Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዋልታው

0 303

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዋልታው

                                                           ሶሪ ገመዳ

የአገራችን ዕድገት ማገርና ዋልታ የሆነው የግብርና ልማት እመርታዎችን እያስመዘገበ ነው። ልማቱ አሁንም ቢሆን የአገራችን ዕድገት ዋነኛ ምሶሶ መሆኑን ቀጥሏል። ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ሚናውን እየተጫወተ ነው።

በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለው ዕድገት አገራችን ድርቅን እንድትቋቋም ያደረጋት ነው። በዘርፉ የተገኘው ከፍተኛ ምርት ለኢኮኖሚያዊ እመርታ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። በተለይ ትርፍ አምራች አካባቢዎች በድርቅ ሳቢያ ምርታቸው የቀነሰ አካባቢዎችን እንዲደገፉ እያደረጉ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጠናቃ፤ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ለማምጣት የተለመችበትን ሁለተኛውን የዕድገት ትልም ከተያያዘች ሶስተኛውን ዓመት እያገባደደች ነው። አራተኛውን ለመቀጠል በዝግጅት ላይ ትገኛለች። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አያሌ ለውጦችንም አስመዝግባለች።

ምንም እንኳን ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት አገራችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በኢኮኖሚው መስክ ሊፈጥረው የሚችለው እጅግ አነስተኛ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ባይካድም፤ የግብርናው ልማት ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህ ረገድ በተለይ ከምርት አኳያ የተፈጠረ ችግር አለመኖሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ይህም የሆነው መንግስት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ምሶሶ ለሆነው የግብርናው ልማት የሰጠው ትኩረት መሆኑ አይካድም።

የአገራችንን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማሳደግና ህዝባችንን ከድህነት ለማውጣት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት የግድ ይላል። መንግስትም ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይ ሶስተኛ ዓመት፤ በመጀመሪያው የዕቅድ ዓመት ላይ የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው። ዘርፉ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ ሃብት በመሆኑ ውጤት ሊያመጣ እያመጣ ነው።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት እንዲይሰመዘግብ ታስቦ ገቢራዊ እየረደገ ነው። የውጥኑ መጨረሻ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ ተችሏል። በዚህም መሰረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው ስምንት በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ዕቅድ ይሳካ ዘንድም በዋናነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ዋነኛ የሰብል ምርቶች በ16 በመቶ ያድጋሉ።

በግብርና ዕድገት ምክንያት ብቻ በዕቅዱ ዘመን አማካይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ 12 ነጥብ ሁለት በመቶ እንደሚደርስ ይታመናል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በዘርፉ የታዩት ለውጠች ይህን ማሳካት የሚያስችሉ መሆናቸውን መገመት ይቻላል። ያለፉትን ዓመታትን ትተን በዚህ ዓመት የመኸር ምርት ብቻ 360 ሚሊዮን ኩንታል እህል መገኘቱ የግብርናውን ተደራሽነት የሚያሳይ ነው። ይህም በዚህ የዕቅድ ዘመን ግብርና ዋነኛው የዕድገት ዋልታና ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ እንደሆነ ያረጋግጣል።

መንግሥት ኋላ ቀሩን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል። መንግስት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሰረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው።

አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ አገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ እንድትሆን እያደረገ ነው።

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች የዕድገቱ ማገር ሆነው ቀጥለዋል። በዚህም የመንግስት ፖሊሲ ትክክለኛነት መረጋገጥ ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር ተፈልጎ አይገኝም።

ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ እየሆነች ነው። ይህ እውነታ ደግሞ ዕድገታችን ትክክለኛ መስመር የያዘ መሆኑን በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ምስክርነት ያገኘ ነው።

ከአርሶ አደሩ ህይወት ጋር ተያይዞ በከርሰ ምድርና በገጸ ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል። በውሃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ውጤታማ ሆነናል።

አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም ችሏል። የመስኖ ልማት ስራው በበጋ የእሸት ምርቶችን ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ዓመታት ስራው በእጅጉ አድጓል። ለአርሶ አደሩ በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የህብረት ሥራዎች አማካኝነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ እየሆነ ነው።

የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል።

የአርሶ አደሩ በማህበርባ በመደራጀቱ በግል ሊፈቱ ያልቻሉ ጉዳዩችን በጋራ ለመፍታት መፍትሔ ሆኗል። መንግስት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው። በተጨማሪም አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የግብርናው ዘርፍ በማደጉ በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮችን ማፍራት ተችሏል። አሁንም ተጨማሪ ሞዴል አርሶ አደሮች እየተፈጠሩ ነው። ስለሆነም በሂደት የተጎናፀፍነው ድል ለላቀ የሁለተኛው ዕቅድ እያበቃን ስለሆነ በቀሪዎቹ የዕቅዱ ሁለት ዓመታት በአንድነት መንፈስ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል።

ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በትክክል ውጤታማ እየሆኑ ነው። በአፈጻጸሙ ከተጠበቀው በላይ መጓዙን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የምርትና ምርታማነት ዕድገት መጠን ለማሳደግ ብርቱ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም እንዲሁ።

እንዲሁም የግል ባለ ሃብቶችን ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። እናም የአገራችን ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው ግብርና ፍጥነቱን ቀጥሏል። ይሀን ፍጥነት በጋራና በመተሳሰብ መንፈስ በአንድነት ተረባርበን ልናስቀጥለው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy