Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

 ነጻነትን እንሻለን ከሚሉ ሃይሎች በስተጀርባ  

0 372

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 ነጻነትን እንሻለን ከሚሉ ሃይሎች በስተጀርባ  

ዮናስ

 

በአገራችን ዴሞክራሲ በትግል እውን ከሆነ በኋላ የዜጎችና የማህበረሰቦች መብቶች ሳይነጣጠሉ ተከብረዋል፡፡ ከግለሰብ እስከ ቡድን መብት ድረስ ያሉ መብቶች እውቅና ተሰጥቷቸው የህግ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በህገ መንግስታችን ሃሳብን የመግለፅ፣ የመቃወምም ሆነ የመደገፍ፣ የመደራጀት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ በህይወት የመኖር፣ ከአካላዊ ጉዳት የመጠበቅ ወዘተ… ግለሰባዊ መብቶች ተከብረዋል፡፡ ይህ ቀጣይነት እንዲኖረውና ያለአንዳች መሸራረፍ ጎልብቶ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚቻለው ሃገሪቱን ለዘመናት ሲሻቸው ተቀራምተው ሲሻቸው ደግሞ ለቤተሰባቸው አካፍለውና አውርሰው “ሲያስተዳድሩ” የነበሩ ገዥዎች በተከተሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ የአገዛዝ ስርዓት ዜጎችም ሆነ ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ተነፍገው በስቃይና እንግልት ይኖሩ የነበረ መሆኑን ከማመንና ከመቀበል ነው።     

ደርግ በመጨረሻዎቹ የስልጣን ጊዜያቱ የእስትንፋሱ ማስቀጠያ አድርጎ የነበረው “የኢትዮጵያ አንድነት” አጀንዳን መሆኑ ይታወቃል። ከደርግ ውድቀት በኋላም የአፈና አንድነትን ማስቀጠልን መሰብሰቢያ አድርገው በፖለቲካ ፓርቲና በነጻ ፕሬስ ስም የተካሄዱትን እርኩቻዎች በአንድ ወገን፣ በተመሳሳይም አንዲትም ቀን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ላለማሰለፍ የተሰባሰቡት ደግሞ በሌላ ወገን ሀገሪቱን ከውድቀት አፋፍ ላይ ጥለዋት የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የሚታወስና የማይዘነጋ ነው ፡፡ ሁለቱ ጥጎች የመጨረሻውን ጫፍ ይዘው ሊሰነዝሩ የተዘጋጁት መባላትም ብዙዎች የኢትዮጵያ እጣ ዩጎዝላቪያን ያጋጠማት እልቂትና መበታተን እንደሚሆን ለመገመት አስችሏቸው የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የሚታወስና የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡  ይህ ግምታቸው ደግሞ ክፉ ምኞት ወይም ሟርት ሳይሆን በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔም የነበረ ለመሆኑ ብዙ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የወቅቱ የኃይል አሰላለፍ ዓይነተኛ መለያ የነበረው የብሄር ብሄረሰቦች መብት ጥያቄ ሌላ መፋለሚያ ነበር፡፡ በተለይ የእስከ መገንጠል መብት ዓይነተኛ የፍልሚያ ርዕስ የነበረ ሲሆን  ኢትዮጵያዊነት ፈቅደውና ወደው የሚጎናፀፉት፤ የኢትዮጵያ አንድነትም በህዝቦቿ መፈቃቀድና መልካም ፈቃድ ላይ የሚመሰረት እንጂ በኃይልና በግዴታ የሚጫን መሆን የለበትም የሚለው አዲስ አስተሳሰብ በአሸናፊነት ወጥቷል፡፡  

“የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በተራዘመ ትግል ዕውን ባደረጉት ዴሞክራሲያዊ መድረክ እየተረቀቀ ያለውን ሕገ-መንግስት የመተርጎም ስልጣን የራሳቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንጂ ለማንም የሚተውት ጉዳይ አይደለም” የሚለው አስተሳሰብ የበላይነትን መያዙም በግዴታ ተጭኖ የነበረው አንድነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገርሰሱን የሚያረጋግጥ ነው ፡፡ “ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ለዳኞች መተው አለበት” ብለው ቢሞግቱም ጥያቄው የሕግ ጉዳይ ሳይሆን የአትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አብረው ለመኖር የገቡት ቃል ኪዳን፣ እምነትና ፖለቲካዊ ጉዳይ በመሆኑ ይህ አቋም አሸናፊ ሆኖ መውጣት ችሏል፡፡

በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ሆኖ ፀድቋል።  

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሀገራቸው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው መረጋገጡ በመላ ሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ሰላምን ከማስፈኑም ባሻገር ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ግንባታ መሰረት ጥሏል፡፡

በሰፈነው ዴሞክራሲያዊ መብትና የመናገርና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ቅስቀሳቸውን ለዴሞክራሲያዊ ፕሬስ ቦታ እስኪጠብ ድረስ ያጧጧፉትና መድረኩን በጩኸት የሞሉት የደርግ ፀሃፌ ትዕዛዞች የቱንም ያህል ዕሪታ ቢያቀልጡ የሚፈልጉትን ሰሚ ጆሮ አላገኙም፡፡ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 የተደነገገውን የፕሬስ ነፃነት የአፈና ስርዓታቸውን ለመመለስ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመዋል፡፡ በወቅቱ የተደረጉ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከ1984 ዓ.ም  ጀምሮ /ከሽግግሩ ጀምሮ ማለት ነው/ በሀገሪቱ እንደ አሸን ከፈሉት የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች አብዛኛዎቹ የደርግ የፕሮፖጋንዳ ሰራተኞች በነበሩ የኢሰፓ አባላትና ወታደራዊ መኮንኖች ባለቤትነት ያለበለዚያም በጥፋት ኃይሎች ቀጥታ ፋይናንስ የሚደረጉ ነበሩ፡፡ ይሁንና መሰረታዊ መብቶቹ የተረጋጡለት ሕዝብ መሃል ምንም መፍጠር አልቻሉም፡፡

በቡድን መልክ የሚገለፁ ማህበረሰቦችም የተሟላ እኩልነት ተጎናፅፈዋል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ሴቶች፣ ሠራተኞች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና የመሳሰሉ ማህበረሰቦች  የቡድን መብቶቻቸውን የተጎናጸፉ መሆኑም እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣይነት ህልውናዋ ተረጋግጦ ልትቀጥል የምትችለው ዜጎቿንና ህዝቦቿን አክብራ ስትይዝ ብቻ እንደሆነ በማመን ተግባራዊ የተደረገው ዴሞክራሲ አገሪቱን ለፅኑ ህዝባዊ አንድነት አብቅቷታል፡፡  

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏና ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ስጋት ቀስ በቀስ አርግቦታል፡፡ መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል በተግባር ታይቷል፡፡ በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ መንገድ ከፍቷል።

መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጣቸው እገዛዎች፣ በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ አዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓቸዋል፡፡  ይህ የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመታት መከበር የጀመረውን መብት ተከትሎ በርከት ላሉ ዓመታት ጥቂት በማይባሉ የህብረተሰብ ልሂቃን ዘንድ ሰፍኖ የቆየውን “መበታተን አይቀሬ ይሆናል” የሚል ጥርጣሬ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማስወገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አሁንም መፍጨርጨሮች የቀጠሉ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል።  

በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት ነው። ኢህአዴግ  የዘመናት የብሄራዊና የመደብ ድርብ ጭቆና የህዝብ ጥያቄዎች ከመሰረቱ ለመለወጥ ከተከተላቸው ቁልፍ የፖለቲካ አቋሞችና ከወሰዳቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎች መካከል የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን የመገንጠል መብቶችን ማረጋገጥ ቢሆንም ከዚሁ ባልተናነሰ አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የመጨረሻው ግብ ሆኖ ተቀምጧል። በዚህም አዲሲቷ ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተች፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ዴሞከራሲያዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት አገር እንድትሆን ራእይ ተቀርፆ እየተሰራ ነው።  

በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በክልሎች መካከል መነጣጠልና መለያየት ሳይሆን ጠንካራ ትብብርና መደጋገፍ የሚፈቅድ ስለሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጎለበተ እንዲሄድ መስራት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊነት ተዘንግቶ ብሄር በመክረሩ እንደገባንበት ማጥ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን እክርረን ብሄርን ብንዘነጋ የሚፈጠረውን ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ይህ እንዳይሆን በተለይ ሁኔታውን ከመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ጋር አዛምዶ በመቃኘት ሃገሪቱን ወደትክክለኛው መንገድ መመለስም ሆነ ከነጻነት በስተጀርባ ትርምስን የሚፈቅዱ ወይም ለትርምስ የሚያመቻቹ ሃይሎችን ማጋለጥ ከመገናኛ ብዙሃኑ ይጠበቃል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት እንደተደነገገው ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብት እና የፕሬስ ነፃነት የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ እንደሆነ እሙን ነው።መብትና ግዴታው እንደተጠበቀ ሆኖ ግን መረጃዎችን በአግባቡና ተዓማኒነት ባላቸው መልኩና በተገቢው ሰዓት ለህዝቡ ለማድረስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሲቸገሩ ይስተዋላል። በተጨማሪም መንግስት እንዲሰራ የሚፈልገውን የምርመራ ዘገባ ለመስራትም የአቅም ውስንነት እንዳለ ይነገራል። ጋዜጠኛው ደፍሮ ቢሰራም አንዳንዴ የመንግስት ባለስልጣናት ረጅም እጅ ስላላቸው ብቻ የመረጃውን እውነታነት ለማድበስበስ ጣልቃ ሲገቡ ይስተዋላልና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲወገዱ የመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋል።  

ከሀገር ደህንነትና ከህዝብ ሰላም አኳያ ችግር ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ካልታሰበ አሊያም ለመስጠት አዋጅ ወይም ህግ ይከለክላል ካልተባለ በስተቀር መረጃን መስጠት የግድ ነው። መረጃ የሚከለክል አካል ካለ የፕሬስ ህጉን ተከትሎ በወጣው ደንብ መሰረት መጠየቅ አለበት። መረጃም የተከለከለው አካል መረጃውን ስላለማግኘቱ ለሚመለከተው ማሳወቅ ይኖርበታል። ምክንያቱም ከልካዩን በህግ ለማስጠየቅ ያስችላልና ነው። መረጃ በወቅቱና በትክክለኛው መንገድ ለህዝቡ መድረስ አለበት፤ ይህ የህዝቡ መብት ነው። መረጃ መስጠት ደግሞ ግዴታ ነው።

ማንኛውም ጋዜጠኛም ሆነ የሚዲያ ተቋም የህዝቡን መረጃ የማግኘት መብት በአግባቡ ማክበር አለበት። ህዝቡን ደግሞ ከብጥብጥ፣ ከሁከት እንዲሁም ለግጭት ከሚጋብዙ የተሳሳቱና ለጸብ አጫሪነት ከሚዳርጉ መረጃዎች ደግሞ መጠበቅ የግድ ይላል። ወደ ባለስልጣናቱ ሲመጣ ደግሞ ጣልቃ የሚገቡ ከሆነ ይህ ሊፈጠር የሚችለው የመጀመሪያው የመረጃ ነጻነትን ህግ በአግባቡ ያለመረዳት ሊሆን ይችላል ማለት ነው፤ በእርግጥ ይህ ከተጠያቂነት አያድንም። ሁለተኛው ደግሞ እንዲሁ አንዳንድ መረጃ የማቀበልና የመስጠት ሃላፊነት ያለባቸው ጋዜጠኞች በአግባቡ ሙያቸውን ካለመረዳት ሊመጣ የሚችልም ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ይህም አግባብ አይደለም። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር  በተደጋጋሚ እንዳሉት መረጃ በትክክል ለህዝቡ መድረስ አለበት። ለህዝቡ የሚደርሰው መረጃ በባለስልጣናት ስሜት ሊቃኝ አይገባም። ግለሰቦች ለህዝቡ በትክክል ሊደርስ በሚገባው መረጃ መሃል ገብተው ትክክለኛ መንገዱን ሊያቋርጡ አይገባም። የተሰራውና የተከናወነው በሌላ እነርሱ በሚፈልጉት መንፈስ ሊቀይሩትም በፍጹም አይገባም። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጋዜጠኞች አካሄዱ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ህግ ውጭ ነው ብለው መቃወም አለባቸው። በዚህ ምክንያት የሚመጣውን ሃላፊነት ሁሉ ለመቀበልና እስከሚመለከተው አካል ድረስ ለማቅረብ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል እንጂ መፍራት የለባቸውም።

ተገቢ የሆነ መረጃ አለመስጠት የግልጽነትንና ተጠያቂነትን አሰራር ማጓደል ነው። የግልጸኝትንና የተጠያቂነት አሰራር ተከትሎ መስራት ደግሞ አንድ የመንግስት ሃላፊ ግዴታው ነው። ለህዝቡ ደግሞ ግልጽ መረጃ ማግኘት መብቱ ነው። ስለዚህ ይህንን የሚያጓድል አካል የመልካም አስተዳደር ችግር አለበት ተብሎ ነው ሊወሰድ የሚችለው። በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ በደንብ ቢፈተሽና ቢታይ መረጃው እንዲዛባ የሚደረገው አሊያም እንዳይተላለፍ የሚከለከለው በብዙ መልክ ሊታይ ይችላል፤ ማለትም ሌብነትን አሊያም ያለመስራትን ሊያመላክት ይችላል። ስለዚህም እንደ መንግስትም ሆነ እንደ  ዜጋ እና ሚዲያ ይህን መታገል ግድ ይለናል።

ከቀጣዩ አጠቃላይ ምርጫ በፊት ያሉት ሁለት ዓመታት፣ በአገራችን ጉዳዮች ላይ የጋራ ብሔራዊ ውይይቶች ልናካሂድባቸው የሚያስችሉ የኢትዮጵያ ዕድሎች ናቸው፡፡ ሁሉም ሊደመጥ ይገባዋል፡፡ ሁለት ዓመታት ብዙ አይደለም፡፡ ስለዚህም ውይይቱ ይዋል ይደር ሳይባል ተጀምሯል፡፡ ይህን አገራዊ ክርክር ስናካሂድ፣ አገራችን ከእነ ኅብረቷና ከእነ ጥንካሬዋ እንዳለች ሆና ትቆየናለች፡፡ ነጻነትን እንሻለን በሚል መፈክር ጥረታችንን ለማኮሰስ የሚሞክሩ ቁጣ አዘልና ከፋፋይ መልዕክቶችን ልንፈራቸው አይገባም፡፡ እነዚህ ፈጣንና ሞገደኛ ጅረቶች በራሳቸው ጊዜ የረጋ ጉዞ ከሚያደርገው፣ ነገር ግን ለአገሪቱ ይበልጥ የተሻለውን አቅጣጫ ከሚያመላክተው ኃያል ወንዝ ጋር የሚቀላቀሉ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy