Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አማራጮቹ

0 316

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አማራጮቹ

                                                     ዘአማን በላይ

አገራችን አሁን በምንገኝበት አጠቃላይ ሁኔታ አኳያ ሁለት አማራጮች ያሏት ይመስላል። አንደኛው፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ተቀብሎ በጠነከረ አንድነት የሀገራችንን ህዳሴ እውን ማድረግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ተሞክሮ የወደቀውን የኒዮ-ሊበራል አስተሳሰብ መከተል ናቸው። ታዲያ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ካለችበት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የትኛው አማራጭ የሚጠቅም መሆኑን መረዳትም ያስፈልጋል።

ይሀ ፅሑፍ የግል ዕይታ እንደመሆኑ መጠን፤ ሁለቱንም አማራጮች ለመዳሰስ እሞክራለሁ። እንደሚታወቀው ሀገራችን በምታከናወነው የፌዴራሊዝም ስርዓት መሰረት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ነው። ቀደም ካሉት ዓመታት የሀገሪቱ ጉዞ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ነው።

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎችና ክልሎች ግጭት የመከሰቱ ሁኔታ እጅግ አነስተኛ ነው። “ለምን?” ከተባለ፤ ይህን መሰሉ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ስለሚያስችል ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ለፅንፈኝነት የሚመች አውድ አይደለም። በመሆኑም ፅንፈኝነት ይህን በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ብሔርተኝነት አይፈልገውም።

ርግጥ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና እየፈጠረ ነው። ምንም እንኳን በዚህ ረገድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገራችን የታየው የሰላም ችግር አንድ ስንክሳር ቢሆንም፤ ብሔርተኝነቱ ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ ነው ማለት ይቻላል።

ከ27 ዓመታት በላይ ፅንፈኝነትን ለመዋጋት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ሆኖም አመለካከቱ አልፎ…አልፎ የሚያንሰራራው በኪራይ ሰብሳቢነትና ባልተገባ ጥቅም በሚሹ አካላት አማካኝነት በመሆኑ ሁለቱን ማነቆዎች ከሕዝቡ ጋር በመታገል ለውጡን ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

ይህን ብሔርተኝት ማንነትን ከማወቅ፣ የሌሎችን ማንነት ከመገንዘብ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥና አካባቢን ከማልማት አኳያ ልንመለከተው እንችላለን።

ማንነትን ለማወቅ በቅድሚያ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን መለየት ያስፈልጋል። የጋራ የሆኑ ባህሪያትን መገንዘብንም እንዲሁ። የሌሎችን ማንነት ለመገንዘብም ከሌሎች ጋር ያለውን የጋራ ፍላጎትና ጥቅም ማወቅ ይገባል። እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀም ያስችላል። ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አካባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት የማዋል ሁኔታን ይፈጥራል።

በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ውስጥ የህዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።

ታዲያ ይህ ግንኙነት ጤናማ ባልሆነ አስተሳሰብ በሚመራበት ጊዜ ግጭት ሊከሰት ይችላል። በኢትዮጵያ የተማከለ አስተዳደር ከተመሠረተበት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ በማህበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተመላበት፣ ግጭት የጠነከረበት፣ በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ሰላም ያጣችበት እንደነበር ይታወቃል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ሰበብ የፅንፈኝነት አስተሳሰብን የሚያራምዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተመልክተናል። ርግጥ ሃሳቦቹ ሀገራችን ከምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ጋር አብረው የማይሄዱ ቢሆኑም፤ ህገ መንግስቱ ማንኛውም ዜጋ አስተሳሰቡን በነፃነት እንዲገልፅ ይፈቅዳል። ሆኖም መንግስት የተለየና የተሳሳተ ሐሳብ ያላቸውም ሰዎች ቢሆኑም ሃሳባቸውን ለምን ይገልፃሉ የሚል ብዥታ የለውም። እናም በተቻለ መጠን በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲያብብ ጥረት ተደርጓል—የሚቀሩ ረጅም ጉዞዎች ቢኖሩም ማለቴ ነው።

በፌዴራሊዝም ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን እውን ለማድረግ ቁልፍ ተግባር ነው። በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር ዜጋ፣ የሌላኛውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲያከብር በምላሹ መከበርን ስለሚያገኝ ነው።

ያለፈው ታሪካችን ስንክሳሮች ብዙ ነው። አንዱ ሌላኛውን በድሎት ሊሆን ይችላል። ያለፈው ታሪክ አንድን ህዝብ የራሱ ዘር ከሌላው በከፋ መልኩ በድሎትም ይሆናል። ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ዳሩ ግን ይህ ክስተት ገዥዎችን እንጂ ህዝብን የሚመለከት አይደለም። ህዝብ እንደ ህዝብ አንደኛው ሌላኛውን ሊበድል የሚችልበት መሰረት ሊኖር አይችልም።

ታዲያ ይህን የተዛባ ቀደምት ግንኙነት በመኮርኮር ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ሃይሎች አሉ። ይህ ዓይነቱ መንገድ በፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅንሰ ሃሳብ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። እናም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን እያጎለበትን አንድነታችንን ማጠናከር ያስፈልገናል።

በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እየተመራን አንድ ስንሆን ተቀባይነታችን ይጎላል። ማንም ከመሬት እየተነሳ ሊያባላን አይችልም። ውስጣዊ አንድነታችን ተጠናክሮ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን እውን እናደርጋለን።

ምን ይህ ብቻ። እንደ ሀገር በልበ ሙሉነት ኢትዮጵያች ያሰበችውን ህዳሴ ልናረጋግጥ እንችላለን። እናም ይህ በፌዴራላዊ ስርዓታችን ዋነኛ ተግባር የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን በማረጋገጥ በሀገር ደረጃ አንድነትን መፍጠር ትርፈ ብዙ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በእኔ እምነት አንዳንድ ወገኖች የሚያነሱት ኒዮ ሊበራል ፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰቦች አፍሪካ ውስጥ ተሞክረው ያልሰሩ ናቸው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ለዚህች ሀገር ጠቃሚ አማራጭም አይመስለኝም። አፍሪካዊቷ ፀሐይ የጠለቀችበት እሳቤ ነው ተብሎም ሊወሰድ ይችላል።

የኒዮ ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ዋነኛ መሰረት ‘ሁሉም ነገር ለገበያና ለግሉ ባለሃብት መተው አለበት፤ መንግስት ህግና ስርዓትን ከማስፈን ውጪ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም’ የሚል ነው።

በዓለም ላይ ፅንፈኛ አመለካከቶችን በግድም ይህን በውድ ለማዛመት ጥረት ያደርጋል። እናም አስተሳሰቡን የማይደግፉትም ይሁን የሚደግፉት ሀገሮች በግዳጅ እንዲቀበሉት በተለያዩ መንገዶች ጥረት ያደርጋል። አፍሪካ ላለፉት 40 ዓመታት ያህል የአዚህ ጉዳይ ሰለባ ነበረች።

አፍሪካዊያን ከነባራዊ ሁኔታቸው ጋር የማይሄደውን የኒዮ ሊበራሊዝምን አስተሳሰብ የግድ እንዲቀበሉ ተደርገው ርዕዩቱ ከአህጉሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሆድ ሆኖ አልተገኘም። አፍሪካ ውስጥ ርሃብ፣ ስቃይና ቸነፈርን ብቻ ነው ያመጣው።

ይህ ሁኔታም በዴሞክራሲ ሰበብ “በዓለም ላይ እኔ ብቻ ነኝ ትክከል” በሚል እሳቤ ከሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ፖለቲካን በኃይል መጫን አግባብነት የሌለው መሆኑን የመሰከረ ነው። አፍሪካ ውስጥ ቦታ የሌለውም ጭምር እንደሆነ ያስመሰከረ እውነታ ነው።

ርዕዮተ ዓለሙ በባህሪው በጥቂት የግል ባለሃብቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ ማህበራዊ መሰረቱ ይኸው የህብረተሰብ ክፍል ነው። እናም እጅግ የሚበዛው የህብረተሰብ ክፍልን የዘነጋው ይህ ስርዓት፤ መንግስታዊ መሰረቱ ጥቂት ባለሃብቶች ስለሆኑ ዴሞክራሲውም ለእነርሱ የቆመ ነው። በዚህም ሳቢያ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ አይሆንም። እናም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በእኛ ሀገር ውስጥም የሚሰራ አይደለም። በምርጫነት ሊቀርብ ቢችልም ተመራጭ መሆን ግን የሚችል አይመስለኝም።

  

  

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy