት የዳረጋት።

 

አገራችን ከአህዳዊ ስርዓት ወደ ፌዴራል ስርዓት  የተሸጋገረችው እኮ አህዳዊው ስርዓትን ሞክራ አልሳካ ስላላት ነው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ  የፌዴራል ስርዓት መከተል ባትችል ኖሮ ምናልባት ህልውናዋ ያከተመው የዛሬ 27 ዓመት ነበር። ይህ ስርዓት የኢትዮጵያን  ህልውና ታድጎታል፤ የግዛት አንድነቷን አስጠብቆላታል፤ በህዝቦች መካከል መቻቻል፣ መከባበርና አብሮ መኖር እንዲፈጠር እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና ልማትን እንዲረጋገጥ አርድጓል።  ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ እሴታችን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በየአካባቢው እያስተዋልን ነው። በዚህም በርካታ ዜጎች ጭንቅት ውስጥ ገብተዋል።። ከወራት በፊት በአገራችን ተከስቶ  በነበረው ሁከት አስጨንቋቸው የነበሩ አንድ እናት እንዲህ ሲሉ አጫወቱኝ። ልጄ ሁሉም ነገር “ዕድገትና ልማትን” ማለታቸው ነው ቀርቶብን የቀድሞው ሰላም፣ የቀድሞው አብሮነት ይሻለናል፤ ነግቶ እስኪመሽ ልጆቻችን ወጥተው እስኪገቡ ስጋት ውስጥ ገብተናል። የእኚህ እናት ጭንቀት በቀላል የሚታይ አይደለም።

 

እንዲህ ያሉ እናቶች የፌዴራል ስርዓቱ የግጭት መንስዔ መስሏቸው የሚሰጡት የመፍትሄ ሃሳብ የተሳሳተ ነው።  ለምን ይህን ስርዓት አንተውና ወደ አንድነት አንመለስም አየነት። እኚህ እናት ተጨንቀው መፍትሄ ይሆናል በሚል የሰጡት ነው።   የፌዴራል ስርዓቱ ለግጭት መንስዔ እንደሆነ አድርገው የሚያራግቡ አካላት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ይህ የፌዴራል ስርዓት የኢትዮጵያ እስትንፋስ ነው።   ህዝቦችን በማሳሳት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ምክንያቱም ዘላቂነት ስለማየኖረው። የፌዴራል ስርዓታችን ለአገራችን የስኬት ምሰሶ ነው። ባለፉት 27 ዓመታት ተቻችለንና ተከባብረን አብረን በመኖራችን በርካታ ነገሮችን አትርፈናል፤ ሰፊና አማላይ ገበያ፣ ጠንካራና አዳጊ ኢኮኖሚ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ መንግሥት፣ በሥነ ምግባር የታነፀ ህዝባዊ  የፀጥታ ኃይል ወዘተ።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን  የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች ከማረጋገጥ ባሻገር አገሪቱን በፈጣን  የምጣኔ ሀብት ለውጥ ምህዋር ውስጥ አስገብቷታል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የነበራት ገጽታም ሆነ ተሰሚነት ባለፉት 27 ዓመታት እጅጉን  ተለውጧል፤ አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም በመስፈኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው። ከባድ ድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ቢከሰትም በራስ አቅም መቋቋም ተችሏል።  ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን በተባበሩት መንግሥታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን መንግሥት ባከናወነው  ተግባር ነው። ይህ የፌዴራል ሥርዓቱ ስኬት አይደለምን?

 

ኢትዮጵያ ወደ ስኬት ማማው መውጣት የጀመረችው በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች ለአብነት የብሄር፣ የኃይማኖት፣ የማንነት፣ የአስተሳብ ልዩነቶችን ማስተናገድ  የሚያስችል ስርዓት መተግበሯና የህዝቧቿ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት መከተል በመቻሏ ነው። አገራችን በዓለም በነውጥ ቀጠናነቱ በሚታወቀው ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምሥራቅ አፍሪካ  ቀጠና ስኬታማ ለመሆን የበቃችው በዚህ በፌዴራላዊ ስርዓት መከተል በመቻሏ ነው ቢባል ስህተት ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ የቀንዱ አካባቢ ሠላም ደሴትና የአካባቢው የኢኮኖሚ ሞተር መሆኗን በተግባር አሳይታለች። ይህ የዚህ ስርዓት ውጤት ነው።

 

እንደእኔ እንደኔ በ21ኛው ዘመን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ማሰብ ራስን በራስ እንደማጥፋት የሚቆጠር ተግባር ይመስለኛል።  አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን የፌዴራል ሥርዓት ችግር እንዲገጥመው የቀድሞው አህዳዊ ስርዓት እንዲመለስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ናቸው።  ይህ ለማንም የሚበጅ አይደለም፤ የጋራ ቤታችንን ያፈርስብናል፤ ሁላችንም ልንቃወመው ይገባል። በአገራችን ችግሮች መኖራቸው የሚካድ አይደለም፤ ይሁንና በኢትዮጵያ የህዝቦች የሠላም፣ ልማትና  የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ጀምረዋል። አሁንም መልካም ጅምሮችን ማጠናከር ይኖርብናል። በነውጥ የሚመጣ ለውጥ መዳረሻው አይታወቅም። በቀል የሠላምን መንገድ እየዘጋ ነውጥና ሁከትን እያባባሰ ወደ ውድቀት ይመራል እንጂ መልካም ነገርን አያመጣም።

የፌዴራል ሥርዓታችን  ዘላቂ ሠላም አስፍኖልናል፤  ልንለማ፣ ልናድግና ልንለወጥ እንደምንችል በተጨባጭ አሳይቶናል። ብዝሃነትን በአግባብና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መያዝ ከተቻለ የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ እንደሚሆነም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ጥሩ ምሣሌ ናት።  በቀደምት የአገራችን ስርዓቶች ምን ይስተዋል እንደነበር የሚታወስ ነው። ዛሬ ያ ሁኔታ ተወግዷል። የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን ተቀብሎ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት መገንባት ከተቻለ ህብረ ብሄራዊነት የስጋት  ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የአንድነት መሰረት እንደሚሆን ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ ናት። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶች ከተረጋገጠ አብሮነትን የሚጠላ አካል አይኖርም። እስካሁን ያለው አብሮነትም የስኬታችን ዋነኛ መነሻም መድረሻም ሆኗል።

 

አገሪቱ ከላይ ያነሳኋቸውን ስኬቶች  ማስመዝገብ የቻለችው ሕዝቦቿ በመከባበርና በመቻቻል አብሮ በመኖራቸው ነው። አብሮ መኖር ያስቻለን ደግሞ ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ በቻለው የፌዴራል ሥርዓታችን ነው። በመሆኑም አንዳንድ ኃይሎች  በአገሪቱ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሁሉ የፌዴራል ሥርዓቱ እንከኖች አድርገው ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለህዝብና አገር ተቆርቋሪ በመምሰል ትናንሽ ግጭቶችን በማጎን  እከሌ የተባለው ብሄር ሊያጠቃህ ነው፤ ተነስ፣ ለወገኖችህ ድረስላቸው ወዘተ በማለት በግጭቶች ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል። የሌለን ነገር እየፈጠሩ ብሄሮችን ማጋጨት ለማንም የማይበጅ የፖለቲካ አካሄድ ነው።  የበቀል መንገድ የትም አያደርስም። በበቀል አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ለየትኛውም አካል ቢሆን የበቀልና የእልህ መንገድ መዳረሻው እልቂትና ወድቀት ነው። በቀል ቁስልን አያደርቅም፤ በቀል ውድቀትን እንጂ ስኬትን አያመጣም። በቀል መለያየትን፣ መቀነስንና ውድቀት እንጂ አንድነትን፣ መደመርንና ስኬትን አያመጣም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy