Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የእማኝነቱ ምስጢር

0 326

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የእማኝነቱ ምስጢር

                                                       ዘአማን በላይ

የዚህ ፅሑፍ አነሳሽ ምክንያት ከመሰንበቻው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም “አይ ኤም ኤፍ” (IMF) በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ሀገራችን የስምንት ነጥብ አምስት በመቶ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ያቀረበው የእማኝነት ትንበያ ነው። እማኝነቱ ሀገራችን በአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን የዕድገት መሪነቱን ከጋና እንደምትረከብም አስታውቋል። ምንም እንኳን የእማኝነት ትንበያው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከያዘችው የ11 ነጥብ ሁለት በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አኳያ ዝቅ ያለ ግምት ቢሆንም፤ ተቋሙ የሰጠው ምስክርነት በራሱ ትልቅ በመሆኑ ምስጢሩን መረዳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ርግጥም ‘እውን የዚህ እማኝነት ምስጢር ምን ይሆን?’ ብለን መጠየቅም ይኖርብናል።

ይህን ጥያቄ ማንሳት የሚያስፈልገው፤ በአንዳንድ ሀገራት ውስጥ የሚከሰቱ ቀውሶች ኢኮኖሚያቸው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ስለሚታወቅ ነው። ዳሩ ግን በአገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጊዜያዊ ቀውስ ተከስቶ ነበር። ታዲያ ኢትዮጵያ ይህ ቀውስ ሳይበግራት አሁንም የንግድ እና የኢንቨስትመንት ማዕከል ሆና እንደምን ልትቀጥልና በያዝነው ዓመት በአፍሪካ የዕድገት መሪነቱን ከጋና እንደምን ልትረከብ እንደቻለች እውነታውን መገንዘብ ይገባል።

በእኔ እምነት ሀገራችን በተለይ ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ገደማ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተደማምረው በቀውስ ውስጥ የነበረች ቢሆንም፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት ግዙፍ ስራዎች ችግሮችን ተቋቁመው አሁን ለምንገኝበት ጠንካራ ቁመና ያበቃን ይመስለኛል። በአሁኑ ወቅት የተፈጠሩትን ችግሮቹን በዘለቄታው ለመፍታት የሪፎርም እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ በመሆናቸው አገራችን ለወደፊቱ የሚጠብቃት ተስፋ የላቀ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም።

ይህ ሃቅ ለኢትዮጵያና ለዜጎቿ ታላቅ ተስፋን የሚያሳይ ነው። የአገራችን ዕድገት መሰረቱ ጠንካራ በመሆኑ በችግር ጊዜ ውስጥም ቢሆን አሉታዊ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል ነው። እናም ዛሬም ሆነ ነገ ይህን የታላቅ ሀገርና ህዝብ ተስፋን ዕድገት በመመካከር፣ በመወያየትና በመተሳሰብ ማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ይመስለኛል።  

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባለፉት ዓመታት የተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ስልቶች በችግር ጊዜ ውስጥም ቢሆን ጠንካራ፣ ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማረጋገጥ ችሏል። በቀውስ ጊዜ ውስጥም ቢሆን ተፈትኖ ጠንካራነቱን ማስመስከሩን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጭምር እማኝነት እየሰጡበት የመጡት እውነታ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ነው። ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ የገቡ ፓርኮችም አሉ። ይህ የመንግስት ተግባር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ተግባር ነው።

በሁሉም የልማት ዘርፎች ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ስኬቶች በችግር ወቅትም ቢሆን ኢኮኖሚውን እንደ ካስማ ደግፈው መያዛቸው አይታበይም። በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡት የልማት እመርታዎች የአጠቃላዩ ሀገራዊ ዕድገት ድምር ውጤቶች ናቸው። በተለይም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመከናወን ላይ የሚገኙት የግብርናው ዘርፍና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለዕድገቱ መፋጠን ጉልህ አስተዋፅኦን እያበረከቱ ይመስለኛል።

ከግብርና አኳያ የዕድገቱ ምንጭ በአነስተኛ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቤተሰቦች በሚካሄድ ልማት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ይታወቃል። ባለን አቅም የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋልና የኤክስቴሽን ስርዓቱን በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በማድረግ እጅግ የላቀ የምርታማነትና የምርት መጠን እየተመዘገበ ነው።

በተለይም መንግስት ከአርሶና አርብቶ አደሩ ጋር በመሆን ከግብርና አኳያ በሰብል ልማትም ሆነ በእንስሳት ሃብት ልማት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የመስኖ ስራን ጨምሮ የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ እንዳይሆኑ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ ነው።  

አሁን ባለው ቴክኖሎጂ የማምረት አቅማቸው ደረጃ ለተቃረቡ ሞዴል አርሶ አደሮች ተጨማሪ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማዘጋጀት የማባዛትና የማሰራጨት ስራም በመከናወኑ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል። ከስትራቴጂክ የምግብ ሰብሎች ምርታማነት መጨመር በተጓዳኝ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የማምረት አቅምን ለማሻሻል በሆርቲካልቸርና በእንስሳት ሃብት ልማት እንዲሁም ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ በማተኮር ርብርብ እየተደረገ መሆኑም የውጤቱ አንድ ክፍል ነው ማለት ይቻላል።

በተለይም ከግብርናው ጋር የተያያዙ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን መሰረት ለማስፋት የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪያችን በማስፋት ረገድ እየተከናወነ ያለው ተግባር ለኢኮኖሚው ጥንካሬ አንድ ግብዓት ሆኗል። በሌላ በኩልም በግብርናው ዘርፍ አገራዊ ባለ ሃብቶች በስፋት እንዲሰማሩም መደረጉም ለኢኮኖሚው ጥንካሬ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። የእነዚህና ሌሎች በግብርናው መስክ የሚከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያ በልማት ዕቅዱ ዘመን በዘርፉ ለማሳካት ያሰበችውን ትልም የሚያረጋግጡ ናቸው።

የኢኮኖሚያችን ማገር ከሆነው ከግብርናው ዘርፍ ባሻገር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እያደረገው ነው። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ነው። ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ የገቡ ፓርኮችም አሉ። ይህ የልማት ተግባር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የውጭ ቀጥተኛ በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ሆነ በነባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምርታማነት የጥራትና የተወዳዳሪነት ደረጃ እመርታና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በከፍተኛ ደረጃ መንቀሳቀስ እንዲቻል የሚያደርጉ ናቸው። በልማት ዕቅዱ ዘመን በኢኮኖሚው ላይ የሚታይ መዋቅራዊ ለውጥን ለማስጀመር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። ይህ ማለት በ2012 ዓ.ም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ እንዲል የሚያደርገው ነው።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ያሳካል ተብሎ ይታመናል። አገራችን ለያዘችው የመካከለኛ ገቢ ራዕይን ለማሳካትም መደላድል እንደሚፈጥርም እንዲሁ።

ርግጥ መዋቅራዊ ለውጡን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። ዛሬን ከነገ ጋር ብናስተያየው፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም ነበር። ይህን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆኑ ግልፅ ነው።

ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሳለጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያስገኘው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አሌ የሚባል አይደለም። የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ የውጭ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው። በዚህም የውጭ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ግኝትን በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል። ይህም የኢኮኖሚው ዋልታ የሆነውን ግብርና በመደገፍ ለዕድገቱ የራሱን ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ ላለፉት 16 ተከታታይ ዓመታት እየተመዘገበ የመጣው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ኢኮኖሚው በጊዜያዊ ቀውስ በጉልህ ሁኔታ እንዳይጎዳ አድርጎታል። በችግር ውስጥ ሆነንም ምጣኔ ሃብታችን ግለቱን ጠብቆ መጓዙና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እማኝነት የመቸሩ ምስጢር ሃቅም ይኸው ይመስለኛል።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት ላይ ሆነን ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመሪነቱን ቦታ ከጋና እንደምትረከብ የገንዘብ ተቋሙ ይፋ ማድረጉ፤ ሀገራችን ወደፊት የሚኖራትን ብሩህ ተስፋ የሚያመላከት ነው። ይኸውም ለውጡ ውጤታማ ሆኖ ሲቀጥልና የሀገራችን ሰላም ወደ ቀደመው ስፍራ በአስተማማኝ ሁኔታ ሲመለስ ዕድገቷ በላቀ መልኩ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን ነው። በመሆኑም ከሰላማችን የምናገኘውን የዕድገት ትሩፋት ለመቋደስ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን በጋራ መፍታት ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy