Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአንድ ልብ…

0 433

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአንድ ልብ…

                                                   ዘአማን በላይ

ዛሬ ሀገራችንን በተመለከተ በአዎንታዊነት የሚቀርቡት ዘገባዎች የሶስተኛ ወገን እማኝነት እየሆኑ ነው። በተለይም በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ በክፍለ አህጉራዊ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተገቢውን ሚና እየተጫወተች ነው። ርግጥ የኢትዮጵያ ተሰሚነትና ተቀባይነት እየጨመረ የመጣው በሀገር ውስጥ በምናከናውናቸው ተግባራት ምክንያት ነው።

ይኸውም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ውስጣዊ ጥንካሬያቸውን በማጎልበታቸው የተፈጠረ ነው። እናም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድ ልብ ሆነው የሀገራቸውን ውስጣዊ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማጠናከር እስከተጉ ድረስ ውጫዊውን ገፅታቸውንና ተፈላጊነታቸውን ማጎልበት ማጎልበት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር ያላት ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል።

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሳሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ ነው። በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያስረዳል።

ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል። የዕድገታችን መስካሪዎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እየሆኑ ነው—ሶስተኛ ወገኖች።

ሀገራችን በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከርም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲጨምር እያደረገች ነው።

በሀገር ውስጥ በተከናወኑት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎች የውጭ ግንኙነታችን፣ ገፅታ ግንባታችንና ተቀባይነታችን እንዲያድግ አስችሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 27 ዓመታት ያህል የተከናወኑት ሰፋፊ ስራዎች አጥጋቢዎች ነበሩ።

ይህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሰላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ በፅኑ መንፈስ እድትንቀሳቀስ አድርጓታል።

ሀገራችን በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረት በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ የቀጣናው አዋኪ ከሆነው የኤርትራ መንግስት በስተቀር ከሌሎች ሀገሮች ጋር በላቀ የግንኙነት ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ዛሬ ‘የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው’ የሚል ፅኑ እና ቁርጠኛ እምነት በመያዙና ሀገራችን ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነፃ ልትሆን የምትችለው፤ ፈጣን የምጣኔ ሃብት ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ሲካሄዱና ህዝቡም በየደረጃው የዕድሉ ተጠቃሚ ሲሆን ነው።

ከዚህ አኳያ በተለያዩ ጊዜያት የተቀረፁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት ካሁን በፊት ዘላቂ የልማትና ድህነት ቅነሳና ፈጣን ልማት ድህነትን የመቀነስ ብሎም የማጥፋት ዕቅድ እንዲሁም ሌሎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራሞች በሚገባ እንዲሳኩ ተደርገዋል። በዚህም ጠንካራ ሀገራዊ አቅም መፍጠር ተችሏል። ይህም በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ቢያጋጥመንም እንድንቋቋመው ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮጵያ ያላት ተሰሚነት ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል በዓለም መድረክ የአፍሪካውያን ድምፅ ጎልቶ እንዲሰማ ማድረግ ችላለች። ከዚህ በተጨማሪ ከአህጉሪቱና ከዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ትልቅ ቦታን መያዝ ችላለች።

ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ የሰላም ግንባታ ዲፕሎማሲን በመከተሏ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር የሰላም አስከባሪ ኃይሏን በብሩንዲ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን ዳርፉርና አብዬ ግዛቶች እንዲሁም በሶማሊያ በማሰማራቷን አኩሪ ተግባር እየፈፀመች ነው። በተለይ በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ በአሚሶም ጥላ ስር ሆና አልሸባብን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች።

እስካሁን ድረስ ያከናወነችው ማስከበር ተልዕኮዎች ስኬታማ መሆናቸውና በአሁኑ ወቅትም ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገሩ መምጣታቸው እንዲሁም ሀገራችን ለሰላም መስፈንና አሸባሪነትን ለመዋጋት እያደረገችው ያለችው ጥረት ተቀባይነቷን አጉልቶታል። ኢትዮጵያ ሰላም የተናጠል ሳይሆን የጋራ አጀንዳ መሆኑን በማረጋገጧ ሌላኛው ይበልጥ ተፈላጊ እንድትሆን ያደረጋት ጉዳይ ነው።

ርግጥ የተሰሚነታችን መጎልበት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ መኖሩ፣ ኢኮኖሚው የተረጋጋና ፈጣን ዕድገት ማሳየቱ (በእማኞች ሳይቀር መረጋገጡ) እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የመሰረተ ልማት አውታር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱና ሀገራችን ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኗ ነው ብዬ አስባለሁ።

አዎ! ዛሬ በሀገራችን ውስጥ በአንፃራዊነት እነዚህ ጉዳዩች በመኖራቸው ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ቀልባቸው ተስቦ ሃብታቸውን ለማፍሰስ ከአራቱም የዓለማችን ማዕዘናት እየመጡ ነው። ታዲያ እዚህ ላይ ለኢንቨስትመንት ወደ ሀገራችን ለሚመጡ ባለሃብቶች ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ይዘው ከመጡ በኋላ እንዳይበረግጉ ማድረግ ወሳኝ ነው።  

ያም ሆኖ የቱንም ያህል ጥሩ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቢኖርና ኢትዮጵያም ለኢንቨስትመንት ያሏት ምቹ ሁኔታዎች ቢረጋገጡ፤ እነዚህን እውነታዎች በውጭው ዓለምም የሚያስተዋውቃቸው አካላት ያስፈልጓታል። ዓለም እንደ አንድ መንደር በምትቆጠርበት ዘመነ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ራስን ሳያስተዋውቁ ምንም ዓይነት ተግባር መከወን አይቻልም።

ታዲያ ይህ ስራ ለሀገራችን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ብቻ የተተወ አይደለም። ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ አምባሳደር መሆን ይኖርበታል። ይህም በርካታ ባለ ሃብቶች ወደ ሀገራችን ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ያደርጋቸዋል። በዚህ ረገድ እስካሁን የተከናወኑት ስራዎች ውጤታማ ቢሆኑም፤ አሁንም ብዙ በመስራት የተፈላጊነታችንን ደረጃ እጅግ ማጎልበት ይገባናል።

በመግቢያዬ ላይ እንዳልኩት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያለንን ተፈላጊነት ይበልጥ እንዲጨምር ለማድረግ በሀገር ውስጥ የምናከናውናቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎች መጠናከር መቻል አለባቸው። ይህን ለማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ በአንድ ልብ እስከተንቀሳቀሰ ድረስ ተፈላጊውን ጉዳይ ማምጣቱ የሚቀር አይሆንም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy