Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዛሬ አግብተው ዛሬ አይወልዱም

0 351

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዛሬ አግብተው ዛሬ አይወልዱም

ኢብሳ ነመራ

የአሜሪካ መንግስት ኮንግሬስ በቅርቡ የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አያያዝ የተመለከተ RH 128 የተሰኘ የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። ይህ የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በተባበሩት መንግስታት የተሰየመ መርማሪ በሃገሪቱ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ ማጣራት እንዲያከናውን እንዲፈቅድ ያዛል። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን ኢትዮጵየን እንዲጎበኙ ጋብዞ ነበር። ሰሞኑንም በተመሳሳይ ግብዣ ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል። የጉብኝቱ ዓላማ ከፍተኛ ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ ተመልክተው፣ ችግሮችን ለይተው ገንቢ አስተያያት እንዲሰጡ ማድረግ ነበር። እነዚህ በአንድ ዓመት ውስጥ የተካሄዱ ሁለት የኮሚሽነሩ ጉብኝቶች የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዝግ እንዳልነበረ ያመለክታሉ።

ያም ሆነ ይህ፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚ/ር ዛይድ ራድ አል ሁሴን ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል። ይህን ጉብኝትም ያደረጉት በHR 128 ወይም በሌላ አካል አስገዳጅነት አይደለም። የጉብኝቱ ግብዣ በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበ ነው።

ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን በባለፈው ዓመት ጉብኝታቸው በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩትን እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጭምር ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በተፈጸመና በተጠረጠረ ወንጀል ታስረው የነበሩ ግለሰቦችን አነጋግረው እንደነበረ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ኮሚሽነሩ በጉብኝታቸው ማጠቃለያ ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ አለባት ብለው ያመኑባቸውን ችግሮች አሳውቀዋል። በወቅቱ በሃገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ቅሬታ እንደተሰማቸው አመልክተው ነበር። በአጠቃላይ ደስተኛ አልነበሩም ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ዓመት ኮሚሽነሩን ለጉብኝት ሲጋብዝ በወንጀል የተከሰሱና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ነን የሚሉ ግለሰቦች መኖራቸውን አልሸሸገም። በሃገሪቱ በተቀሰቀሱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች መኖራቸውንም አልሸሸገም። በወቅቱ የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ስራ ላይ እንደነበረም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህ ባለበት ሁኔታ የሰብአዊ መብት አያያዜን ተመልከቱልኝ ብሎ ከፍተኛ ኮሚሽነሩን መጋበዙ ብዙዎችን ሊያስገርም ይችል ይሆናል። ጉዳዩን በአግባቡ ላጤነ ግን፣ መንግስት ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶችን ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመለክት ነው። በቅድሚያ የኢፌዴሪ ህገመንግስት በመዕራፍ ሶስት ላይ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶችን የሚያረጋግጡ ድንጋጌዎችን ይዟል። ህገመንግስቱ ከዚህ በተጨማሪ የህገመንግስቱን ተፈጻሚነትና አተረጓጎም በሚመለከተው አንቀጽ 13 ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ በምዕራፍ ሶስት የተዘረዘሩት መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምመነቶችና ዓለም አቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማል ይላል። ይህ ህገመንግስታዊ ዕውነታ የሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች ጉዳይ በኢትዮጵያ ለመንግስት የዘፈቀደ ውሳኔ ያልተተወ፣ ህገመንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ያመለክታል።  ሆኖም ይህ በራሱ መብቶችና ነጻነቶች መከበራቸውን አያረጋግጥም።

ህገመንግስታዊ ድንጋጌው በራሱ መብቶችና ነጻነቶች መከበራቸውን ስለማያረጋግጥ፣ በህገመንግስቱ መሰረት የመንግስትን የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚከታተልና ይፋ የሚያደርግ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋማት እንዲቋቋሙ ተደርጓል። ይህም ቢሆን ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች መከበራቸውን ስለማያረጋግጥ፣ በየወቅቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ አፈጻጸም ክትትል የሚደረግበት የሰብአዊ መብት አያያዝ የድርጊት መርሃ ግብር ይዘጋጃል። በዚህ የሰብአዊ መብት አያያዝ የድርጊት መርሃ ግብር መሰረት ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዟን ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ታስገመገማለች።

እንግዲህ፣ ከላይ የሰፈሩት ህጎችና እርምጃዎች ግብ ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ ነው። ይሁን እንጂ በሃገሪቱ የሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች አያያዝ ሁኔታ ጥሩ የሚባል አይደለም። እንደየአተያያቸው አንዳንድ ወገኖች ደግሞ እጅግ አስከፊ ይሉታል። እጅግ አስከፊ የሚሉት ወገኖች ለዚህ የሚያቀርቡት አስረጂ፣ በክስና በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን፣ በአደባባይ ተቃውሞ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎችን ነው።

እርግጥ ነው፣ እነዚህን ድርጊቶች እንደሰብአዊ መብትና ነጻነቶች ጥሰት መውሰድ ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ መንግስት፣ ፖለቲከኞቹና ጋዜጠኞቹን ለክስ ያበቃቸውና በጥፋተኝነት ያስፈረደባቸው የፈቀዱትን አቋም በመያዛቸው፣ በማራመዳቸው፣ በመግለጻቸው፣ በመደራጀታቸው . . . አይደለም ባይ ነው። ከዚህ ይልቅ በሃገሪቱ ህጎች በወንጀልነት የተደነገጉ ድርጊቶችን በመፈጸም ጥርጣሬና መፈጸማቸው በማስረጃ በመረጋገጡ እንደሆነ ነው ሲያሳውቅ የቆየው።

ይህን ጉዳይ ለፍርድ ቤት የቀረቡ የጥፋተኝነት ማስረጃዎችን ወደጎን ገፍቶ እንደሰብአዊ መብትና ነጻነት ጥሰት ብቻ መመልከት ትክክል ነው ብሎ መውሰድ ስህተት ላይ የሚጥል ይመስለኛል። በድፍኑ ማስረጃዎቹን ወደጎን በመግፋት እንደመብትና ነጻነት ጥሰት መውሰድ ከፖለቲካ አቋም የመነጨ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው።

በተቃውሞ ሰልፎች ላይ የሚጠፋውን ህይወት በተመለከተ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ላይ ገዳይ ጥይት ተኩሶ ህይወታቸውን እንዲያጡ፣ አካላቸው እንዲጎል ማድረግ በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። ይሁን እንጂ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ተቃውሟቸውን የገለጹበት መንገድ ከግምት መግባት ይኖርበታል። መሳሪያ ታጥቀው ከነበረ፣ ከጸጥታ አስከባሪዎች ላይ መሳሪያ ለመንጠቅ ይሞክሩ ከነበረ፣ በሰላማዊ ዜጎች ህይወትና አካል ላይ ጉዳት የአያደረሱ ከነበረ፣ ዘረፋና በከፍተኛ ደረጃ የንብረት ውድመት እየፈጸሙ ከነበረ . . . በዚህ የሃይል እርምጃ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የከፋ ጉዳት ለመከላከል የሃይል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። ይህ እርምጃ በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎችን ህይወት ሊያጠፋ ይችላል። እዚህ ላይ መታየት ያለበት የሰዎች መሞት ብቻ ሳይሆን እርጃው የተወሰደበትን ሁኔታና ተመጣጣኝነቱም ጭምር ነው። የእርምጃው ተመጣጣኝ የመሆኑ ያለመሆኑ ጉዳይ ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል።  

በሃገራችን ባለፉ ሁለት ዓመታት ከአደባባይ ተቃውሞ ጋር የሰው ህይወት መጥፋተን መነሻ በማድረግ የወጡ አብዛኞቹ ሪፖርቶችና ዘገባዎች የሟቾችን ቁጥር ከማጋነን በተጨማሪ ስለተመጣጣኝነት የሚያነሱት ብዙም ነገር አልነበረም። ይህ ሪፖርቶቹና ዘገባዎቹን ፖለቲካዊ ዓላማም ጭምር ይኖራቸዋል ለሚል ጥርጣሬ ያጋልጣቸዋል። እናም የሁኔታውን ትክክለኛ ገጽታ አያሳዩም።

ያም ሆነ ይህ፣ በኢትዮጵያ በህገመንግስቱና በሌሎች ከህገመንግስቱ በመነጩ ህጎች የተደነገጉ የሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶችን የሚጣሱ መሆናቸው እውነት ቢሆንም፣ ይህ ለምሳሌ በደርግ ግዜ በቀይ ሽብር የግድያና አፈና ዘመቻ እንዲሁም በዘውትር የስርአቱ አሰራር ሲደረግ እንደነበረው ተቋማዊ አለመሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ የሚፈጸሙት፣ በአመዛኙ በፈጻሚዎች የስልጣን ገደባቸውን አለማወቅ፣ አድማዎችን ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ የመበተን የጸጥታ አስከባሪ ሃይል አባላት ክህሎት ጉድለት፣ የወንጀል ምርመራ ሳይንስ ክህሎትና ብቃት ማነስ . . .ወዘተ ናቸው። በዚህ ረገድ ተጠያቂነትን ተግባራዊ የማድረግ ክፍተትም መኖሩ አይካድም።

የኢፌዴሪ መንግስት በሃገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚ/ር ዛይድ ራድ አል ሁሴን እንዲጎበኙ ከአንድ ዓመት በፊትም ሆነ ሰሞኑን የጋበዘው በሃገሪቱ ምንም የሰብአዊ መብት ጥሰት አልተፈጸመም፣ ይህን አረጋግጡልኝ በሚል እምነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተቋማዊ አለመሆኑን፣ በዋናነት ከአፈጻጸምና ከብቃት ማነስ የሚመነጭ መሆኑን ታሳቢ በማደረግ እውነቱን ተመልክተው የሚሻሻልበትን መላ እንዲያመለክቱትና እንዲያግዙት በማሰብ ነው።

ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሃሰን ባለፈው ዓመት ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ጠንከር ያለ ቅሬታ አድሮባቸው የነበረ ቢሆንም፣ በዘንድሮ ጉብኝታቸው ግን መሻሻል መኖሩን ተናግረዋል። እርግጥ ነው መንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ በማሳለፍ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በወንጀል ተጠርጥረው የክስ ሂደት ላይ የነበሩና ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ ተረጋግጦ የተፈረደባቸውን ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ አድርጓል። ይህ እርምጃ በትክክል የሃገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚያስሳስባቸውን ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ስጋት አለዝቧል። በቅርቡ ወደስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማሰፋት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በግልም ሆነ በጋራ ለመነጋገር መንግስታቸው ያለውን ፍላጎት በይፋ መግለጻቸውም በገለለተኛ የመብትና ነጻነት ተማጋቾች ዘንድ ያለውን ስጋት ቀለል አድርጎታል።

በሰሞኑ የኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን ጉብኝትም ይህንኑ ታዝበናል። በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ጉብኝት አድርገው ከአባ-ገዳዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊዎች፣ ከኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒትርና በመጨረሻም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተገናኘተው የተወያዩት ኮሚሽነሩ በሰጧቸው መግለጫዎች በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎን መኖራቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን ከተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጧቸው መግለጫዎች፣ ኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት በማምጣት ወደ ተለመደው ተፅእኖ ፈጣሪነቷ ለመመለስ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኗን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ቆይታቸው ህዝቡ ውስጥ አዲስ የተስፋና የመነቃቃት ስሜት መመልከታቸውን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፣ ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለው እምነት ከፍተኛ መሆኑን መታዘባቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተጀመሩ መንግስታዊ የለውጥ ሂደቶችንም አድንቀዋል።

ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ክልል ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ ከሰሞኑ ባደረጉት ጉብኝት የእስረኞች መለቀቅን ጨምሮ የሚበረታቱ ለውጦች መታዘባቸውን ተናግረዋል። የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመትን ጨምሮ የተደረጉ መንግስታዊ የስልጣን ሽግግሮችና የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል የተጀመሩ የምርመራና ክትትል ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። የሁሉም ሃገሮች ዴሞክራሲያዊ እድገት በሂደት የሚገነባ መሆኑን እንረዳለን ያሉት ሚ/ር ዛይድ ራድ አል ሃሰን፣ በመንግስት የሚዘጋጁ እንደ ጸረ ሽብርተኝነት አይነት ህጎችና አዋጆች፣ የህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱና ሁሉንም ተወካዮች ያሳተፉ መሆን ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጣም አስፈላጊ ሃገር መሆኗን፣ እንዲሁም የሚመሩት ተቋም በተለያዩ መስኮች ሃገሪቱ የያዘችውን የዴሞክራሲ ጉዞ እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።

እንግዲህ፣ ሚ/ር ዛይድ ራድ አል ሁሴንም እንደገለጹት የአንድ ሃገር የሰብአዊ መብት አያያዝ በአንድ ቀን ጀምበር በአዋጅ የሚሰምር አይደለም። የሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶችን የማስከበርና የመጠበቅ ተግባር በሰዎች ነው የሚፈጸመው። ለዚህ ተግባር የሚዋቀሩ ተቋማትም አሉ። በመሆኑም ከአስፈጻሚዎች አመለካከትና ብቃት ማነስ፣ ከተቋሞች አደረጃጀትና አሰራር፣ አንዲሁም ተቋማቱ ካላቸው የተደራሽነት እጥረት ወዘተ የሚመነጩ ችግሮች ማጋጠማቸው ተጨባጭ እውነት ነው። በአጠቃላይ ህዝብ የሰበአዊ መብት ላይ ያለው የግንዛቤ ጉድለትም ክፍተት የሚፈጥርበት ሁኔታ አለ።

በሃገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በተለይ ስርአቱን በሃይል ለማስወገድ በይፋ አውጀውም ይሁን በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም ለሰብአዊ መብት አያያዝ አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆኑም እውነት ነው። እነዚህ አካላት የሚፈጥሩት ሁኔታ ከፈጻሚዎች ብቃትና ከተቋማዊ አቅም ማነስ ጋር ተዳምሮ ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም የሚያደርግ ሁኔታ ይፈጥራል።

እነዚህ ሁኔታዎች በአጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ በሂደት እየጎለበተ የሚሄድና የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የሚደረጉ ምርመራዎች በጥንቃቄና በፍጹም ገለለትኝነት መከናወን የሚገባቸው መሆኑን ያመለክታሉ። በመሆኑም በአንድ ሃገር ላይ የሚሰነዘር የሰብአዊ መብት አያያዝ ትችት በቅድሚያ ጥሰቶች ተቋማዊ አለመሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል። በመቀጠል ከጊዜ ወደጊዜ የሚታየውን መሻሻልና አጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ህጎች የሚፈጸሙበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል።

የሰሞኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን ጉብኝት የሰብአዊ መብት አያያዝ ሂደት መሆኑንና ከሚታየው መሻሻል አንጻር መታየት እንዳለበት ከግምት ያስገባና በሃገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ለውጥ በተስፋ የተመለከተ ነው። ኦሮሞዎች Har’a fudhanii haar’a hindhalchani/ዛሬ አግብተው ዛሬ አይወልዱም እንዲሉ፣ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲም ሆነ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ በመሻሻል ሂደት ውስጥ መመልከት ጨዋነት ነው። ከልብ ለኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚጨነቅ አካል፣ ያለው ተጠብቆ ተጨማሪ መሻሻል እንዲታይ ለማገዝ፣ ሁኔታውን በሂደት ውስጥ ነው የሚመለከተው። ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ ያለውን ያሳጣ እንደሆን እንጂ ያግዛል ብሎ መወሰድ ስህተትነቱ ያይላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy