Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀጠናው አምባሳደር

0 346

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቀጠናው አምባሳደር

ስሜነህ

 

በሃገራችን አሁን አንጻራዊ ሰላም የሰፈነ ቢሆንም ከአንጎበሩ የተላቀቅን ላለመሆናችን  ማሳያ የሚሆኑ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው። በጉጂና በጌዲዮ ብሄረሰቦች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለዚሁ ማሳያ ይሆናል። በዚህ ግጭት በርካቶች የተፈናቀሉ ሲሆን ህይወታቸውንም ያጡ ዜጎች መኖራቸው ተሰምቷል። ለዘመናት አብረው ተዋልደውና ቤተሰብ መስርተው በሚኖሩት ኢትዮጵያውያን መካከል እንዲህ ዓይነት ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲፈጠር ያስቻለው ምክንያት ምንድነው ብሎ መጠየቅ ከአገር አልፎ የቀጠናው የሰላም አምባሳደር ከሆነች ሃገር ይጠበቃል። ሌላኛው ማሳያ  ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉት ዜጎች መኖራቸው ናቸው።

 

በእርግጥ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ሁኔታ የሚመረምር ቡድን ወደ ባህርዳር መላኩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማስታወቁን የተመለከቱ መረጃዎች ወጥተዋል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚያብሄር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደገለፁት የተላኩት የኮሚሽኑ መርማሪ ባለሙያዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ጨምሮ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀም አለመፈፀሙን ያጣራሉ። የተገኙ መረጃዎችን በማጠናከርም የምርመራ ውጤቱ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ብለዋል። በምርመራ ውጤቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን የሚያመላክት ከሆነም በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ምክረ ሃሳብ አያይዞ እንደሚያቀርብም ተናግረዋል።ሌላም ማሳያ መጥቀስ ቢቻልም ለመነሻ እና መንስኤውን እና መፍትሄውን ከህገመንግስታዊ ስርአቱም ሆነ ከእሴቶቻችን አኳያ ለመጠቆምና ለማሄስ በቂ ማሳያዎች ይሆኑናል።

 

በሃገሪቱ የመዘዋወር መብት እንዲሁም ቋሚ የመኖሪያ ቦታ የመመስረት ለሁሉም ዜጎች በዘር በሀይማኖት በብሔር ልዩነት ሳይደረግ የተሰጠ ሰፊ መብት መሆኑን ከህገመንግስቱ አንቀፅ 32 ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል። ይህ መብት ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ መብት አይደለም በህጋዊ መንገድ የገቡ የውጭ ሀገር ዜጎችን ሁሉ የሚያጠቃልል መብት ነው።  የአማራ ክልል ህዝቦች በተለያዬ ጊዜ በየቦታው በየጊዜው ሲፈናቀሉ ማየት እንደልምድ በመቆጠሩ ሰሞኑን ከቤንሻንጉል ክልል ስለተፈናቀሉት 527 አባውራዎች መንግስት ከላይ በተመለከተው አግባብ ምርመራ መጀመሩ ተገቢ ነው። እነዚህ ሰዎች የተፈናቀሉበት መነሻ በሁለት ግለሰቦች የግል ግጭት መሆኑን በተፈናቀሉት ሰዎች በኩል የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች በህገመንግስቱ አይነኬ የተባሉት እና ባስቸኳይ ጋዜ አዎጅ እንኳን የማይታገዱት መብቶች ተጥሰውባቸዋል።

 

የኢፌድሪ ህገመንግስት በጊዜ በቦታ በዘር እንዲሁም በሀይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ለማንኛውም ኢትዮጰያዊ በኢትዮጰያ ውስጥ ተንቀሳቅሶ የመስራት እንዲሁም መኖሪያ ቦታ የመመሰረት መብት በአንቀፅ 32 (1) ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል።ነገር ግን ቤኒሻንጉል ላይ ዜጎች  የዚህ ሰፊ መብት ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም።

በጉጂና ጌዲዮም ሆነ ቤኒሻንጉል  በተነሳው ግጭት ሰዎች የሞቱት በህገመንግስቱ አንቀፅ 93 ላይ በግልጽ የተመለከተው በህይወት የመኖር መብት ተጥሶ ነው።  

እነዚህ የተፈናቀሉ ሰዎች ህይወታቸውን ሙሉ የደከሙበት ንብረት በዘረፋ እና በቃጠሎ መክኗል። ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ያላቸው ቢሆንም በመሬቱ የመጠቀም መብታቸው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ተጥሷል።ስለሆነም እነዚህን ችግሮች የፈጠሩ አካላት እንዲሁም በህገመንግስቱ አንቀፅ 13 ላይ የተቀመጠውን ሰብአዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ ያልተወጡ አካላት ሊጠየቁ ይገባል።

 

አሁን ኢትዮጵያን ለገጠማት ቀውስ ኢትዮጵያዊ መፍትሔ ለመሻት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ እዚህ ላይ “ብልሆች ከፈተና ይማራሉ” የሚለውን የጠቢባን ብሒል ልናስታውስ ይገባል፡፡እዚህ ጋር ብሔራዊ ፖለቲካዊ ቀውስ የገጠማት ኢትዮጵያ ብቻ እንዳልሆነች ልናጤን ይገባል፡፡ የእኛን አገር ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ችግሩ የጋራችን ሆኖ ሳለ፣ ሁላችንም የምንጋራው መፍትሔ ላይ ለመድረስ በሚያስችለን መልኩ፣ በብሔራዊ ቀውሳችን ላይ ተሰባስበን የጋራ ውይይት አለማድረጋችን ነው። አሁን ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ መድረኮች እየተፈጠሩ ነው።  

 

በዓለም ዙሪያ የተፋጠነ የኢኮኖሚ ሽግግራዊ ለውጥ ወይም “ትራንስፎርሜሽን” በማካሄድ ላይ የሚገኙ ሌሎችም ብዙ አገሮች ጥልቅ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከብራዚል እስከ ታይላንድ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ቱርክ ይኼን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ቀውሶች አንዳች የሚጋሩት ነገር አላቸው፡፡ እርሱም በፖለቲካው አመራር ላይ የተደላደሉት አካላት፣ የሥልጣን ትሩፋትና የበዛ ምቾቱ አዘናግቷቸዋል፡፡  አዲስ የተያዘው የመንግስት አቅጣጫም ይህንኑ ማጥራት ነው።

 

አገሮች መከፋፈልና መፈራራት ውስጥ ሲገቡ፣ ይህ ሁኔታ ለበለጠ አለመረጋጋት ይዳርጋቸዋል፡፡ አለመረጋጋቱ አንዳንዴ ክፉን በሚመኙ የውጭ ኃይሎች፣ አንዳንዴም በገዛ ማኅበረሰባቸው ውስጥ ባሉ ፅንፈኞች ሊቆሰቆስ ይችላል፡፡ ሌላው ይቅርና የዓለማችን ኃያላን የሚባሉት እንደ አሜሪካና ብሪታኒያ ያሉ አገሮችም፣ በብሔራዊ ተዋስዖዋቸው ላይ በሚጎሉ ከፋፋይ ኃይሎች ግፊት ሕዝባቸው ወደ ሁለት ተቃራኒ ጫፎች ሲጎተት ተመልክተዋል፡፡   

 

እኛ ዘንድ ያለው በዘውግ የተከፋፈለ ሕዝባዊ ምኅዳር ነው፡፡ ይህም ምኅዳር አውራጃዊ አጀንዳዎችና ዘውጌ ብሔረተኛነት በተጠናወተው ማኅበራዊ ሚዲያ አሁንም ይበልጥ ወደ ተቃራኒ ጎራዎች እየተጎተተ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግልጽ በሆነ ሕዝባዊ መድረክ ወደ አንድነት የሚያመጣ ብሔራዊ ውይይትን በምንሻበት በዚህ ጊዜ፣ በምትኩ እያየን ያለነው ቁጥራቸው የበዛ፣ መሳ ለመሳ የሚጓዙ ሴራ ተኮር ክርክሮችን ሆኗል፡፡ ይኼ ችግሮቻችንን ሊፈታልንና አገራችንን ወደፊት ሊያራምዳት አይችልም፡፡

በሌሎችም አገሮች እንደሆነው ሁሉ፣ በኢትዮጵያም የአብዛኛዎቹ ዜጎች ፍላጎት ለማኅበረሰባቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለራሳቸው ምርጥ የሆነውን ነገር ለማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ከመሻት የዘለለ አይደለም።ግን ደግሞ የፖለቲካው መዋቅር በዓይነተኛነት የኢትዮጵያ ዘውጌ ብሔረተኛ ቡድኖችን ባማከለ ሁኔታ ነው የተቀረፀው፡፡ የ1987 ዓ.ም. የብሔር ብሔረሰቦች ሕገ መንግሥት ሁላችንም የምንገነዘባቸው አሳማኝ ታሪካዊ ምክንያቶችን ታሳቢ አድርጎ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ሥር የሰደዱ የታሪክ ጠባሳዎች ለማከምና ለዚህች ታላቅ፣ ባለብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ሕዝቦች በሙሉ የእኩልነት መብትን በማጎናፀፍ ዓላማ ነው የተቀረፀው፡፡ ያ መቼም ሊቀለበስ የማይችል ግዙፍና ታሪካዊ ዕርምጃ ነው፡፡ የትኛዎቹም ትልልቅና ውስብስብ የብዙ ብሔር ማንነቶች ያሉባቸው አገሮች የፌዴራል ሥርዓት ይከተላሉ፡፡ ኢትዮጵያም ይኼንን መስመር መምረጧ ትክክል ነበር፡፡

 

ነገር ግን የትኛውም የፌዴራል ሥርዓት በሒደት የሚዳብር እንጂ አንዴ ተሠርቶ የሚያበቃ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ በየጊዜው ከሚመጡ ተለዋዋጭ ሁነቶች ጋር ተጣጥሞ መሄድ ይኖርበታል፡፡ ማንነቶች በሒደት ያድጋሉ፡፡ ብሔሮች ባህሪያቸውን ይቀይራሉ፡፡ የብሔርተኝነት ስሜት ኑሮውን በግብርና ላይ በመሠረተ ማኅበረሰብና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር በሚያደርግ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለው ገጽታ ሙሉ በሙሉ የተለያየ ነው፡፡ ባለፉት የሩብ ክፍለ ዘመን ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ያልታየ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ እጅግ ተለውጣለች፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አስተዳደራዊ ተግባራት ግን፣ ከሁነቶቹ ጋር በተጣጣመ መልኩ አልተለወጡም፡፡

 

በእርግጥም በክልሎች ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ እውነተኛ ብሶቶች፣ መፍትሔ የሚሹ እውነተኛ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን በመሠረቱ ካየነው ይኼ የኦሮሞ ፣ የአማራ ፣ የትግራ ወይም የደቡብ ሕዝቦች ችግር አይደለም፡፡ ይልቁንም ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ሕዝቦች፣ አፋር፣ ጋምቤላ ወዘተ ውስጥ የሚታይ የኢትዮጵያ ችግር ነው፡፡ ይኼ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ችግር በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ከሞላ ጎደል የተለያየ ገጽታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የትኛውም ክልል የገጠመውን ችግር፣ ከሌሎቹ ክልሎች ተለይቶ በራሱ ሊፈታው አይችልም፡፡

 

የዜግነት ዓይነተኛ ትርጉሙ የማይገሰሱ የግለሰብ መብቶችንና በሃይማኖት፣ በዘር፣ በብሔር ወይም በፆታ ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት ለሁሉም በእኩልነት የሚከበሩ የጋራ የዜግነት መብቶችን እሳቤ ይይዛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ባለን ማንነትና እንደ ዘውጌ ብሔረተኛ ቡድኖች አባልነታችን ባሉን ማንነቶች መካከል ሚዛን እንደሚኖረን ሁሉ፣ ባህልና ቀንቋን ባማከለው የክልል ፖለቲካና የዜጎች የጋራ ሕይወትን በሚመለከት ፖለቲካ መካከልም ሚዛን ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ የቀጠናው አምባሳደር በመሆናችን ልክ የተቃኘ እይታና ጉዞ ያስፈልገናል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጂቡቲ በነበራቸው ጉብኝት ለጂቡቲ ፓርላማ አባላት  ባደረጉት ንግግር የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ተወካዮች አቅም መጠናከር ያለውን ጥቅም አጉልተው መናገራቸውን እዚህ ጋር ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡ “ሁላችሁም እንደምታውቁት ታሪካዊ ግንኙነታችን ተምሳሌትነቱ ለኢጋድ አባል አገሮች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አገሮችም ጭምር ነው፡፡ ግንኙነታችን የተለየ ነው፡፡ አንድ ዓይነት ሕዝብ ግን በሁለት ሉዓላዊ አገርነት የምንኖር ነን፡፡ የኢኮኖሚ ውህደቱን ይበልጥ ለማሳደግና ለማጠናከር እንሠራለን፤” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጂቡቲ ፓርላማ አባላት ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሁለቱ አገሮች የእርስ በርስ በመረዳዳት፣ አገራዊና ቀጣናዊ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት እንደሚተባበሩም ተናግረዋል፡፡

የሱዳኑም ጉብኝት በተመሳሳይ ያለንበትን ደረጃ የሚያሳይ እና ከላይ የተመለከተው አይነት ግጭት የማይመጥነን መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። በእርግጥም “ዕጣ ፈንታችን በዓባይ ወንዝ ለዘለዓለሙ የተገመደ ነው”፤ በማለት፣ ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት ምን ያክል ጠንካራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

“በሦስትዮሽ ውይይት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የናይልን ውኃ እንዴት በፍትሐዊነትና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሚቻል እየተነጋገሩ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም ማድነቅ እወዳለሁ፤” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተናግረዋል፡፡የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽር በበኩላቸው፣ ሁለቱ አገሮች ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡“ለአካባቢው ሰላምና ደኅንነት የምንሠራውን ይበልጥ ማጠናከር እንፈልጋለን፡፡ በተለይ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት በኢጋድና በሁለትዮሽ መንገዶች እየሠራን ነው፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተስማማንባቸውና የሱዳን አቋም የሆኑ ጉዳዮች አሁንም እንዲጠበቁ፣ ሱዳን ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡ይህ ደግሞ ከውስጥ በላይም በውጭ ያለንን አምባሳደርነት የሚያረጋግጥ እና እዚህም እዚያም ከላይ በተመለከተው አግባብ የምንገባባቸው ግጭቶች ይህን ገጽታ እንዳያስነጥቁን የሚያስጠነቅቅ ነው።

 

ይህን በሚያጠራና ሃገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ በሚያስችል ጥሩ ጅምር ላይ የምንገኝ ቢሆንም ያለ ጥርጥር ከፋፋይ ድምፆች መሰማታቸው አይቀርም፡፡ ጥላቻን የሚሰብኩ ዛሬ በቁሙ ያለ ሁሉ ድምጥማጡ ቢጠፋ፣ ሁሉንም ነገር ያላንዳች ችግር መልሰን ልንተክለው እንችላለን ሲሉ ለምድር ለሰማይ ቃል የሚገቡም ይኖሩ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ድምፆች አጀንዳችንን እንዲቀርፁልን ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ ብሔራዊ ክርክርና ውይይታችን ከአገር ወዳድነት ጋር በተቆራኘው መካከለኛው መንገድ ላይ መልህቁን መጣል ይኖርበታል፡፡ የወጣቶቻችን አዎንታዊ ዕምቅ አቅም አስተዋፅፆ ይኖረዋል፡፡ ይኼን በመሰለው አገራዊ ተዋጽኦ፣ ጥበብና ሁሉን አስማሚው መካከለኛ መስመር አሸናፊ ሆኖ  እንዲወጣ መስራት ከሁላችንም ይጠበቃል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy