Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዜጎች ክብር ሲረጋገጥ…

0 316

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዜጎች ክብር ሲረጋገጥ…

                                                              ደስታ ኃይሉ

የኢፌዴሪ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችን ከሱዳን፣ ከኬንያና ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች እንዲለቀቁ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ይህም መንግስት ለህዝቡ ያለውን ወገንተኝነት የሚያሳይ ነው።

መንግሥት ለዜጎቹ ጥቅም፣ ደህንነትና ክብር መረጋገጥ ያለውን የማይናወጥ አቋም በገሃድ የታየበት ሁኔታም ነው። ይህ የመንግሥት ተግባር ለዜጎቹ ሁለንተናዊ መብቶች ምን ያህል ተቆርቋሪ እንደሆነና በአገራችን ውስጥ አንድነትንና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ከሁሉም በላይ ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህዝቦችን አንድነት በሚፈለገው መጠን እንዲያጠናክረው ያደርጋል።

በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ የህዝቦች አንድነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ምክንያቱም ሀገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት በህዝቦች ተጋድሎ እውን የሆነና በእነርሱው ፈቃድ ብቻ ማናቸውም ጉዳዩች እልባት የሚሰጣቸው መሆኑ ነው።

ፌዴራላዊ ስርዓቱ ባለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት የህገ መንግስቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ እንዲሆኑ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን መቀጠላቸውን ማንም አይክድም።

በአሁኑ ወቅት በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል። የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ፀድቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ አግኝተዋል። ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ አረጋግጦላቸዋል።

የዜጎቻችን ከተለያዩ አገራት ማረሚያ ቤቶች መለቀቅ እነዚህ አንድነቶች ይበልጥ በጋራ መንፈስ እንዲከናወኑና አዲሲቷ ኢትዮጵያ የእኔ ናት የሚል መንፈስ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።

በአገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል።

ይህ ሁኔታም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንድነትን ለሚያጠናክሩና መሰረቱን ለሚያሰፉ እንጂ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈፀም አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች እንዳይስፋፉ ያደረገ ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ መንግስት የታገለለትንና በህገ መንግሥቱ ውስጥ ተካትቶ ዛሬም ሆነ ነገ በፅናት የሚያምንበትን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማይገሰሱ መብቶች ላይ ከቶም ቢሆን ድርድር የሚያውቅ አይመስለኝም። ከ26 ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራቶች ስንቃኛቸው የሚያሳዩን ዕውነታዎች ይህንኑ ነውና።

እርግጥ የብሔረሰቦች መብት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለትና ለተግባራዊነቱ ህዝቦች በሙሉ የተረባረቡበት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ገዥው ፓርቲም ይሁን የሀገራችን ህዝቦች ያላቸው አቋም መቼም ቢሆን ሊቀለበስ የሚችል አይደለም።

እናም ከሚያራምዱት ፖለቲካዊ ርዕዩተ-ዓለም አኳያ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በህልም ዓለም ቅዠት ሲያፈርሱ የሚያድሩት የአገራችንና የህዝቦቿ ጠላቶች፣ አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎች እንጂ፤ በህገ መንግሥቱ ያገኘውን መብት ተጠቅሞ በሰላማዊ ሁኔታ ሥራውን በማከናወን 27 ዓመታትን የተሻገረውና የመብቱ ባለቤት የሆነው የአገራችን ህዝብ አለመሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል።

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከግጭት ጋር የተያያዙ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁንና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ተጫውቷል። ይህ የአገራዊ አንድነት ሁኔታ ይበልጥ መጥበቅ አለበት። ታዲያ ለዚህ ጥንካሬያችን ህገ መንግስቱን ምርኩዝ ማድረግ ይኖርብናል።

በህገ መንግስቱ ላይ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመገንባት ቃል ገብተዋል። በዚህ ሰነድ መሰረት እየተመሩም ኢኮኖሚቸውን አሳድገዋል። በአንድነታቸው ጥላ ስር ሆነው የቀጠናው መሪነት ሚናቸውን እያጠናከሩ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ ተደርገዋል።

ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ተደርጓል። የዜጎች ከእስር ቤት እንዲለቀቁ የማድረግ ተግባር ይህን አንድነት በማጠናከር ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር ነው።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የህዝቦች የጋራ የሰላምና የልማት መናኸሪያ እንዲሁም ‘ሁሉም ህዝብ የእኔ ነው’ የሚል አስተሳሰብ እንዲራመድባትና በጋራ የሚታደጉባት አገር መሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል። ይህ ተግባር በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ ክብር የሚቸረው መሆኑን ያሳያል።

በኢትዮጵያችን እየተተገበረ ያለው ስርዓት ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን እንዲጎናፀፉ ከማድረግ ባለፈ የዜጎችን ክብርና ችግር የሚመለከትና ሰቆቃቸውንም የሚታደግ መሆኑን ያስመሰከረበት ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ህዝቦች በሚገኙበት አገር ውስጥ የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ዜጎች በመንግስታቸው ላይ እምነት ሊያዳብሩ ይገባል። በተለያዩ አገራት ውስጥ ያሉ እስረኞች በነፃ እንዲለቀቁ በመንግስት በኩል የተደረገው ጥረት ይህን መሰሉ አመለካከት እንዲፈጠር ያደረገ ነው። የዜጎች ክብር እንዲህ በመንግስታቸው አማካኝነት ሲረጋገጥ ማየት እጅግ የሚያኮራ ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy