Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመጀመሪያው የጉብኝት ቦታ…

0 551

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመጀመሪያው የጉብኝት ቦታ…

                                                              ሶሪ ገመዳ

ኢትዮጵያ ከሁሉም የጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ወዳጅነትንና ትብብርን የምታራምድ አገር ናት። የኤርትራ መንግስት ከጠብ አጫሪነት ተግባር ወጥቶ ለሰላምና ልማት የሚቆም ቢሆን ኖሮ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ የመጀመሪያው የጉብኝት ቦታ አስመራ ልትሆን ትችል ነበር።

ይሁን እንጂ የኤርትራ መንግስት በባህሪው ከእነዚህ ተግባሮች የማይታቀብ በመሆኑ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በተመረጡ ዕለት ለኤርትራ መንግስትና ሕዝብ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በማጣጣል አስመስክሯል። ነገር ግን ጠብ አጫሪው ጎረቤት አሁንም ቢሆን መፍትሔው ሰላም መሆኑን ተገንዝቦ የሰላም ጥሪውን በመቀበል በአዲስ የትብብርና የእድገት ጎዳና መራመድ ይገባዋል።

የኤርትራ መንግስት ለሰላም የቀረበለትን ጥሪ ቢቀበል፣ ተጠቃሚው ሁለቱም ህዝቦች ናቸው። በተለይም ከአገራችን ህዝቦች ጋር በደምና በስጋ የተሳሰረው የኤርትራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ከሚደርስበት ግፍና ሰቆቃ መላቀቅ የሚችል ይመስለኛል።

እርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ከዚያ ሀገር ህዝብ ጋር በደም፣ በታሪክ፣ በባህልና አብሮ በመኖር ሊፋቁ የማይችሉ ትስስር ያለው ህዝብና መንግስት የዚህን ህዝብ ሰቆቃና ስቃይ በዝምታ ሊያዩ አይችሉም።

በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝብ ሻዕቢያንና አገዛዙን በመሸሽ፣ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ሻዕቢያ በራሱ ህዝብ ላይ ያረቀቀውን የ“ተኩስና ግደል” ፖሊሲን አምልጠው ወደ ሀገራችን የሚመጡትን ኤርትራዊያን መጠለያ በመስጠት፣ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ተንቀሳቅሰው እንዲኖሩ በመፍቀድና እንደ ሀገራችን ዜጎች እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ በነፃ እንዲማሩ እያደረጉ ነው።

በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ወንድምና እህት የሆነው የኤርትራ ህዝብ ስቃይ የራሳቸው ጭምር መሆኑን እያሳዩ ነው። እርግጥም ወንድምና እህት ኤርትራዊያን ወደ ተስፋዊቷ ሀገር ተስፋቸውን ሰንቀው መምጣታቸው ትክክል መሆኑን በአሁኑ ወቅት ከሀገራችን ዜጎች ባልተናነሰ ሁኔታ ለእነርሱ እየተደረገ ያለውን ነገር የሚገነዘቡት ይመስለኛል። ይህም ኢትዮጵያ በሰላም የምታምንና ጎረቤቶቿም በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካላት ፍላጎት የመነጨ ነው።  

ለዚህ ደግሞ ኤርትራና ኢትዮጵያ ሰላም ማስፈን ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለሰላም ያላት አቋም የሚናወጥ አይደለም። አሁንም የኢትዮጵያ የሁልጊዜ ሰላም ወዳድ አቋም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነትም ቀርቧል።

በመሆኑም የኤርትራ መንግስት አንድ ቦታ ላይ ተቸክሎ የሚያቀርበውን የተሳሳተ አቋሙን ወደ ጎን በማለት ስለ ሰላም የተዘረጉ እጆችን መጨበጥ ይኖርበታል—ከሁሉም በላይ የህዝብ  ሰላምና ተጠቃሚነት ይቀድማልና።

የኤርትራ መንግስት የራሱን የተፈጥሮ ፀጋዎች ከመጠቀም ይልቅ በሌሎች አንጡራ ሃብት ላይ ተንጠላጥሎ ለማደግ የሚሻ ነው። በዚህም ሳቢያ ከነፃነት በኋላ የኤርትራ መንግስት ፍፁም ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለመጠቀም ቆርጦ ተነሳ። የሀገራችንን የተለያዩ ምርቶች በራሱ ስም እየተለጠፈ ከመሸጡም በላይ፤ ሀገራችን ውስጥ በነበረው ባንኮች ውስ ፎርጂድ እስከመስራት የደረሰ ወንጀሎችን ሲፈፅም ነበር።

ምን ይህ ብቻ! በድንበር አካባቢም የገንዘብ ልውውጡ እርሱን በሚጠቅም መንገድ ብቻ እንዲከናወን እስከመጠየቅ ደረሰ። ሁሉንም ጉዳዩች በትዕግስት ሲይዝ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ግን ሀገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማሻሻዎችን በመከተሉ ሻዕቢያ አኮረፈ። ኩርፊያውንም ባድመንና አካባቢዋን በመውረር ገለፀ። ሃቁ ይህ ነው።

ይህም ሲጀመር የወረራው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እንጂ ከድንበር ጋር የተገናኘ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ያም ሆኖ ሻዕቢያ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ወሰደው።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግን ቀደም ሲል እንዳልኩት ህዝቦችን የሚጠቅም አልነበረም። የአንድን ቤተሰብ ጎጆ ሁለት ቦታ የሚከፍልና ቤተሰብን ጭምር የሚለያይ ነው። ይሁንና እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የተወሰነው የአልጀርሱ ስምምነት ለህዝቦች ዘላቂ ሰላም የማይጠቅም መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱ ሀገራትን ህዝቦች የሚያቀራርብና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ይህን ለሁለቱም ሀገራት የሚበጅና በጠረጴዛ ዙሪያ እንደራደር የሚል ወሳኝ መግለጫን ወደ ጎን በማድረግ በኢፌዴሪ መንግስት የተዘረጉትን የሰላም እጆች አልቀበልም በማለት ጦረኝነትንና ትንኮሳን የሙጥኝ ያለው የኤርትራ መንግስት ነው።  

በመሆኑም በእኔ እምነት የድንበር ማካለሉ ጉዳይና የመደራደሩ ሁኔታ በኤርትራ መንግስት ሜዳ ላይ የሚገኝ ኳስ እንጂ በኢትዮጵያ መጫወቻ ሜዳ ላይ አይደለም። ይሁንና የኤርትራ መንግስት በራሱ ሜዳ ላይ ያለችውን ኳስ የውስጥ ችግሮቹ ማስተንፈሻ ከማድረግ አልቦዘነም። ዛሬ ግን ከዚህ የተሳሳተ መንገድ ወጥቶ ወደ ሰላሙ መንገድ መመለስ ይኖርበታል።

የኢፌዴሪ መንግስት ምን ያህል ለሰላም የወቆመ መሆኑን ለማሳየት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን “…ከኤርትራ ጋር ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለት ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ እጠይቃለሁ።…” በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ብቻ ሁነኛ ማሳያ ነው። ይህም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ከሰላም ለአንድም ደቂቃ ቢሆን ምን ያህል ትርፍ እንደሚያገኙ የሚያውቁ መሆናቸውን የሚያስረዳ ነው።

ሰላም በግለሰብ፣ በቤተሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለው ችግር ተዘርዝሮ አያልቅም። ሰላም የሰው ልጅ ወጥቶ ሰርቶ እንዲገባ፣ ቤተሰብ ልጅ ወልዶ ስሞ ለወግ ማዕረግ እንዲያበቃ፣ ልጅን ወደ ለማስተማር፣ የተመረተና የተሰበሰበ ምርት እንዲሰበሰብ፣ ሸቀጥ በገብይት እጦት ምክንያት እንዳይበላሽ የሰላም ዋጋ ከፍተኛ ነው። ይህም ሰላም በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ያለው ቦታ የማይተካ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በአንፃሩም ሰላም ከሌለ ማናቸውም ነገር ይጠፋል፣ ህይወትን በአግባቡ አለመምራት ብቻ ሳይሆን ክቡሩን ህይወት እስከማጣት የሚደርስ አደጋ መከተሉ አይቀርም። የሰላም መኖርና አለመኖር ንፅፅሮሽ ሁለት የማይገናኙ ነገሮች ቢሆኑም፤ ንፅፅሩን መመልከት የሰላም መኖርን ውድነት እንድናውቅ ያደርገናል።

ከሀገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ላለፉት 27 ዓመታት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። እናም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የአገራችን መንግስትና ህዝብ ናቸው።

ለኤርትራ መንግስት የቀረበው የሰላም ጥያቄ ምላሽ ቢያገኝ ኖሮ፣ የጠቅላይ ሚኒስትራችን የመጀመሪያው የጉብኝት ቦታ አስመራ ትሆን ነበር። አሁንም ቢሆን የአገራችን ሰላም ወዳድነት የሚቀየር ባለመሆኑ የኤርትራ መንግስት ይህን ምቹ አጋጣሚ መጠቀም ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy