ከጉብኝቶቹ ምን አተረፍን?
ዘአማን በላይ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጂቡቲ፣ በሱዳንና በኬንያ ያደረጓቸው የስራ ጉብኝቶች ለሀገራችን ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። በዚህም በሶስቱ ሀገራት የተካሄዱት ጉብኝቶች ዓላማ፤ ኢትዮጵያ ከችግር ወጥታ በጋራ ጥቅም ለመስራት እና ለመልማት ፍላጎት ያላት መሆኗን ለማሳየትና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የመተማመን መንፈስ በመፍጠር የተጀመሩ ትብብሮችን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው።
ሀገራችን ለክፍለ አህጉሩ ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲኖር አሁንም ቁርጠኛ መሆኗን ማሳየት ሌላኛው የጉብኝቶቹ ዓላማ ነው። በጉብኝቶቹ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሆን የወደብ ልማትን በጋራ ለማካሄድና ለማስተዳደር የተስማማችበት ነው። በጎረቤት ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መብት እንዲከበርና ማረሚያ ቤት የሚገኙም እንዲፈቱ ማድረግ የተቻለበት ጉብኝት ነው።
አካበቢውን በመሰረተ ልማት በማሰተሰሰር ሀገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን ለማስቻል የሀገራችን ቁርጠኛ አቋም የተንፀባረቀበት እንደሆነ ግልፅ ነው። በእነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ የተቀዳጀቻችው ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ናቸው።
ከጂቡቲ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ጉብኝት ታላቅ ስኬት የተመዘገበበት ነው። ጂቡቲ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚስተናገድባት ናት። ከሀገራችን ጋር በባቡር መስመር የተሳሰረች ሀገር ናት። ጂቡቲ ያላትን ወደብ በጋራ ለማልማት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈራርመዋል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ በመሪዎቻቸው በኩል የደረሱት የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነት፤ አገራችንን በጅቡቲ የወደብ ድርሻ ባለቤት ጅቡቲንም በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ባለ ድርሻ የሚያደርጋት ነው።
ኢትዮጵያና ጂቡቲ በወደብ ልማት፣ በእርሻ ልማት፣ በመንገድ ልማትና ሃገራቱን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመስራት ስምምነት ደርሰዋል። ይህ ስምምነት ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ ከማድረጉ በላይ ላቀዱት ኢኮኖሚያዊ ውህደት ፈር ቀዳጅ ነው።
በስምምነቱ የመሰረት ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥም ተነስቷል። ይህም ሀገራችንን በጂቡቲ የወደብ ድርሻ ባለቤት የሚያደርጋትና በወደቡ ክፍያ ላይም ድምስ እንዲኖራት ያስችላል። ጅቡቲም በበኩሏ፤ በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተመሳሳይ መልኩ ድርሻ ይኖራታል።
በኢትዮጵያ በኩልም ጅቡቲ የምትሳተፍባቸው የተመረጡ መሰረተ ልማቶች በጥናት የሚወሰኑ ናቸው። ርግጥ የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነቱ ሁለቱንም ሀገራት በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ ሰጥቶ መቀበል ይመስለኛል። በእኔ እምነት ይህ ሂደት ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ያተረፍንበት ጉብኝት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሱዳን ጋር የተፈራረሙት ስምምነትም ከሀገራችንና ከሱዳን ተጠቃሚነት አኳያ የታቃኘ ነው። ኢትዮጵያ በፖርት ሱዳን ላይ ለብቻዋ የምትጠቀምበት ወደብ በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ከስምምነት ላይ ደርሳለች። በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በተደረጉ ውይይቶች የጋራ መግባባት ላይየተደረሰ ሲሆን ይህም ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያም ሁለቱ ሀገራት የጋራ አቋም ይዘዋል። የሱዳን ፕሬዳንት ሐሰን አል በሽር ሀገራቸው ግድቡን በገንዘብ እስከ መደገፍ ድረስ ትብበር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አስታውቀዋል። በኢኮኖሚያዊ ትስስር ረገድም አዲስ አበባንና ካርቱምን በባቡር መስመር ለማስተሳሰር ተስማምተዋል። በሀገራቱ መካከል የንግድና የኢንቨስትመንት ልውውጡ እንዲጠናከር ለማድረግ ታስቧል። ይህ ሁኔታም ሁለቱ ሀገራት ካሏቸው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር አኳያ የሚያደርጉት ኢኮኖያዊ ትስስር በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።
በወደብ ልማት በኩል ልማቱንና በጋራ የማስተዳደሩ ስራው በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ ሀገራቱ ተስማምተዋል። ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የሱዳን ወደብን ለሰሜንና ሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስትጠቀም ብትቆይም፤ በጠቅላይ ሚኒስትራችን አማካኝነት የተፈራረሙት ትብብር ስራውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አኳያ ሱዳን አሁንም ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ፖሊሲ እንዲኖር እንደምትፈልግ ፕሬዚዳንት አልበሽር ገልፀዋል። ይህ የሀገሪቱ አቋም የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ዙሪያ ላለፉት ዓመታት ሲያራምደው ከነበረው አቋም ጋር አንድ ዓይነት ነው።
ዶክተር አብይ በተለያዩ ምክንያቶች በሱዳን እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ጥያቄውን ተከትሎ በሰጡት ትዕዛዝ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እንዲፈቱ ተደርገዋል። ይህም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ሀገራችን ምን ያህል ለዜጎቻቸው እንደሚጨነቁ የሚያሳይ ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኬንያም ያደረጉት ጉብኝት የሀገራችንን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው። ዶክተር አብይ በኬንያም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በውይይታቸውም መሪዎቹ ግንኙነታቸውን በንግድና ዲፕሎማሲ መስክ ለማጠናከር ተስማምተዋል። መሪዎቹ በኢኮኖሚያዊና ፀጥታ ጉዳዮች፣ በላሙ ወደብ ልማትና ኬንያ በየዓመቱ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ባሰበችው 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ አተገባበር ዙሪያም ተመካክረዋል።
መሪዎቹ የኢትዮጵያና ኬንያ ሞያሌን የምስራቅ አፍሪካ የቢዝነስና የንግድ ማዕከል እንድትሆን በጋራ ለማልማት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የሁለቱ ሀገሮች አንጋፋ መሪዎች የሆኑት ቀዳማዊ ኃይለስላሴና ጆሞ ኬንያታ ያስቀመጧቸው የልማት፣ ትብብርና የህብረት ራዕይ ለማሳካትና ግንኙነቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ በተለያዩ ምክንያቶች እስር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲለቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ተስማምተዋል። የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን መሰረት ያደረገ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ በቱሪዝም መስክ ለመተባበር መስማማታቸውም ተመልክቷል።
በተጨማሪም ሀገራቱ በሚዋሰኗቸው የድንበር አካባቢዎች በሚገኙ ወንዞችና የውሃ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሪዎቹ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ሀገራቱ በጋራ በሚያካሂዱት የፀረ ሽብር ዘመቻም በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንዲሁም አሸባሪውን አልሸባብን ማስወገድ ቀዳሚ ጉዳይ እንዲሆን ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሶማሊያ ለሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (AMISOM) ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ የሚቻልበትን አግባብ ለማመቻቸትም ተስማምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በውይይታቸው ወቅት የሀገራቱን የቆየና ታሪካዊ ግንኙነት ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። በንግግራቸውም ባለፉት ጊዜያት በተሰራ ስራ መኩራራት እንደማይገባና ከፊት ለፊት በርካታ ስራዎች መኖራቸውን በማንሳት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ኬንያም በፕሬዘረዳንቷ ኡሁሩ ኬንያታ አማካኝነት ኢትዮጵያ ኬንያ ነጻነቷን እንድትቀዳጅ ላደረገችው አስተዋጽኦ አቅርባለች። ፕሬዚዳንቱ በሀገራቱ መካከል በርካታ ስምምነቶች ቢደረሱም አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆኑን በማስታወስ ለተግባራዊነቱ ሁለቱም ሀገራት መስራት እንደሚኖርባቸው ጠይቀዋል። ስለሆነም ባለ ድርሻ አካላት ሀገራቱ የደረሷቸው ስምምነት በፍጥነት ገቢራዊ ይሆኑ ዘንድ እንዲሰሩና ከሀገራቱ ግንኙነት የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።
ኬንያና ኢትዮጵያ ከሁለት አመት በፊት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚያስችል የሁለትዮሽ ብሄራዊ ኮሚሽን ያቋቋሙ ሲሆን፤ በኮሚሽኑ አማካኝነትም የመከላከያውን ዘርፍ ጨምሮ ሀገራቱ ልዩ ግንኙነት የሚያደርጉባቸው ስምምነቶች ተደርሰዋል። የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ስብሰባ በፈረንጆቹ 2016 በኬንያ ተካሂዷል። ሁለተኛውና 36ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባ ደግሞ በያዝነው ዓመት በኢትዮጵያ ይካሄዳል።
ይህ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለየት ያለና ታሪካዊ ከመሆኑም በላይ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለሀገራቱ የሚያስገኝ ነው። በምሳሌነትም ሀገራቱ በየብስ ትራንስፖርት ለመገናኘት ከሞምባሳ-በሞያሌ-አዲስ አበባ የሚዘረጋ መንገድ ግንባታ በጋራ እያካሄዱ መሆናቸውን መግለፅ ይቻላል። ይህም የኢትዮ-ኬንያ ታሪካዊ ወዳጅነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረና በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት ከሶስቱ ሀገራት ጋር የደረሰው ስምምነት ‘ይበል!’ የሚያሰኝና የሀገራችንን እንዲሁም የሀገራቱን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው። ከጉብኝቶቹ ያተረፍነው እጅግ ብዙ ነው። እንዲህ ዓይነት ጉብኝቶች ወደፊትም ከሌሎች ሀገራት ጋር በተጠና ሁኔታ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።