Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዜጎች መከታ

0 286

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዜጎች መከታ

                                                     ሶሪ ገመዳ

የኢፌዴሪ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት የአገራችንን የዲፕሎማሲ ሥራዎቻች ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ተግባር በሌሎች አገራትም መቀጠል ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም መንግሥት ለዜጎቹ እያከናወነ ያለው ተግባር ትክከለኛውን ማንነቱን እያንፀባረቀ ስለሆነ ነው። ይኸውም ምን ያህል ተቆርቋሪና አሳቢ መሆኑን በገሃድ በማሳየቱ ነው።

በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ያካሄዱት ጉብኝት ብሄራዊ መግባባትን በማጠናከር ረገድ የጎላ ሚና ተጫውቷል። የፀጥታ ስጋትን በማስወገድም አስተዋጽኦው የሚታይና የሚጨበጥ መሆኑ በተጨባጭ ታይቷል።

በውጭ አገርም በኬንያና በሱዳን እንዲሁም በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዲለቀቁ መደረጉ፤ መንግሥት ለዜጎቹ ያለውን ቅርበትና ተቆርቋሪነት እንዲሁም መከታነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ከማንም የመሰወር ጉዳይ አይመስለኝም።

እናም ይህ በአዲሱ የመንግስት አመራር እየተካሄደ ያለው አስመስጋኝ “ዜጋ ተኮር” ተግባር ሊደነቅና ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ነው። መንግስት የዜጎች መከታ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት ክስተት ነውና።

እንዲህ ዓይነቱ ቅን የሆነ አስተሳሰብ በመንግስት ደረጃ ብቻ መፈፀም የለበትም። ዜጎችም ይህን መሰሉን አስተሳሰብ መላበስ አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትረሩ ከሳዑዲ አረቢያና ከተባበሩት አረብ ኢምሬት የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ቆይታ መልስ በሚሌኒየም አዳራሽ ያሳሰቡትም ይህነኑ ነው። እርሳቸው የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሁሉም ዘርፎች ባለ ራዕይ መሪዎች ያስፈልጓታል ብለዋል።

አሁን በትምህርት ላይ የሚገኙትን 29 ሚሊየን ያህል ዜጎቿ ለተሻለች ኢትዮጵያ ወሳኝ መሆናቸውንና ወጣቱ ትውልድ የመወያየት የመደማመጥና የመከባበር ባህል ማዳበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል። በተለይም ስለ ራዕይ በግልፅ መወያየትና መነጋገር እንደሚገባ ዶክተር አብይ በሚሌኒየም አዳራሽ መሳጭ ንግግራቸው አብራርተዋል።

እርግጥ ለወጣቱ ራዕይ ያስፈልገዋል። ወጣቱ ችግሮችን ‘ታግዬ አሸንፋለሁ፣ ነገ እለወጣለሁ’ በሚል መንፈስ መወጣት እንዳለበት እንዲሁም በስሜታዊነት ሳይሆን በ“ምክንያታዊ” አስተሳሰብ መመራት ይኖርበታል። እናም በአዲስ የስራ መነሳሳት መንፈስ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት ይመስለኛል።

መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ለወጣቱ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ ገልጿል። ወጣቱ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሱ ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሉት በመሆኑ ጥያቄዎቹን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠው አስታውቋል። በዚህም መሰረት ተንቀሳቃሽ ፈንድ ከመመደብና ወጣቱም ተጠቃሚ እንዲሆን ከክልሎች ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።

ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራችን ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርበታል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ይህን ስሜታቸውን በራዕይ ካገዙት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “ስለ ራዕይ መወያየትና መነጋገር ይጠበቅባቸዋል” ያሉት ከዚህ ተነስተው ይመስለኛል።

በራዕይ የሚመራ ወጣት ውጤታማ ይሆናል። በየተሰማራበት ቦታም በውጤት የታጀበም ይሆናል። ተገቢ ሀገራዊ ክብርንና ዕውቅባንም ይጎናፀፋል። ዶክተር አብይ “በዚህ ዓመት በሀገሪቱ በሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች የክብር ተመራቂዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚያዘጋቸው የውጭ ሀገር የከፍተኛ ትምህረት ስኮላር ሽፕ ተጠቃሚ ይሆናሉ” ያሉትም ለዚሁ ነው።

ሀገሪቱ የህፃናትን አስተሳሰብን ለመቅረጽና ለነገ ማንነታቸው መሰረት ለመጣል ህፃናትን መሰረት ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ስርዓት ሊኖር ይገባል። አስተሳሰብን በመቅረጽ ረገድ የሃይማኖት መሪዎች፣ መምህራን፣ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

እርግጥ የነገዎቹ ወጣቶች የዛሬ ህፃናት ናቸው። በህፃናት ላይ የሚሰራ የአስተሳሰብና የአመለካከት ስራ የተሻለች ሀገርን ለመገንባት ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ይህም በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ካለው ሚዛናዊ አስተሳሰብን የማጎልበት ተግባር ጋር ተደምሮ ነገ በተሻለ ዕይታ የምትመራ ኢትዮጵያ እንድትኖር እገዛ ያደርጋል። በሀገራችን ህገ መንግስት ላይ የተቀመጡ መብቶችንም በሚዛናዊነት ለመጠቀም ያስችላል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ማንኛውም ዜጋ ጥያቄዎችን በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚያቀርብበትን አሰራርና መብት እንዳስቀመጠ በሚገባ ያውቃሉ።

በተለያዩ ጊዜያትም ይህን መብታቸውን እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ዳሩ ግን ይህን መብታቸውን በሰላማዊ ትግል የሚያጠናክሩነትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም የህዝቡን ፍላጎት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ጋር ነጥሎ በመመልከት ሰላማዊ ትግሉን ማጎልበት ይገባል። ይህን እውነታ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና ህገ መንግስታዊ መፍትሔ መሻት የዜጎች ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በፅንፈኞች እንዲሁም በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች ተጠልፎ ህገ ወጥ በሆነ መስመር እንዳይጓዝ አሁንም ሚዛናዊ አስተሳሰብን፣ የሀገርንና የህዝብን ራዕይ ማጤን የግድ ይላል። በተለይ ወጣቶች ራዕያቸውን በመሰነቅ ወደፊት መራመድ ይኖርባቸዋል።

ስርዓቱ የዛሬው ወጣት ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። የአገራችን ወጣት ከ27 ዓመት በፊት እንደነበሩት ወጣቶች በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ የሚሄድ አይደለም። ዛሬ ቀና ብሎ በማንነቱ በመኩራት እንዲሁም በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋፅኦ መጠን ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው። ለምሳሌ ያህል ምንም እንኳን ስፋትና ጥልቀቱ እንዲሁም ከአፈፃፀም ጋር በተያያዘ ዕድሉ ገና የሚቀረው ቢሆንም፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ አነስተኛና ጥቃቅን የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ ሆነዋል።

ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጠቅመው አገራቸውን ያሳደጉ ወጣቶች ቀላል አይደሉም። ይህም በስርዓቱ ውስጥ ወጣቶች ተጠቃሚነት ስለ መሆናቸው አንድ ማሳያ ነው። የአገራችን ወጣት ከስርዓቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ምክንያቱም የራሱ ስርዓት መልሶ ራሱን ሊጎዳው የሚችልበት ምንም ዓይነት አመክንዩ ስለሌለ ነው። እናም ወጣቶቻችን ራዕያቸውን በመያዝ፣ በጠራ ሚዛናዊ አስተሳሰብ በመመራት የበኩላቸውን አገራዊ ሃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል። መንግሥት የዜጎች መከታ መሆኑን በዚህ ከላይ በጠቀስኳቸው ተግባሩ ሲያሳይ ወጣቶችም የድርሻቸውን በዚህ ሁኔታ ሊወጣ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy